ግንዛቤው

0
1061

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የያዝነው የጥቅምት ወር ስለ ጡት ካንሰር ግንዛቤ የሚሰጥበት ወር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጡት ካንሰር በተለይ ሴቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃት ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ላይ ሲነገርና ሲጻፍ ተከታትለናል። የተለያዩ የግንዛቤ መስጫ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል ሲባልም አድምጠናል።

ግንዛቤው ግን ምን ያህል እንዳስገነዘበ ለማወቅ ያስቸግራል ለምን ያህል ሰዎችም ተደራሽ እንደነበር ለማወቅ ያዳግታል። በተለይ ወደ ገጠሪቷ የአገራችን ክፍል ይህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ምን ያህል ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነና ነዋሪዎቹም ግንዛቤውን በደንብ መገንዘባቸውን በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል።

ይህ ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚያጋጥሙ የካንሰር ዓይነቶች በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ወጣት ሴቶች ላይ በስፋት ይከሰታል። የበሽታው ዋነኛ መንስኤዎች በእርግጠኝነት ባይታወቁም በተካሄዱ ጥናቶች ላይ ግን እድሜ (ከ50 ዓመት በላይ) የጡት ካንሰር የመያዝ እድልን የሚጨምር ሲሆን፣ በዘር የሚመጡ የዘረመል ለውጦች፣ ከወለዱ በኋላ ጡት አለማጥባት፣ የጡት ካንሰር የቤተሰብ ታሪክ ሲኖር፣ ከአቅም በላይ ውፍረትና አልኮል መጠጣት የመሳሰሉት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችል ተገልጿል።

ስለሆነም ሴቶች ከእነዚህ ተግባራት ማለትም ከሲጋራ፣ ከአልኮል እንዲሁም ከአላስፈላጊ ጨረር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ይመከራሉ።

ብዙ ጊዜ ለተለያዩ ነገሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። ነገር ግን እነዚህ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ምን ያህል አመርቂና ለሁሉ ተደራሽ ናቸው? ተገቢነታቸውስ ምን ያህል ነው? የተፈለገውንስ ግብ የሚመቱ ናቸው? ግንዛቤው መሰጠቱን ለመግለጽ ነው ወይስ መሰጠት ስላለበት ነው የሚሰጠው? ግንዛቤው የሚሰጠውስ ለተገቢውና በተገቢው ሰው ነው? ግንዛቤ ሰጪው አካልስ በቂ ግናዛቤ አለው? የሚሰጥበት ቦታስ የት ነው? ለእነዚህና ለተጓዳኝ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል።

አንዳንድ ጊዜ ለደንቡና ተደረገ ለመባል ብቻ የተለያዩ ዝግጅቶች ይከናወናሉ። ዓላማና ዒላማ የሌላቸው ግንዛቤ መስጫዎች እንደውም ውዝግብን ይፈጥራሉ። እናስገነዝበዋለን ብለን የሰበሰብነው ሰው አለማወቃችንን ተገንዝቦ ይሄዳል። እውቀት እናስጨብጠዋለን ብለን የሰበሰብነውን ሕዝብ ውሀና አበል ጨብጦ እንዲሄድ እናደርገዋለን። የመጣበትን ዓላማ እናሳጣዋለን። አንዳንዴም የነበረውንም ግንዛቤ እናስጠፋዋለን። መጀመሪያ አሠልጣኙ ወይም አስገንዛቢው ሊሠለጥንና ሊገነዘብ ይገባል። እሱ ያመነበትን ጉዳይ ለሌላው ቢገልጽ ሰሚውም በቶሎ ያምናል።

ወደ ቀድሞው ነጥቤ ልመለስ፤ ሴቶች በጡት ላይና በጡት አካባቢ የሚወጣ እባጭ፣ የጡት መጠንና ቅርጽ መለያየት፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መገልበጥ፣ በተወሰነ የጡት ቆዳ ላይ የመጠንከር ስሜት ካጋጠማችሁ የጡት ካንሰር ሕመም ምልክቶች ስለሆኑ በጊዜ ወደ ሕክምና ቦታ በመሄድ ሐኪሞችን ማማከርና መመርመር ያስፈልጋል። ሐኪሞችና አሠልጣኞችም ኅብረተሰቡን የማስገንዘብ ተግባራቸውን በተገቢው መንገድ ሊያከናውኑ ይገባል።

ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here