ቆቦ እንዴት ሰነበተች?

0
1826

ምልሰት

ጥቅምት 24/2013 ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የተፈጸመው ክስተት ለጦርነቱ መነሻ ነበር። በተጠቀሰው ቀን በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ ተሰማ።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ›› አወጀ። አዋጁ ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ›› ይባል እንጂ በወቅቱ ሲገለጽ እንደነበረው ከሆነ የለየለት ጦርነት ነበር። ጦርነትም ተባለ ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ››፤ ኹነቱ በትግራይ ክልል ለስምንት ወር ገደማ ዘለቀ።

በዚህም የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጦርነትና ርሃብ ሲፈራርቅባቸው እንደቆዩ የወቅቱ ተደጋጋሚ እሮሮአቸው እንደነበር አይዘነጋም።

ይህ አንዲህ እያለ ከስምንት ወር ገደማ ቆይታ በኋላ በጦርነቱ ምክንያት የአርሶ አደሩ የእርሻ ወቅት እንዳይስተጓጎል የሚለውን ጉዳይ አጽንኦት በመስጠት የፌዴራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አወጀ።

ሆኖም ግን ሕወሓት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከሐምሌ 2013 ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልል ጦርነት እንደከፈተ ይታወሳል። ከትግራይ ክልል የተነሳው ይኸው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልልም ተስፋፋ። ሰላማዊ ሰዎች፣ ወላድና አራስ እናቶችና ነፍሰጡሮችን ጨምሮ በክረምት ወቅት ከየኖሩበት አካባቢ መፈናቀል ግድ እንደሆናቸው መግለጻቸው የወቅቱ አሳዛኝ ክስተት ነበር።

በዚህ ኹኔታ ጦርነቱ ለስድስት ወራት ገደማ ዘለቀ። በዚህም ሕወሓት የአማራ ክልል እስከ ደብረ ሲና አፋር ክልልም እንዲሁ በድንበር አካባቢ ያሉ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችሎ የነበረ ሲሆን፤ ከስድስት ወር ገደማ ቆይታ በኋላ ጥምር ኃይል ባደረገው መልሶ የማጥቃት ‹የኅልውና ዘመቻ› ታጣቂ ቡድኑ የተስፋፋባቸውን ቦታዎች በታህሳስ ወር 2014 ለመልቀቅ ተገደደ።

በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ በ100 ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቄያቸው መፈናቀላቸው እንዲሁም መሠረተ ልማት እና ተቋማት መውደማቸው በየወቅቱ የሚነገር አሳዛኝ ዜና ነበር።

ይህ እና መሰል የደረሱ ጉዳቶች የጦርነቱ ውጤት ቢሆኑም፣ በኋላ አማራ እና አፋር ክልል ከታጣቂ ቡድኑ ነጻ ወጡ ተባለ። ተፈናቃዮችም ወደየቀዬአቸው መመለስ ጀመሩ። ሆኖም ግን ከዚያን ጊዜ በኋላም ጦርነቱ በተለይም በአማራ እና ትግራይ ክልል ድንበር አካባቢዎች ሲያገረሽ እንደቆየ በተለይም በራያ ቆቦ ዙሪያና አፋር ክልል ያሉ የመንግሥት አካላት ሲያመላክቱ ነበር።

በኋላ ላይ የድርድር ጉዳይ በተደጋጋሚና በብዛት ተነስቶ፣ ችግሩም በዚሁ መንገድ ይፈታል የሚል ተስፋ ተጣለ። መንግሥትም ድርድሩን የሚያሳልጡ ያላቸውን በኮሚቴ በማዋቀር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ። ይህ በእንዲህ እያለ የሕወሓት ቡድን ድርድሩን በሚመለከት ‹አደራዳሪዎቹን አላምንም› በሚል ሰበብ እንዳልተስማሙ ሲገልጽ ቆየ። ይህንንም ተከትሎ ባሳለፍነው ዓመት ነሐሴ 18/2014 ለሦስተኛ ጊዜ በአማራ እና አፋር ክልል ዳግም ጦርነቱ ተቀሰቀሰ።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በበኩሉ ታጣቂ ቡድኑ ከላይ በተጠቀሰው ቀን በአማራ በራያ ቆቦ ወረዳ ግራና ቀኝ ጦርነት ስለመቀስቀሱ በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ከዚህ በኋላም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ በአማራ ክልል ቆላማውና ደጋመው ክፍል የሚገኙ የገጠርና ከተማ ቦታዎች በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር ለመሆን ተገደዱ። ይሁን እንጂ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ጥምር ኃይል ባደረገው መልሶ የማጥቃት ሥራ የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ከመስከረም 22 እስከ 23/2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ለቆ እንደወጣ ዜናው ተሰማ።

ታዲያ ታጣቂ ቡድኑ በሦስተኛው ዙር ጦርነት ተቆጣጥሯቸው በቆዩ ቦታዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ ከደረሱ ጥፈቶች መካከል ሞት፤ ተገዶ መደፈር (ወንዶችን ጨምሮ)፤ መፈናቀል፤ መታገት፤ ዘረፋ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ውድመት ግንባር ቀደም እንደነበሩ የዐይን እመኞች ይመሰክራሉ።

በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በማስመልከት ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 አጠናሁት ባለው ጥናት፣ 240 ሺሕ 236 ሰዎች ላይ ሰብዓዊ ቀውስ እንደደረሰ ያሳያል። ሰባዓዊ ቀውሱ የግድያ፤ ድብደባ እንዲሁም ቀላልና ከባድ ጉዳቶችን ያጠቃለለ ነው።

ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን በተመለከተም ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ማለትም በሦስተኛው ዙር ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ሳያካትት 292 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ስለመውደሙ በጥናቱ ተረጋግጧል።

በተለይም በሦስተኛው ዙር ጦርነት የሕወሓት ታጣቂዎች ከትመውባት የቆየችው ከተማ ራያ ቆቦ መሆኗ ሲነገር ነበር። በዚህም ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳስከተለ መፈናቀል የቅንጦት ሆኖባቸው በጦርነት ቀጠና ውስጥ የኖሩ የዐይን እማኞች የተከሰተውን እውነታ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሞትና መደፈር

በቆቦ ከተማ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች ባላቸው መረጃ ብቻ በሦስተኛው ዙር ጦርነት ከ29 የሚልቁ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ተገድለዋል። በራያ ቆቦ ከተማ ዙሪያ አንዳንድ ለወዳጅ ዘመድ ስልክ ለመደወል ኔትወርክ ወዳለበት ቦታ (ቆቦ ሆስፒታል አካባቢ) የተሰባሰቡ ቁጥራቸው ከ15 ይበልጣል የተባለላቸው ሰዎች በድሮን ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል።

እንዲሁም በራያ አላማጣ፤ ኮረም፤ ራያ ቆቦ፤ አራም፤ ሮቢትና ጎብየ ዙሪያ ብቻ ከ275 የሚልቁ ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን በቦታው የነበሩ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ‹‹ቁጥራቸውን ባላውቅም ሰዎች ሞተዋል። ታጣቂዎቹ መሣሪያ፤ ምግብ፤ ብር አምጡ በማለት በበትር ያልደበደቡት ሰው የለም።›› ይላሉ።

‹‹ሰባት ሺሕ መሣሪያ ታመጣላችሁ›› የሚለው የሕወሓት ትዕዛዝ ሌላኛው በጦርነቱ ቀጠና ለነበሩ ሰዎች የእንግልት መንስኤ ነበር ተብሏል። በራያ ቆቦ ከተማ ቤታቸው ሲፈተሽ መሣሪያ ያልተገኘባቸው 10 ሰዎች ጫካ ውስጥ ታስረው ተደብድበዋል ሲሉ የተናገሩም አሉ።

በኹለት ቀናት ብቻ ከ200 ቢበልጡ እንጂ የማያንሱ መሣሪያዎችን ታጣቂ ቡድኑ ከአርሶ አደሩ አስገድዶ እንደወሰደም ተጠቅሷል። ራያ ቆቦ ከተማን ጨምሮ በወረዳው ዙሪያ የሚገኙ ዞብል፤ አሞራ ገደል፤ ዲቢ፤ አዲስ ዓለም፤ አቧሬ እና ሌሎች አካባቢዎች የመሣሪያ ነጠቃ የተከናወነባቸው ናቸው።

ከግድያ፤ መታገትና ዘረፋ በተጨማሪ ተገዶ መደፈር ጥቃት እንደተፈጸመ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

አንድ ባለታሪክ ለአዲስ ማለዳ የሆነችውን ስትናገር፣ ታጣቂዎች አራት ሆነው እንደደፈሯት አልደበቀችም። እለተ ሐሙስ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ተገዶ የመደፈር ጥቃት የደረሰባት እለት መሆኑ ለወጣቷ አይረሴ ትውስታዋ ሆኗል።

ሥሟ እንዳይጠቀስ አደራ ያለችው ባለታሪኳ፣ በራያ ቆቦ ወረዳ ቆቦ ከተማ ነዋሪ ናት። ሕወሓት ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልል ለሦስተኛ ጊዜ በቀሰቀሰው ጦርነት ታጣቂዎች በቡድን ሆነው ያደረሱባትን ‹‹አሰቃቂ ድርጊት›› በማስመልከት ለአዲስ ማለዳ ተከታዩን አለች።

‹‹ወቅቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። በተለይም በጳጉሜ ወር ውስጥ ሌሊት ይቅርና ቀንም በከተማው ሰው የሚኖር አይመስልም። ፀጥ፤ ረጭ ብሏል። ከታጣቂዎች በቀር ዝር የሚል የለም። የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ ቆቦ ከተማ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ ያልተፈናቀሉ ነዋሪዎችም ውሎ አዳራቸው ጓዳ ውስጥ ሆኗልና ነው። በተለይም እናቶች ወጣት ልጆቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ገድበዋቸዋል። እናማ ማንም የድረሱልኝ ጥሪ ቢለፍፍ የሚደርስ የለም።›› ስትል ጥቃቱ በደረሰባት ሰዓት ማንም ሊደርስላት ይችል እንዳልነበር ታወሳለች።

አክላም በታጣቂዎች ተገዳ የተደፈረችበትን ኹኔታ እንባ እየተናነቃት እንዲህ ስትል በአጭሩ ታስታውሳለች፤

‹‹በቅድሚያ አባቴን እግሩንና እጁን ቅፍድድ አድርገው አሰሩት። ከዛም በዙሪያዬ ከበው ቆሙ። ኧረ ስለፈጠራችሁ ተውኝ ብልም የሚሰማ የለም። እንዳልጮኽ አባትሽን እንገድለዋለን አሉኝ። አባቴ መጮኽ መንፈራገጥ ጀመረ። ግን ስለታሰረ ምንም ማድረግ የሚችልበት አጋጣሚ አላገኘም።…ታጣቂዎቹ የፈለጉትን አድርገው ወጡ። የእድሜ ልክ የልብ ስብራት አወረሱኝ።››

ይህም ቢሆን የደረሰባትን የልብ ስብራት ተቋቁማ የወደፊት ሕልሟን ከማሳካት ወደኋላ እንደማትል ገልጻለች። ወጣቷ ፖሊስ ሆኖ ወንጀለኛን በማጋለጥ ያሳደጋትን ሕዝብ ማገልገል በልቧ የታተመ የዓመታት እቅዷ ስለመሆኑ በወኔ ትገልጻለች። ወኔን የተላበሰ ገለጻዋ ለዓላማ ያላትን ፍላጎትም በግልጽ ያሳያል።

ባለታሪኳ ከስድስት ወር ገደማ በፊት አዲስ ማለዳ ለዘገባ ወደ ራያ ቆቦ ከተማ ጎራ ብላ በነበረችበት ወቅት በመጀመሪያው ዙር ጦርነት በከተማው ዙሪያ የነበረውን ዘርፈ ብዙ ትክክለኛ ክስተት ከገለጹ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናት።

ሌሎች በርካታ ሴቶች፣ ወንዶችም ጭምር ተገዶ የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ገልጻ፤ ‹‹ድርጊቱ አንገት የሚያስደፋ በመሆኑ ኹሉም ለመናገር ፈቃደኛ አይሆኑም። በእኔ የደረሰ አይድረስባችሁ!›› ስትል ንግግሯን ቋጨች።

በተለይም ያልተፈናቀሉና በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ የቆዩ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ በሦስተኛው ዙር ጦርነት የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በየቤቱ እየዞረ መሣሪያ እና ምግብ አምጡ ከማለት ባሻገር በቡድን በመሆን ሴቶችና ወንዶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ይፈጽም ነበር።

በቆቦ ከተማ የሚኖሩ አንድ የ65 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ፣ በጦርነት የተደፈሩት ሴቶች ብቻ ሳይሆን ወንዶችም ጭምር ናቸው ይላሉ።

አክለውም በየቤቱ እየተዘዋወረ መሣሪያና ምግብ ‹‹አምጡ›› ከማለቱ ባሻገር ወንዶችን ሳይቀር አስገደድዶ የመድፈር ጥቃት በማድረስ አሳፋሪና የዓለም ሕዝብ ማውገዝ ያለበትን ድርጊት ፈጽሟል ነው ያሉት። ከሦስተኛው ዙር ጦርነት በፊት በነበረው ጦርነት የተጠኑ ጥናቶች እንዲያሳዩት፣ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ተገደው እንደተደፈሩ ነው።

ለአብነትም በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ የማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከአማራ ምሁራን መማክርትና ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ድረስ በክልሉ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ጥናት ይህንን ጉዳይ አንስቷል።

ጥናቱ በክልሉ በሚገኙ በስምንት ዞኖች፤ በአንድ ከተማ አስተዳደር በ87 ወረዳዎች እንዲሁም 915 ቀበሌዎች ተደርጓል የተባለ ሲሆን፤ በዚህም ከ4 ሺሕ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።

ታዲያ በጥናቱ የተጠቀሰው ራሳቸውን ያጋለጡት እንዳሉ ሆኖ 29 ወንዶች በሕወሓት ታጣቂዎች ተገደው እንደተደፈሩ ወይም ግድረ ሰዶም እንደተፈጸመባቸው ነው።

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው ትዕግስት አጥናፉ የተባሉ የሥነ ልቦና መምህር በተለይም በጦርነት ወቅት በሰዎች ላይ ከባድ የሥነ ልቦና ጉዳት እንደሚከሰት ገልጸዋል። እንዲህ ዓይነት ችግር ባለባቸው ስፍራዎች በአስቸኳይ ሥነ ልቦና ምክር መስጠት ይገባልም ብለዋል።

በተለይም ተገዶ የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን እንዲሁም ወንዶችን ቀርቦ ምክር አገልግሎት መስጠትና ማማከር ከጭንቀት ያወጣቸዋልም ነው ያሉት።

ገበያ፣ ውሃ እና መብራት

‹ቆቦ እንዴት ሰነበተች?› ተብሎ ሲጠየቅ ሌላው ከነዋሪዎቹ የተገኘው ምላሽ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ያለው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። በከተማዋ የምግብ ፍጆታ ከአራት እጥፍ በላይ መናር እና ከአንድ ዓመት በላይ የውሃና የመብራት አገልግሎት መቋረጥ ፈታኝ እንደነበር ተጠቅሷል።

የምግብ ፍጆታ በሰላሙ ወቅት ሲሸመትበት ከነበረው ዋጋ በአራት እጥፍ መጨመሩ ለሸማቾች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ስለመሆኑ ተሰምቷል።

በቆቦ ከተማ ገበያ በሰላሙ ጊዜ ከ50 እስከ 60 ብር ሲሸጥ የነበረ ጤፍ ወደ 150 ብር፤ ከዚህ በፊት ዋጋው ከ40 ብር ልቆ የማያውቅ አንድ ጣሳ ማሽላ ከ80 እስከ 100 ብር፤ 70 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ክክ 270 ብር እንዲሁም 90 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ምስር ወደ 300 ብር ከፍ ማለቱ ተጠቅሷል።

የአምስት ፍሬ ሽንኩርት ዋጋ 100 ብር፤ በሌላ ወቅት 500 ብር ሲሸጥ የነበረ ሦስት ሊትር ዘይት ወደ 1 ሺሕ 500 ብር ንሮ እንደሰነበተም ነዋሪዎቹ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ገበያ ወጥተው የንግድ ልውውጥ በሚያደርጉበት ወቅት የሕወሓት ታጣቂዎች ብሩን እንደሚወስዱባቸው ነው። የሕወሓት ታጣቂዎች ገበያ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሲያደርሱት የነበረውን ‹ግፍ› በተመለከተ አንድ አርሶ አደር እንዲህ አሉ፤

‹‹በሬዬን ሽጬ ለማስተዳድረው ቤተሰብ እህል ለመሸመት ገበያ ወጣሁ። ገዢ ሲጠይቅ ታጣቂዎችም አብረው መጡ። ከገዢው ጋር በዋጋ እንድንስማማ ለማድረግ ሞከሩ። እኔ ግን ዋጋው አነስተኛ ስለሆነ ለመሸጥ ፈቃደኛ አልነበርኩም። ታጣቂዎቹ ሽጥ ብለው አስገደዱኝ። በሬዬን 35 ሺሕ ብር ሽጬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ነገር ግን ታጣቂዎች ተከታትለው ቤቴ ድረስ መጥተው ብሩን ነጠቁኝ።››

አክለውም ይህ አምናም ሆነ ዘንድሮ በአርሶ አደሩ ላይ የደረሰ ግፍ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የስኳር፤ ደም ግፊት፤ ኤች ኤ ቪ ኤድስ ሕሙማን የመድኃኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው እንዲሁም ለነፍሰጡር እናቶች ሕክምና አገልግሎት መቋረጡ ነዋሪዎቹን ለስቃይ የዳረገ ኹኔታ ነው ተብሏል።

በጦርነቱ የወደመው የውሃ መሠረተ ልማት ባለመጠገኑ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ውሃ የሚያገኙት ከወንዝ በመቅዳት አልያም የከተማ ከንቲባው በዘረጋው ውሃን በጀኔሬተር የመሳብ አገልግሎት መሆኑን ይገልጻሉ።

ለአገልግሎቱ ደግሞ የነዳጅ መወደድ መሰናክል እንደነበር የቆቦ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አዲሱ ወዳጆ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር።

ከውሃ ባሻገር የመብራት ችግር ደግሞ ሌላኛው ነዋሪዎቹን የፈተነ ጉዳይ መሆኑ ተነስቷል። በራያ ቆቦ ከተማ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠሩንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

ይህ ሁሉ እና ሌሎች በሂደት የሚሰሙ ነገሮች የራያ ቆቦ ዙሪያ ነዋሪዎች ለ37 ቀን ክራሞታቸው ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here