ዳሰሳ ዘ ማለዳ ጥቅምት 19/2012

0
655

1– በኢትዮጵያ ለ10 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል የተባለው እና 300 ሚሊዮን ዶላር የተበጀተለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።  ማስተር ካርድ ፍውንዴሽን ከስራ ፈጠራ ኮሚሽን በጋራ በመሆን በመጪዎቹ ዐስር ዓመታት ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።አዲሱ ፕሮጀክት “ወጣቷ አፍሪካ በኢትዮጵያ ትሰራለች” በሚል መርህ መጀመሩም ተገልጿል።በመጀመሪያ ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ አራት አጋሮች የተለዩ ሲሆን በዚህም በተመደበው 119 ሚሊዮን ዶላር ለ1 ነጥብ 4ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጠራል ተብሏል።(ኢቢሲ)

……………………………………………………………..

2-በባሌ ሮቤ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች የሮቤ ነዋሪዎች ከፌዴራልና ከክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የሰላም ኮንፍረንስ ተካሄደ።ባሌ የምትታወቀው በሃይማኖትና በብሄር መቻቻል በመሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት በሮቤ የተከሰተው ኹከት በፍፅም ይህንን ሕዝብ የሚወክል ተግባር አይደለም ሲሉ የገቢዎች ሚኒስቴር አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

……………………………………………………………..

3-በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ ባለፈው እሁድ ጥቃት የተፈጸመበት የገምሹ በየነ የግንባታ  ኩባንያ ሰራተኞች በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው መውጣት መጀመራቸውን ተናገሩ። ሰራተኞቹ ባለፈው እሁድ በኩባንያው ንብረቶች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ከአካባቢው ለቀው እንዳይወጡ በአካባቢው ነዋሪዎች ታግደው እንደነበር ተናግረዋል። (ዶይቼ ቬለ)

……………………………………………………………..

4-በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትየጵያውያን ላይ እየተባባሰ የመጣውን የመብት ጥሰትና የተለያዩ ጥቃቶችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።በተለያዩ ወቅት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ በመምጣቱ ይህንን ችግር ለማቃለል በሊባኖስ ለከፋ የመብት ጥሰትና ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ ዜጎችን በፈቃደኝነት ላይ በመመስረት በቅርቡ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው ተናግረዋል።ወደ አገራቸው መምጣት ለማይፈልጉ ዜጎችን ደግሞ ባሉበት አገር ችግራቸውን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………………..

5-የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት ከተያዙ 91 አዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የ5 ፕሮጀክቶች የጨረታ ሂደት መጠናቀቁን አስታወቀ።በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር  ሳምሶን ወንድሙ እንደተናገሩት በያዝነው በጀት አመት ቀድሞ የተጀመሩ 25 ሺሕ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሸፍን የመንገድ ግንባታ በ364 አገር ውስጥና በውጪ ተቋራጮች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።(ኢቢሲ)

……………………………………………………………..

6-በኢትዮጵያ በተከሰቱ ኹከቶች የተሳተፉ አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ ። በተለይም በሲዳማ፣ በአማራ ክልል የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በአፋርና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች እንዲሁም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እየመረመረ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።በነበረው አለመረጋጋት ከ70 እስከ 80 ሰዎች ተገድለዋል ያሉት ኮሚሽነሩ ከዚህ ውስጥ 10 ሰዎች በጸጥታ ኃይል እርምጃ እንደሞቱ ገልጸዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………………..

7-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ላለበት የማጣሪያ ጨዋታ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጉን አስታዉቋል።ብሔራዊ ቡድኑ ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር በኅዳር ወር መጀመሪያ ለሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ ጥሪ ማቅረቡን ገልጿል።(ዋልታ)

……………………………………………………………..

8- በአዲስ አበባ ለሦስት አዳዲስ የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ መውጣቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድወሰን አንዱዓለም እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ለሦስት ኤፍ ኤም ሞገዶች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ወጥቷል።በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡ ተጫራቾችን በመለየት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።(ኤዜአ)

……………………………………………………………..

9-በኮሬ ብሔረሰብ እና በጉጂ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በጋሞ ባይራ የሐገር ሽማግሌዎች በባህላዊ እርቅ ስነ ስርዓት መፈታቱን ገልጸዋል። በተፈጠረው ግጭት የበርካቶች ሕይወት በመጥፋቱ እና ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተከትሎ የኮሬ ብሔረሰብ የጋሞ ባይራ ሐገር ሽማግሌዎች እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ በጠየቁት መሰረት በኢትዮጵያ የሰላም ተምሳሌት የሆኑት ጋሞ ባይራ የሐገር ሽማግሌዎች የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ወደ ግጭት የገቡትን ኹለቱን አካላት ከ6 ጊዜ በላይ ተመላልሶ በማወያየት እና በማደራደር ሰላም እንዲወርድ አድርገዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………………..

10-ዛሬ በዋለዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት የቀድሞው ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ኡመር በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል “ክልሉን በጥሩ ሁኔታ ከማስተዳደር ውጪ ወንጀል አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” ሲሉ ተናገሩ።በአብዲ መሐመድ ኡመር የክስ መዝገብ እስካሁን ያልቀረቡ ሰባት ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸውና ውጤቱ ለኅዳር 22/2012 እንዲቀርቡ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰቷል።(ዋልታ)

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here