ቤቱ ብዙም ሰፊ የሚባል አይደለም፤ ግን በጣም ትልቅ ነው። አንድም በዋጋ ለመተመን የሚከብድ፣ አንድም እጅግ ውድ የሆነ የታሪክ ማህደር ይገኝበታል። የኢትዮጵያን ታሪክ በራሷ ቋንቋም ሆነ በባዕዳን ቋንቋ የከተቡ እጅግ ጥንታዊ መጻሕፍት ይታያሉ። የቆዩ ሸክላዎች፣ ባርኔጣዎችና ሜዳልያዎች ይገኛሉ። ከመቶ ሀምሳ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ደብዳቤዎች፣ የኖሩ ጋዜጣዎች…ብዙ ብዙ።
ይህ ቤት ከበርካታ ዓመታት በፊት አልነበረም። ያገኘውን ሥራ መሥራት የሚቀናውና በዛ አጋጣሚ ሎተሪ ይዞ ይዞር የነበር አንድ ትንሽ ብላቴና የፒያሳ ኤንሪኮ አካባቢ ግርግር ስቦት ከመኖሪያው መርካቶ አካባቢ ይልቅ ውሎውን በዛ አደረገ። አሁን ፒዛ ዲ ናፖሊ ሬስቶራንት የሆነውና ለወትሮ የጣልያን መጻሕፍት ቤት ወደነበረው ስፍራ አቅንቶ ለጣልያኖቹ መላላክና ከመጻሕፍትና ንባብ ዓለም በግብር መተዋወቅን ትምህርት ቤት ከመመላለስ ይልቅ ወደደው።
ብላቴናው በእድሜ ከፍ ሲል፣ በ1985 በቤተ መጻሕፍቱ ለጣልያኖች ከመታዘዝ ባለፈ የራሱንም እንቅስቃሴ ለማድረግ እድል አገኘ። የእንግሊዘኛ ዘፈን ካሴቶችን ማቅረብ ጀመረ፤ ከዛ በደንበኞቹ ፍላጎት መጻሕፍትን ወደ ማቅረብ ዘለቀ። በዛ መልክ በቤተመጻሕፍት 16 ዓመታትን አገልግሏል።
ይህ ሰው አብዲ ነጋሽ ይባላል። የቅርስ አሰባሳቢ የሚለው ትልቅ ሥራውን በቀላል ለማስረዳት ያግዝ ይሆናል፣ እርሱ ለአገር ተቆርቋሪና የታሪክም ሰብሳቢ ጭምር ነው። ‹‹ይህችን አገር ያቆዩት ከኋላ የነበሩ ሰዎች ናቸው፤ እነሱን አለማክበር ውድቀት ነው።›› ብሎ ያምናል።
አዲስ ማለዳ መጽሔት ከተወሰኑ ወራት በፊት ከአብዲ ነጋሽ ጋር ሥራውን፣ ያሉትን ቅርሶችና ሰነዶች እንዲሁም የወደፊት ሐሳቡን በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥቂት ቆይታን አድርጋ ነበር። ያንንም መለስ ብለን በማውሳት ወደ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ይዘነው መጥተናል።
መርካቶ አካባቢ ነው የተወለድከው። መርካቶ ደግሞ ብዙ የግብይት እንቅስቃሴ አለ። እድገትህን እስኪ አጫውተን? ልጅ ሆነህ ምን ነበር የሚስብህ?
ልጅ ሆኜ አለማስቸገር የሚሉት ነገር ነበር የሚታገለኝ። ቤተሰብ ብዙ ነን። አባቴ አየር መንገድ ነበር የሚሠራው። እኔ እሱን ላለማስቸገር ሎተሪ ሁሉ አሸጥ ነበር፤ ከትምህርት ቤት ስመጣ። ታድያ ሎተሪ እሸጥና ቁርስ ምሳ እራት ራሴን ችዬ ነበር የምማረው።
በዛ አጋጣሚ ነው ወደ ጣሊያን መጻሕፍት ቤት በር ላይም የመጣሁት፤ ከመርካቶ ሎተሪ እየሸጥኩ። በኋላ ለጣልያኖቹ መላላክ ጀመርኩ፤ ተግባብቼአቸውም ወደ ካሴት ንግድ፣ ከዛ ወደ መጽሐፍ ገባሁ። ጣሊያኖቹ ናቸው ያስተማሩኝ። የእነርሱ የማንበብ ፍቅር ነው እኔን ወደዛ የሳበኝ። እናም ድሮ ልጅም ሆኜ ቢሆን ብዙውን መርካቶ አካባቢ ሳይሆን ራስን የማውጣት ነገር ነበር ትኩረቴ።
ብዙ ወንድሞች እንዳሉህ ነገርከኝ። አንተ ብቻ ነህ በዚህ ሙያ የገባኸውና ለየት ያልከው?
በዚህ ሥራ ማንም የለም። ዘጠኝ ነን የአንድ እናት እና የአንድ አባት ልጆች። ሁላችንም በመተሳሰብ ነው ያደግነው። ሁሉም ሥራዬን ደጋፊ ናቸው፤ ይንከባከቡኛል። ሁሉም በሌላ ንግድ እና በሌላ ሥራ ላይ ነው ያሉት። ይህንን ሥራዬን እንዳጎለብት፣ ለገንዘብ ሳይሆን ፍላጎቴን ይወዱታልና ምን እናግዝህ ይሉኛል። የምገዛበትም ሳጣ ከእነርሱ ነው ብዙ ጊዜ የምወስደው። አያስጨንቁኝም፤ እኔም ባዘዙኝ መሠረት እገኛለሁ። ከቤተሰብ ወጣ ያልኩ ነኝ፤ ብዙ ሰው የሚለኝ እንደዛ ነው።
አነስተኛ በሆነው በዚህ ቢሮ ውስጥ በርካታ የታሪክ መጻሕፍት፣ ሸክላዎች፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት የታተሙ ጋዜጦች፣ ሜዳሊያዎች፣ ታሪካዊም ሀይማኖታዊም የሆኑ በርካታ ቅርሶች ይታያሉ። ቅርስ መሰብሰብ ከምን ጀመርክ?
መጽሐፍ ነበር የምወደው። በጣም የቆየ መጽሐፍ ሳይ እደነግጥ ነበር። ጣሊያንኛ ለማወቅ ጉጉቱ ነበረኝና ጣሊያኖች አምጣ የሚሉኝን የጣሊያንኛ መጻሕፍት ነበር ብዙ የማገኘው። በጣም የሚስበኝ እና የሚያስደነግጠኝ የነበረው እንዳልኩሽ የቆየ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ፣ አስቀድሜ ከስር የማየው ዓመተ ምህረቱን ነው፤ የታተመበትን። የመጀመሪያውን እትም ስታገኝ የሚሰማሽን አስቢው፤ በ1850 የታተሙና እንዲያ የመሳሰሉ የቆዩ መጻሕፍት ሳይ እደነቃለሁ።
ከመጻሕፍቱ በኋላ ብዙ ነገር እንዳለን አወቅኩኝ። እኛ በአግባቡ አልያዝነውም እንጂ ብዙ ነገር ከሰው በፊት እንደነበረንና በጣም ብዙ ነገር እንዳለንም ጭምር ገባኝ። እና በአግባቡ ደግሞ ከያዝነው ትልቅ ነገር እንዳለን ተረዳሁ። ከዛ በኋላ ቆይቼ ነው ወደ ሸክላዎቹ የገባሁት።
በሙዚቃም ኢትዮጵያ የትና የት እንደ ነበረች ታዘብኩ። በሸክላ ሙዚቃ 1901 ያሳተምን፤ ያውም አንድ አይደለም ኻያ እና ሠላሳ፤ በ1920ዎቹ የጀርመን ኩባንያዎች የሸክላ ሙዚቃ ያትሙልን እንደነበረ፣ ያም <ፓርላፎን> የሚባል ነው። በ1940ዎቹ እንደዚሁ ፋሺስቶች ሙዚቃችንን እንዳተሙልን፣ …ወዘተ ስሰማ፤ ይህች አገር እንደዚህ ነበረች ብዬ በደስታ ነው ሥራውን የምሠራው።
በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አሉ። በፈረንሳይኛ፣ በጣሊያንኛ እና በጀርመንኛ የተጻፉ። መጻሕፍቱ እንዲተረጎሙ እንደምትፈልግም ሰምቻለሁ። እነዚህ መጻሕፍት ላይ የሚያስማማ ታሪክ ይገኛል ብለህ ታምናለህ?
ምን መሰለሽ! ይተረጎማል። ከዛ የምንቀበለውን እንቀበላለን፤ የማንቀበለውን እንተዋለን። ግን ዋናው ምንድን ነው፤ የሚያስማማንን መውሰድ። አንድ ጸሐፊ በሚጽፈው ላይ የራሱን ነገር ሳይጨምርበት አይጽፍም። ስንተረጉም ግን ቀጥታ እንተርጉመው። ምንም ነገር ሳንጨምር ሳንቀንስ። ከዛ ታዛቢ የራሱን ይወስዳል። እኛም መማሪያ ይሆነናል፤ የዛ ጊዜ እንደዚህ ነበርን እንዴ እያልን እንማርበታለን። ጥሩውን ደግሞ እናጎለብተዋለን፤ እናሳድገዋለን። ያንን ነው እኔ የምስማማበትና ደስ የሚለኝ፣ ከነምናምኑ ቀጥታ መተርጎሙ።
መጻሕፍትን ለውጭ አገር ዜጎች ትሸጣለህ?
አይ! ምን መሰለሽ! ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው እሸጣለሁ። መጽሐፍ ግን የሚሸጥ አለ፤ የማይሸጥም አለ። ተባዝቶ በጣም ብዙ የሆነውን በመላው ዓለም ላይ የሚገኝ ነገር የትኛውም ቤተ መጻሕፍት ሊገኝ የሚችል ከሆነ ትሸጭዋለሽ። የማይገኝ ከሆነ ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ቢቀመጥ ለኔ ደስታ ነው።
እኔም ጋር ቢቀመጥ፤ አሁን እዚህ ቁጭ ብለው የሚያነቡት አሉ፤ የማይወጣ። እሱ ደስ ይለኛል። የምሸጥላቸው ደግሞ አለ። ብዙዎቹ ፈረንጅ አገር የታተሙ ናቸው። እነሱን ብዙ ኮፒ ካለኝ ብሸጥ ችግር የለውም፤ ከእነሱ ጋርም ነው የመጣው።
ብዙ ጊዜ ግን ለአበሻ የምሸጠው ነው የሚበዛው። አሁን አሁን ደግሞ ብዙ አሉ፤ መጻሕፍትን የሚገዙ የነቁ አበሻዎች።
እዚህ ቤት ማን ማን መጥቷል? ማንስ መጥቶ የበለጠ አስደነገጠህ?
ብዙ ሰው መጥቷል፤ የማይመጣ የለም። ከመንግሥት ባለሥልጣናት መጥተዋል። ሙሓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት በተደጋጋሚ መጥቷል። ሙዚቀኞች ይመጣሉ። ሥማቸውን ባላነሳ ይሻላል። ቴአትረኛ፣ የፊልም ባለሞያዎች እንደነ ደበበ እሸቱ ይመጣሉ፤ ቤቱ መወያያም ነው። ቁጭ ብለን እናወራለን።
ታማኝ በየነን በሕይወቴ አስበው ነበር። እሱ ሲመጣ ደስ ብሎኛል። ዓለምፀሐይ ወዳጆም መጥታለች። በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሉ እንዲሁም ባለሥልጣናት መጥተዋል፤ ይመጣሉ።
የበፊቱ ቢሮህ መፍረሱን ተከትሎ እንጦጦ ፓርክ ውስጥ ቦታ ተሰጥቶሃል። እንዴት ሆነ?
ቢሮዬ ሲፈርስብኝ በጣም ከፍቶኝ ነበር። እና በማኅበራዊ ድረገጽ ላይ ጻፍኩኝ። ‹በጣም በጣም ከፍቶኛል። ከልጅነት እስከ እውቀት የሠራሁበትን ቤት በኹለት ቀን አፍርስ ተብያለሁ›› ብዬ ነው የጻፍኩት።
ከዛ በጣም ብዙ ሰው ነበር የደወለለልኝ። ሰው ይህን ያህል ያውቀኛል እንዴ እስክል ድረስ። ወደ 500 ሰው ጽሑፉን ሼር አድርጎታል (ተጋርቶታል)።
እና በጣም ነበር የከፋኝ፤ አለቀስኩ። እንዲህ ደክሜ ከሬዲዮ ጣቢያ፣ መጽሔት፣ ጋዜጣ የመሳሰሉት ከእኔ ነበር የሚወስዱት። የመንግሥት አካል ከዛሬ ነገ ቦታ ይሰጠኛል ብዬ እየጠበኩኝ እያለ በኹለት ቀን አፍርስ ተባልኩኝ።
ጥሩ ጥሩ ጓደኞች አሉኝ፤ በጣም ተባበሩኝ። እነሱ ወደዚህ ሱቅ እንድከራይ አደረጉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ‹አብዲ እንጦጦ ውስጥ ይሆንሀል ወይ?› ብሎ አንድ ታዋቂ ሰው ደወለልኝ። ከየት ነው ስለው ‹ከቤተመንግሥት አካባቢ ነው። እንጦጦ ብንሰጥህስ?› ሲለኝ፤ ለጊዜው የትስ ቢሆን፣ ደግሞ ንጉሥ ጠጠር ይስጥ ወርቅ እሺ ብሎ መቀበል ነው። ከዛ [ከቤተመንግሥት] አካባቢ ሰው ከሆነ እሺ ብዬ እቀበላለሁ በሚለው ተስማማሁኝ።
በኋላ ነብዩ ባዬ፣ ዳንኤል ክብረትና ሌሎችም ሆነው ከሳምንት በኋላ እንጦጦ ወስደው ያን ቤት አስረከቡኝ። እኔም ቤቱን በፕሮፌሰር መስፍን ስም ሰየምኩት። እርሱም ያን ሰሞን ነበር ያረፈው። እና ወደ እንጦጦ በመሄዴ አልተስማማም ነበር። ‹ለምን ትረከባለህ? አንተ የፒያሳ ከንቲባ ነህ።› እያለኝ እየተወያየን ነው፤ ከዛ በኋላ አንድ ሳምንት ሳይቆይ ነው ኮሮና ተይዞ ጳውሎስ የገባው።
እንደ አገር የምናውቀው ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ወይም ወመዘክር ነው። ቅርሶችን በግል መሰብሰብ የተለመደ አይመስልም። እዚህ ላይ ምን ትላለህ? በውጪስ ይህ ልምድ አለ? የምታውቀው ሄደህ ያየኸው ይኖር ይሆን?
በኢንተርኔት ነው የማየው፤ ይልኩልኛል። የተለያዩ አገራት የሚኖሩ ብዙ ፈረንጅ ወዳጆች አሉኝ። ማታ ማታ እጻጻፋለሁ። እና ‹ኢቤይ› ላይ ሽያጭ አያለሁ።
ማኅበራዊ ሚድያው ለእኔ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። የምደግፈውም ለዚህ ነው። ተራ ጭቅጭቅና ወሬውን ትተን ብዙ አስተማሪ የሆኑ ሰዎች አሉ። እኔም ብዙ ፈረንጆች ዐያለሁ፣ አንዳንዶቹ ያስደነግጣሉ።
ጂም ማርሻል የሚባል ሎሳንጀለስ የሚኖር ሰው አለ። አራትና አምስት ሺሕ የሚጠጉ የኢትዮጵያ መጻሕፍት አሉት። የሌሉት እቃዎችም የሉም።
አንድ ሰሞን ወመዘክር ጀምሮ ነበር፣ አንድ ታዋቂ ሰውዬ ጥንታዊ እቃ ወደ ተቋሙ ሲወስዱ ይከፍሏቸው ነበር፤ ከደብዳቤ ጋር። ለወመዘክር አቅራቢ ነበሩ። ትላልቅ ሰዎች ይህን ያውቃሉ፣ ከሚወጣ [ከአገር] እኛው እንግዛ በሚል ሰብረውም ቢሆን ይከፍሉና ይገዙ ነበር።
ለግለሰብ ታሪክ መሰብሰብ መብት ነው። ግለሰቡ ልጅዬው ጋር ሲደርስ ምን ይሆናል የሚለውን ግን መንግሥት ማሰብ አለበት። እኔ አለሁ፤ ስሞት ምንድን ነው ሊሆን የሚችለው? አንድ ሴት ልጅ አለችኝ፤ ስለዚህ ሥራ አታወቅም። ወንድሞች አሉኝ፤ ስለዚህ ጉዳይ በስፋት የሚያውቁት ነገር የለም። ምን ይሆናል ብሎ መንግሥት መጨነቅ አለበት።
አንዳንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚደንቅ ቅርስ አለ፤ የነገሥታት ቁሳቁሶችና ዕቃዎች የመሳሰሉት፣…ወዘተ ያ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ በየቤቱ። እነርሱ ያንን በውዴታ በአገር ወዳድነት ቢሰጡ ጥሩ። ከዛ ውጪ ኑሮአቸውን፣ መጦሪያቸውን አመቻችቶ ገንዘብ ቢሰጣቸው በቅርብ አገኛለሁ ብሎ መንግሥት ቢገዛ ደስ ይለኛል።
ያም ብቻ ሳይሆን ከአየር መንገድ ጋር ያለው ግንኙነት መጥበቅ አለበት። እዛ አገር ወዳድ ሰዎች መቀመጥ አለባቸው፤ በትንንሽ ነገር የሚታለሉ መሆን የለባቸውም። ዶላር ስትይዢ የሚይዙ የታሪክ እቃዎችን ግን ዝም ብለው የሚያሳልፉ አሉ። ሁሉም ግን አይደሉም። ሥልጠናውም ስለሌለ ነው፤ ጥንታዊ የአገር ቅርስ ምን እንደሆነ።
ፈረንሳይ ውስጥ የኢትዮጵያ የሆነ የሌለ ነገር የለም። ስዊዘርላንድ፣ ጣልያን እንዲሁም እንግሊዝ ደግሞ የባሰበት ነው። እንግሊዝ ግለሰቦች ላይ ያለው የንጉሣዊ ንብረቶች ብዙ ናቸው። አገር ሲረጋጋ ይዘዉት ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ።
ገፍቶ የሚመጣና እንቀበል የሚልህ የሚል አካል ካለስ?
ለአንቺ ቦታና ጊዜ ካመቻቹልሽ አንቺ ሰብስበሽ ታቆያለሽ። በአንድ ወቅት ግን ለአገር ነው የምትተይው። ሰማይ ቤት ይዘሽው አትሄጂም። ስንኖር ድጋፍ ማድረግ፤ ከነቁጥጥራቸው ጭምር። የግድ አንድ ቦታ ወመዘክር መሆን የለበትም። እንደውም ጥሩ አስበው ነበር፣ በየኮንዶሚንየም ቤተመጻሕፍት ይከፈታል ብለዋል። ይህን ስሰማ ደስ ብሎኝ ነበር። እኔም ባለሁበት እሠራለሁ ብዬ አስቤም ነበር።
እንዳልኩት የነጠሩ እቃዎች አሉ፤ ለአገር የሚጠቅሙ ትላልቅ የሙዝየም እቃዎችና እንደዛ ያሉ ሀብቶች ያሏቸው ሰዎች አሉ። እነሱን ሰዎች መንከባከብ። ሲያልፉም ይሁን ከመሞታቸው በፊት አምጥተው ሊያስረክቡት የሚችሉ የሚያምኑት አካል ይፈልጋሉ።
ያንን ነው የምንፈልገው እንጂ፣ እኔኮ ብሞት አንድ ኃይል ይመጣና ወንድሞቼም ቢሆኑ ወስደው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም ለእገሌ ብለው ሊሰጡት ይችላል። ግን በበለጠ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ አሉ። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደክሙትን ታያለሽ፤ ቤተመጻሕፍት ለመክፈት። እኛ ከስር ከስር የያዝናቸውን እዛና እዚህ ቢገቡ ብለን ማሰብ አለብን።
እንረዳዳና እንደግ ነው። በቤተመጻሕፍትና ሙዝየሞች በተቋቋሙ ቁጥር ከየት አምጥተን እንሞላለን ብለው እንዳይጨነቁ ግለሰቦች ጋር እንዳለ ማወቅ አለባቸው። በየክፍለ አገር ብዙ ሰዎች ጋር አለ። ጅማ፣ አምቦ፣ ሥልጣኔ የነበራቸው አካባቢዎች። ፒያሳ ራሷ ቅርስ ናት። ንብረት ወይም ቅርስ እቃ ብቻ አይደለም።
የታዋቂ ሰዎችን ቤት አሁን ስናፈርስ ምን እናደርገዋለን? መሬት አላጣንም፤ ስንት ክፍት ቦታ አለ። ሌላ ከተማ መፍጠር እንችላለን። ደጃች ውቤ ሲፈርስ ስቀስቅ ብዬ ነው ያለቀስኩት። እነ ሜሪ አርምዴ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ በዓሉ ግርማ፣ ስብሃት ገብረእግዚአብሔርን የመሳሰሉ ምሳሌዎቻችን ጥሩ ጊዜ ያሳለፉበት ነው። ቤቱ ራሱ ትንሽ ደሳሳ ጎጆ ነው። ይረሳልኮ! አንዳንዴ ለትውልድ ሲነገርም ውሸት ነው የሚመስለው። እነዚህን ቤቶች ማን ይሆን ጨክኖ እጅ ያነሳባቸው ትያለሽ።
እኔ የነበርኩበት ሱቅ ማለትም የፈረሰው ቤት በ1924 የተሠራ ነው፤ ግሪኮች ናቸው የሠሩት። ከዛ ይልቅ ያናደደኝ አረአያሥላሴ ኃይሌ የተባሉ የወመዘክር ሥራ አስኪያጅ በ1949 በዘጠኝ ሺሕ ብር የገዙት ቤት ነው። እና እርሳቸው ከለቀቁት በኋላ ደርግ ወረሳቸው። ደርግ ምርጥ ቤት እንደሆነ ስላወቀ የሴኔጋል አምባሳደር መኖሪያ አደረገው። ከዛ በኋላ የመጣው መንግሥት የአንድ የውጭ ድርጅት አደረገው። ከዛ ተስፋ ጎህ የኤድስ ሕሙማን መርጃ ድርጅት ገብቶ ሠርቶበታል።
ብዙ የኪነ ሕንጻ ባለሞያዎች ተደንቀው ፒያሳ አይነካ የሚል ማኅበር አቋቋመው እንደነበር አስታውሳለሁ። መንግሥትና መሣሪያ ከአቅም በላይ ሲሆን ሰዎች ይዳከማሉ፤ ከመሣሪያ በታች ከሆንሽ ምንም ነገር ሲሆን ዐይንሽ እያየ እርጅና ይመጣል። ከዛ በኋላ የፈረሱ ብዙ ምርጥ ቤቶች ነበሩ። ፈርሰው ክፍት ሆነው ይታያሉ። በዚህኛው ስርዓት መንግሥታዊ ማእከላት ይሠራባቸዋል እያሉ ነው። የፈረሰውን ግን አያካክስም፤ ታሪክ ነው የጠፋው።
የሃይማኖት ይዘት ያላቸው ቅርሶችና መዛግብት አሉህ። የእስልምናም የክርስትናም። በግልህ የእስልምና እምነት ተከታይ ነህና፤ እንዴት ነው ይህን የምታቻችለው?
የእምነት ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው ለእኔ። እኛ ያለን እነሱ ጋር የሌለ ከሆነ አብያተ ክርስትያናት ቢወስዱት ደስተኛ ነኝ። በጻድቃኔ ማርያም ለሚገኙ አንድ አባት እንዲህ የሰጠኋቸው አሉ። መጽሐፈ መነኮሳት ኮፒ አድርገን ጠርዘን እንሰጣለን።
እነሱ የበለጠ የሚጠቀሙበት ከሆነ እዛ እንዲቀመጥ ብለን ነው። 150 ዓመትና ከዛ በላይ እድሜ ያላቸው መጻሕፍት አሉ። የካቶሊክም፣ የወንጌላውያንም አሉ። አናሲሞስ ነሲብ መጀመሪያ በአፋን ኦሮሞ በቁቤ የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ አለ። እነሱን በሙሉ የሚገባው ቦታ ብለሽ ትሰጫለሽ። ዋናው አገርን ማገልገል ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



