ለተፈናቀሉ ዜጎች የታሰበው የኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዢ ተራዘመ

0
543

የመንግሥት ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና ችግረኛ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚውል የኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴን ግዢ ላልተወሰነ ጊዜ አራዘመ።

በብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲገዛ የተጠየቀው ይህን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በጨረታው ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች በጨረታው ሰነድ ላይ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በመጠየቃቸው የስንዴው ግዢ ጨረታ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን አገልግሎቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የጨረታ ሰነዱን ከገዙ 52 ዓለም ዐቀፍ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል አራቱ በጨረታው ላይ ግልፅ ያልሆኑልን ነጥቦች አሉ በማለት ማብራሪያ በመጠየቃቸው ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ለመስጠት እና ሌሎች ተጫራቾች መሰል ጥያቄዎች ካሏቸው ማቅረብ እንዲችሉ ጨረታው ላልታወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገልጿል።
የጨረታው ሰነድ ከመስከረም 10/ 2012 ጀምሮ ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ጥቅምት 18/ 2012 ጨረታው ክፍት እንደሚሆን የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ገልጾ ነበር።

አብዛኛዎቹ የማብራሪያ ጥያቄዎች በማጓዝ ሂደቱ ላይ እንደሆኑ የመንግሥት ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መልካሙ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የሚገዙ እቃዎችን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ተጫራቾች በሚያቀርቡት ዋጋ ጅቡቲ ወደብ ድረስ እንዲያመጣ የሚደረግ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቦታ ከሌለው ተጫራቾች በራሳቸው ጅቡቲ ወደብ ድረስ እንዲያመጡ ይደረግ ነበር ብለዋል። አሁን አቅራቢዎቹ በራሳቸው እንዲያመጡ የሚያደረግ አሰራር መጀመሩ ለጥያቄዎቹ መንስኤ ነው ብለዋል።

ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚገዛው 2 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና ችግረኛ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚውል ነው።

በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት የሚለማው መሬት ወደ 1.8 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ ሲሆን ከዚህም የሚገኘው ምርት 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ የምርት መጠኑም በሔክታር 27 ኩንታል ነው። ይህም አገሪቱን በአፍሪካ በስንዴ ምርት ልማት በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

ሆኖም ግን አገሪቱ ለዜጎቿ የዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴን ከውጭ በማስገባት ታቀርባለች። ይህም ከአገሪቱ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታ 25 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ሲሆን፣ በዓመት ስንዴ ከሌሎች አገራት ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በአማካኝ 600 ሚሊዮን ዶላር ያህል ነው።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ገደማ ወጪ የተደረገ ሲሆን ለግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አንድ መቶ 55 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባቀረበው 6 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጉን አመላክቷል። በአጠቃላይም አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ የፈፀመ ሲሆን ለዚህም ግዢ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ይታወሳል።

ጨረታው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይከፈታል ተብሎ የሚጠበቀ ሲሆን የስንዴው ግዢ መዘግየት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና ችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለከፋ ችግር አያጋልጥም ወይ ስንል የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴን በስልክ ብንጠይቅም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here