ከራስ ለራስ

0
1047

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሁለም ሰው እኩል ነው። ማንም ከማንም አይበልጥም፤ ማንም ከማንም አያንስም። ነገር ግን በተግባሩና በችሎታው የመበላለጥ ሂደት ውስጥ ይገባል። ለዚህ መበላለጥ ደግሞ ዋናውን ሚና የሚወስደው የራሱ የግለሰቡ አቅምና ለራሱ የሚሰጠው ቦታ ነው።

በተጨማሪም የራሱን ድክመትና ጥንካሬ ማመኑና አለማመኑም ግለሰቡ የሚገኝበትን ደረጃም ይወስናል። ከምንም በላይ ደግሞ ለራሱ የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ከሆነ፤ ማንም ከፍ ሊያደርገው አይችልም። ምክንያቱም ‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ…ባለዕዳ አይቀበለውም›ና።

አንዳንድ ጊዜ ከልጅነታችን ጀምሮ ይዘን የመጣናቸው ትንሽ የሚመስሉ ነገሮች ከጊዜ በኋላ ስር ሰደው ማንነታችን ላይ ተጽእኖ ሲፈጥሩ ይስተዋላል። በልጅነት እድሜያችን ጀግንነትን ለወንድ ፈሪነትን ለሴት፣ ወሬኛነትን ለሴት ከወሬ መቆጠብን ለወንድ፣ ጥንካሬን ለወንድ ደካማነትን ለሴት፣ ተመሪነትን ለሴት መሪነትን ለወንድ መድበው አሳዩን። እኛም ይህን ምድብ በልባችን መድበን ተግባር ላይ ሲውልም በቸልታ እየተመለከትነው እንገኛለን።

ራስን ማክበር መከበር ነው። አንዲት ሴት ልጅ ፈሪ የሆነን ሰው ለመግለጽ ‹አንተ ሴት!› የምትለው ከሆነ በተዘዋዋሪ እኔ ፈሪ ነኝ እያለች ነው። እንዲሁም ወሬኛነትን ለመግለጽ ‹ምን እንደሴት ወሬ ታመላልሳለህ› ካለች ሴት ልጅ ወሬኛ ስለመሆኗ ምስክርነት ሰጠች ማለት ነው። ወንድ ልጇ፣ ወንድሟ ወይም ባለቤቷ ማዕድ ቤት ገብቶ ለመሥራት ሲዘጋጅ ዐይታ ‹ምን እንደ ሴት ማድቤት ለማድ ቤት ያርመጠምጥሀል› ካለች፤ ‹ወንድ ወደ ችሎት ሴት ወደ ማጀት› ለሚለው አባባል ማረጋገጫ ሆነች ማለት ነው።

ሴት ልጅ የሴት ልጅን ማንነት አንኳሰው የሚገልጹ ሐሳቦችንና አባባሎችን ራሷ የምትደግፋቸው ከሆነ ራሷን በራሷ እንደበደለች ልትቆጥረው ይገባል። ሁሉም ነገር ከራስ ነው የሚጀምረው። ራስ እያጠፉ ሌላን አታጥፉ ማለት ከባድ ነው። በራስ ‹ራስን› እያሳነሱ ከሌላ ሰው ከፍ አድርጉኝ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት  ነው። ራስን ዝቅ ዝቅ እያደረጉ ወደ ላይ አውጡኝ ማለት ሩቅ የማያስኬድ ሐሳብ ነው።

ወንድ ልጅ ሲያለቅስ ያየች እንስት ‹ማልቀስ የሴት ልጅ ተግባር ነው› የምትለው ከሆነ ራሷን የአልቃሻነት መገለጫ ማድረጓን አምናለች ማለት ነው። አክላም ‹ወንድ ልጅ አደባባይ ላይ አያለቅስም። ይህ የኔ ሥራ ነው› ካለችውም ደካማነቷንና በቀላሉ ተስፋ ቆራጭነቷን አምና የእውቅና ሰርተፍኬት መቀበሏን ያሳያል።

ይህ ነው ለራስ ድክመት የራስን ሽልማት መስጠት። እንዲህ ሲባል ግን ማልቀስ የደካማነት መገለጫ ነው ማለት አይደለም። ሰውነት መታጠብ የሚጀመረው ከራስ ነው። ቅድሚያ ለራስ፤ ራስን ማወቅ። ለራስ ከፍተኛ ግምት መስጠት ራስን ለማበልጸግ ይረዳል። ራስን በራስ ማመን።

እህቴ! ሌላ ሰው ማድረግ የለበትም ብለሽ የምታስቢውን ራስሽ አታድርጊው። ከራስ ለራስ መልካምነትን አፍልቂ።

ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here