አዳጊ ጥበበኞችን በአንጋፋ መድረኮች

0
1099

ዛሬ ላይ አንጋፋ የተባሉ በስስት የሚታዩና በጉጉት የሚሰሙ በየዘርፉ ያሉ የጥበብ ሰዎች ትላንት ጀማሪዎችና አዳጊዎች ነበሩ። በሙያቸው ‹አማተር› እየተባሉ ይጠሩ የነበረበት ዘመንም ሩቅ ያልሆነ፣ አሁን ላይ እውቅ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ብዙ ናቸው። አሁን ለደረሱበት ደረጃ አንድም መድረክ ሰጥቶ ያገዛቸው፣ አንድም እድል ነፍጎ አዲስ መንገድ እንዲያዩ ግድ ያላቸው አጋጣሚ ትልቅ ድርሻ አለው።

በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ አዳጊ ጥበበኞች እድል ያገኙ የነበረው በተለያዩ የኪነት ቡድኖችና ክበባት ውስጥ ነበር። አሁን ላይ ግን እነዚህ እድሎች የሉም በሚባል ደረጃ ደርሰዋል።

ይህን ጉዳይ እንድናነሳ ሰበብ የሆነን በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝም እና ኪነጥበብ ቢሮ የኪነጥበብ ሀብቶች ልማት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ የሥነጽሑፍ ምሽት መርሃ ግብር ነው።

‹አሻራችን ቀንዲላችን ማዕዳችን› የሚል ኃይለ ቃል የነበረው ይኸው መሰናዶ፣ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትንሹ አዳራሽ የተካሄደ ነው። በዚህም ላይ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በኪነጥበብና ሥነጽሑፍ ዘርፍ ያሉ ጀማሪና ወጣቶች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። የሥራዎቻቸው ጭብጥም ከመድረኩ ኃይለ ቃል ጋር የተናበበ፣ ታላቁን የሕዳሴ ግድብና አገራዊ ዕይታዎችን ያነሳ ነበር።

ግጥሞች፣ ወጎችና መነባንቦች ናቸው የቀረቡት። የዳኞችን ዕይታ መሠረት በማድረግም በደረጃ ከአንድ እስከ ሦስት በየዘርፉ የገንዘብ እና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝም እና ኪነጥበብ ቢሮ የኪነጥበባት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሐት፤ ቢሮው ትልቅ አገራዊ መልዕክቶችን የተሸከሙ ከአማተር እንቅስቃሴዎች ጋር የተናበቡ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎችን አጉልተው የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች ማድረጉን ጠቁመዋል።

በ2014 ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መድረኮች በቢሮው ተዘጋጅተዋል። ከዚህም ባሻገር የሥዕልና የፎቶ አውደ ርዕዮች፣ የተለያዩ የጥበባት ክዋኔዎችን በአንድ ላይ የያዙ መድረኮችን ቢሮው ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።

ይህ መድረክ በነባር የኪነጥበብና የሥነጽሑፍ ምሽቶች ላይ ታክሎ፣ የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት ተደራሽ በሚያደርጉ መልኩ፣ ክፍለ ከተሞችን ሁሉ እንዲያካትት ሆኖ በሰፊው እንደሚዘጋጅና ለዛም ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ሰርፀ በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ከዚህ መድረክ አንድ የምንረዳው ነገር፣ አማተር ለሚባሉ የኪነጥበብ ‹ባለሞያዎች› እንደ አገር ፍቅር ያሉ አንጋፋ መድረኮች ላይ ቦታ ማግኘት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ነው። ይልቁንም በኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ዘመናት የነበሩና አሁን ደብዝዘው ከነመኖራቸው የተዘነጉ የኪነት ቡድኖችና ክበባትን ያስታውሰናል።

ስለአማተር ከያኒያን

ሰርፀ ፍሬስብሐት በአሻም ቴሌቭዥን በአሻም ፈትል መሰናዶ ላይ በነበራቸውና ‹መታሰቢያነቱ ለማዲንጎ አፈወርቅ ይሁን› ባሉት ቃለመጠይቅ ላይ ለአዳዲስና አማተር ከያኒያን መለማመጃ የሚሆኑ አውዶች ስለመጥፋታቸው አንስተው ነበር። ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በልጅት ዘመን የተቀላቀለውና ለሙያው መሠረት የሆነው አንድም የኪነት ቡድን መሆኑን አንስተዋል።

‹‹አሁን መለማመጃ ትምህርት ቤት የለም፣ የክበብና የኪነት እንቅስቃሴ የለም። ድንገት ነው ድምጻዊ የሚኮነው፣ ባለሞያዎችን መቅረጫ የነበሩ ተቋማት ፈርሰው ስላለቁ።›› ብላዋል።

እርግጥም ነው። አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ እንዳዘጋጃቸው ዓይነት መድረኮች ካልተፈጠሩ አልያም በየክፍለ ከተሞቹና ወረዳዎች ያለውን እንቅስቃሴ ሥራዬ ብሎ በትኩረት መያዝ ካልተቻለ፣ ነገ ላይ አንጋፋዎችንና የሚደነቅ ሥራ የሚሠሩ ባለሞያዎችን የማግኘቱ ነገር አድካሚ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ዳዊት ንጉሡ ረታ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ መለስ ብለው 1980ዎቹን ያወሳሉ። ዘመኑንም ‹‹በወቅቱ በአማተር የቴአትር፣ የሙዚቃ፣ የጋዜጠኝነትና የሥነጽሑፍ ክበባት ሁሉም እንደየችሎታው ተደራጅቶ፣ ከባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ሕጋዊ ፈቃድ በማግኘት የሚንቀሳቀስበት ወርቃማ ዘመን!›› ይሉታል።

ከዚህም ጋር አያይዘው የተወሰኑ ባለሞያዎችን በመጥቀስ አማተር ከያኒያንን በመመልመል፣ በማሠልጠን ብሎም መድረክ እንዲያገኙ በማስቻል የሠሩትን ሥራ አብራርተዋል። ለአብነት ተስፋዬ ሲማ ተጠቅሷል።

ዳዊት በጽሑፋቸው፣ ‹‹ይህ የጥበብ ባለሙያ በአንድ ዙር እስከ 60 የሚደርሱ ወጣቶችን በመመዝገብና የማወዳደሪያ ፈተና በማውጣት አምስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው በወቅቱ የስፖርት ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ልክ እንደ መደበኛ ትምህርት የቴአትር ጥበባት ትምህርት ይሰጥ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ትምህርቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የቴአትር ጥበባት ኮርስ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ሲሆን፣ ልዩነቱ የጊዜ ብቻ ነው። ተስፋዬ ሲማ ያንን ሥልጠና የሚሰጠው ለሦስት ወራት ብቻ ነበር።›› ይላሉ።

በዛ ሥልጠና ተሳትፈው አሁን ላይ በዘርፉ አንጋፋ ከሆኑት መካከልም ኮሜዲያን አስረስ በቀለ፤ አለልኝ መኳንንት ፅጌ፣ ጥላሁን ዘውገ፣ ተፈራ ወርቁ እንደሚገኙበት ያስታውሳሉ።

እንደዛው ሁሉ ተስፋዬ አበበ ወይም ፋዘር (የክብር ዶክተር) ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። አሁንም ድረስ ወጣቶችን በነጻና በፈቃደኝነት በማሠልጠን የሚታወቁት ተስፋዬ አበበ፣ ከተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ጀምሮ አሁን ላይ በሙያው ከወጣትነታቸው የሚልቅ አንቱታን ያገኙ የሙያ ልጆችን አፍርተዋል። ይህ የእርሳቸው ተግባርም አሁን ድረስ በአማተር ከያኒያን ላይ በሚገባ መሥራት የሚያስገኘውን ፍሬ ለማየት ሕያው ምስክር ነው።

ከግለሰቦች የግል እንቅስቃሴ በተጓዳኝ አማተር ክበባትና ማኅበራትም በዚህ ድርሻ እንደነበራቸው ዳዊት በጽሑፋቸው አውስተዋል። እንዲህም ሲሉ አስቀመጡት፤

‹‹በ1980ዎቹ ከቴአትር ቤቶች ባልተናነሰ መልኩ የጥበብ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ በርካታ አማተር ክበባት ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ በታላላቆቹ የመድረክ ሰዎች ወጋየሁ ንጋቱ፣ ሱራፌል ጋሻው፤ ገድሉ አሰግደው፤ ወዘተ ሥም አማተር ክበባት ተመሥርተው እንደነበረ አስታውሳለሁ። እነዚህ የቴአትር ቡድኖች በቴአትር ቤቶች መድረክ እየተከራዩ፣ የመድረክ ቴአትሮችን ገንዘብ በማስከፈል እስከማሳየት ደርሰው ነበር። በዚህን ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተመዝግበው በሕጋዊነት ይንቀሳቀሱ የነበሩት ቡድኖች ከ500 በላይ ነበሩ።››

ዳዊት አያይዘው አፍለኛውና ዩኒቲ ክበባትን በጽሑፋቸው አውስተዋል። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን ደራሲና ተዋናይ ሰለሞን ዓለሙን ጨምሮ የማስታወቂያ ባለሙያ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ደራሲና ተርጓሚ እንደዚሁም ተዋናይት አዜብ ወርቁ፣ ተዋናይት ድርብ ወርቅ ሰይፉ፣ ፍሬሕይወት መለሰና የመሳሰሉት በወቅቱ አፍለኛው ካፈራቸው የጥበብ ልጆች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

እነዚህ የዛሬ አንጋፎች በክበባት እንቅስቃሴ በነበሩበት ወቅት አዳራሽ ይከራዩ የነበሩት ከአንጋፋዎቹ ነው። በዛም ያቀርቧቸው የነበሩ ቴአትሮችና የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ዛሬ ድረስ የሚታወሱ ናቸው።

‹‹በዩኒቲ ኮሌጅ አማካኝነት የተመሰረተው የዩኒቲ የቴአትር ክበብም የጥበቡን ልጆች በማፍራት ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም። የመድረክ ድራማ ደራሲና ተዋናይ ቴዎድሮስ ለገሰ፤ አዘጋጅና ተዋናይ ተሻለ ወርቁ፣ ተዋናይ ደምሴ በየነ ወዘተ ግኝታቸው ከዚሁ ከዩኒቲ የቴአትር ክበብ ነው።›› ሲሉም የዩኒቲ የቴአትር ክበብን አውስተዋል።

ይኸው ክበብ በአገር ፍቅር ቴአትር ሳይቀር መድረክ በማግኘት ሥራውን ያቀርብ እንደነበርና፣ አንዳንድ ሥራዎችም ዓመታትን የቆዩ ብሎም ከአዲስ አበባ ተሻግረው በተለያዩ ክልል ከተሞች ጭምር ለዕይታ የቀረቡ መሆኑን በጽሑፋቸው አስታውሰዋል።

ከኪነጥበብ ዘርፉም ባሻገር አማተር የጋዜጠኝነት ክበባት እንደነበሩ ዳዊት በጽሑፋቸው አውስተዋል። ይህንንም በሚመለከት እንዲህ የሚል ሐሳብ አስፍረዋል፤

‹‹የአማተር ክበባቱ በቴአትር ብቻ የተወሰኑም አልነበሩም። በእነ ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ ሥም የተሰየሙ፣ ትፍላሜ የተሰኘ፣ ሰናይ የሚባል ወዘተ አማተር የጋዜጠኝነት ክበባት እንደነበሩና ለበርካታ ጋዜጠኞች መፈጠርም በር እንደከፈቱ አስታውሳለሁ።›› ብለዋል

እነዚህ ክበባት የንባብ ባህል እንዲዳብር፤ ሥነ-ጽሑፍን የሚሞካክሩ አዳጊ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እንዲበረታቱ፤ ኅብረተሰቡ ሥነጽሑፍን በሚመለከት ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ያደረጉትን አስተዋጽኦም ያደንቃሉ።

እርግጥም የሚደነቅ ነው። አሁን ላይ ሄድ መለስ ቢሉና በቀደመው መጠን ተጽእኖ እየፈጠሩ ያሉ ባይሆንም የሕጻናትና ወጣቶች ቴአትር፣ ሚዩዚክ ሜይዴይ እና መሰል ጥቂት ተቋማት የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉና አማተር ከያኒያንን ለማገዝ ብሎም ለማፍራት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

አሁን ላይ እነዚህ ክበባት አለመኖራቸው፣ አማተር ከያኒያን የሚስተናገዱበትና የሚታዩበት መድረክ አለመፈጠሩ ሙያተኛን እየቀነሰ፣ ዘርፉንም ደስ ያለው ሁሉ ደስ እንዳለው የሚገባበት ያደርገዋል።

አሁን ላይ ያለው ቴክኖሎጂ በአንድ ወገን በብዙ መልኩ ጥቅም ያለው ቢሆንም፣ ትክክለኛ የሆነ ሙያተኛና ተገቢ የሆነ ሥርዓት ካልተዘረጋ በቀር ዘርፉ ቸል እየተባለ ለማኅበረሰብ የሚሰጠው ዋጋም ሳይታይ እየቀረ መሄዱ አይቀርም። ትላንት ለዛሬ አንጋፎች የሚሆኑ መድረኮች ክፍት እንደነበሩ ሁሉ፣ ዛሬም ለነገ እየታሰበ ተረካቢ ሙያተኛ ትውልድን ለማፍራት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ይመከራል።

በሥነጽሑፉ ብቻም ሳይሆን በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ፣ በትወና፣ በስዕልና መሰል የጥበብ አውዶች ሁሉ ሙያተኞችን ብሎም በሚገባ የታሹ ባለሞያዎችን ለማግኘት ለአማተር ከያኒያን ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮም ትልልቅ የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ለአማተር ከያኒያን እድልና መድረክን በመስጠት፣ ለክበባትና ለእንቅስቃሴው ትንሣኤ የመፍጠር እድል አለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here