የተገላገሉት ምጥና ፈተና

0
754

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች መካከል የ12ኛ መልቀቂያና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተናውንና ተፈታኞቹን የተመለከተውን የሚደርስበት አልነበረም። ከእቅዱ ጀምሮ ወደዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የነበረው አቀባበል በብዙዎች ሲወራ ሰንብቶ ነበር።

የዋዜማው ሰሞን ግን ከፈተናው የማይገናኝና ያልተጠበቀ ክስተት ዋና አጀንዳ ሆኖ ነበር። ለፈተና መጥተው ወለዱ የሚባሉ ተማሪ እናቶች ሁኔታ እጅግ የተጋነነ ሽፋን አግኝቶ ነበር። አንዲት ሴት እየመሰለቻቸው በየዩኒቨርሲቲው የወለዱ ሴቶች ታሪክ ይፋ ሲደረግ ቁጥሩ እየቆየ ማሻቀቡን የተመለከቱ ከመገረም አልፈው ለማሸሞር የሞከሩበት ነበር።

ይህን ያህል ሴቶች የወለዱት ምን ሲያደርጉ ከርመው ነው? በሚል በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። በእርግጥ ያገቡና ትልልቅ ሴቶች ፈተናውን ለመውሰድ ወደዩኒቨርስቲዎቹ መግባታቸው ቢታወቅም፣ በሰላም ተገላግለዋል የሚል ምስላቸውን የያዘ ዘገባ ሲሰራጭ ውሎ አድሯል።

ትምህርት ሚኒስቴር ወላድ እናት የሆኑ ተማሪዎች ለመፈተን እንዳይመጡ መከልከሉንና ይህ ቢሆንም ግን ፍተሻ አልፈው ወደመፈተኛ ገብተው መገኘታቸውን ተናግሯል። ሞባይልን ሲያስሱ ሲበረብሩ የነበሩት የጸጥታ አካላት፣ ቦርጭ መስሏቸው ነው ወይስ አሳዝነዋቸው ያስገቧቸው በሚል ቀልድ ቢሰነዘርም ምላሽ አላጣም። በርብሩ የተባሉት መኮረጃ እንጂ ፅንስ አይደለም በማለት ነፍሰጡሮቹ ከልጆቻቸው ስለማይኮርጁ አስገብተዋቸዋል ብለው አስተያየታቸውን ቀልድ ቀብተው የሰጡም ነበሩ።

መንግሥት የወለዱ መኖራቸውንና ሌላ ጊዜ ትፈተናላችሁ ቢባሉም ሳይሰሙ ስለተገኙ እንዳልተከለከሉ ተናግሯል። በእርግጠኝነት ምን ያህል ሴቶች እንደወለዱ ባይነገርም፣ ለእያንዳንዳቸው በወለዱበት ሆስፒታል አንድ ፈታኝ መምህርና ጠባቂ የጸጥታ ኃይል ተመድቦላቸው እንደነበር ከተሰራጨ ምስል ጭምር መመልከት ይቻል ነበር።

አንዳንዶች ግን ወልደው ወዲያው ወደመፈተኛ ገብተው እንደተፈተኑ ቢነገርም፣ ጨቅላ ሕጻናቶቻቸውን ማን እንደያዘላቸውም ሆነ ማን እያረሳቸው እንደሆነ ምንም የተባለ ነገር የለም።

አንዳንዶች የወሊዱ መጠን ሲጨምርባቸው ለማጣራት ያደረጉትም ሙከራ ነበር። ከአጠቃላይ ተፈታኞች ከ80 በላይ በቅርቡ የወለዱና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የወለዱ እመጫቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ሌሎች 100 የሚደርሱ ተማሪዎችም የመውለጃ ጊዜያቸው የደረሰ ነው በሚል ተመዝግበው ይሁን ገምተው ማረጋገጥ የማይቻል ቁጥር ይፋ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

ያም ተባለ ይህ፣ ተማሪዎቹ በዚህ መጠን ከወለዱ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ምን እንደሚያደርጉ የተነበዩም ነበሩ። ልጆቻቸውን ጥለው ነው ወይስ ይዘው የሚማሩት በሚልም አስተያየት የሰጡ ቢኖሩም፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው እንደሚወልዱ በርካቶች የእነሱም እጣፈንታ ተመሳሳይ ይሆናል በሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የ12 ዓመት ትምህርታቸውን ጨርሰው የመልቀቂያ ፈተናውን በሚገላገሉበት ወቅት፣ የ9 ወር ሸክማቸውን በሰላም መገላገላቸው ጥሩ ነው። የፈተናው ውጤታቸውን ወዲያው አውቀው ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንዲሆንላቸው የተመኙም አሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here