ሰብዓዊነትን የዘነጋ ብልጽግና!

1
2059

እድገት ለሰው ነው። አገር በሥልጣኔ ማማ ላይ ልትደርስ የምትችለውም፣ ብትደርስ ደግሞ የሚጠቀመውም ሰው ነው፤ ዜጎቿ ናቸው። ነገር ግን የሰዎች ነገር፣ ደኅንነትና ሰላማቸው ችላ ተብሎ የሚመጣ የትኛውም እድገትና ሥልጣኔ ለማንም የሚበጅ አይሆንም። ባለመረጋጋትና ሰላም በማጣት ውስጥም የሚመጣ ዘላቂ የሆነ እድገትም ሆነ ብልጽግና እንደማይኖር እሙን ነው።

ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት ተስፋ ተጥሎበት የኢትዮጵያን ትንሣኤ ያመጣል ተብሎ የተጠበቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና አመጣለሁ እያለ ቢሆንም በተግባር ግን በእለቱ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ይስተዋላል። ይህም ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች ውጪም በብዛት የሚስተዋል ሲሆን፣ በዚህ ዙሪያ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ ይመስል ምላሽ ሲሰጥም ሆነ ኃላፊነት ወስዶ የዜጎችን ደኅንነት ሲጠብቅ አልተስተዋለም። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ዘገባዎችን በማጣቀስና የቀደሙ ክስተቶችን በማውሳት ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት መከበር ወይም የሰብዓዊ መብቶች አለመሸርሸር የአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት መሠረት ስለመሆኑ፣ ከሰብዓዊ መብት ተማጓቾች እስከ ዓለም ዐቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማት በየጊዜው ለዓለም አገራት ያሳስባሉ። ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በርካታ አገራት የዜጎቻቸውን ሰብአዊ መብቶች በእጅጉ የሚጎዳና ለሁለንተናዊ ቀውስ የሚዳርግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያስተናገዱ ነው።

አሁን ላይ ከ167 በላይ የዓለም አገራት የዜጎቻቸውን ሰብዓዊ መብቶች ያላስከበሩ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። ከእነዚህ አገራት መካከል አንዳንዶቹ የዜጎቻቸው እንቅስቃሴ ደኅንነት ያልተጠበቀ የሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ አደገኛ የሚባል የደኅንነት ችግር ያለባቸው ናቸው።

የሰብዓዊ መብቶች መከበር የነገሮች ሁሉ መሠረት መሆኑን ዓለም ይስማማል። ይሁን እንጂ የመስማማቱን ያህል ዓለም ለሰብዓዊነት የሰጠው ትኩረት ከወሬ ያለፈ በተግባር የሚታይ አለመሆኑን ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያነሳሉ።

የዜጎቻቸውን ሰብዓዊ መብት ማስከበር ከተሳናቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች። በተለይ ራሱን የለውጥ መንግሥት ብሎ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ ወዲህ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው። ብልጽግና መራሹ መንግሥት ኢትዮጵያን እየመራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድታቀና እያደረግሁ ነው ቢልም፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር አለመቻሉን የሚያመላክቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት፣ በነጻነት የመንቀሳቀስና በቂ መሠረታዊ ፍላጎት ባልተሟላበት ሁኔታ፣ ‹ኢትዮጵያን አበለጽጋለሁ› የሚለውን የብልጽግና አስተዳደርን ሐሳብ ብዙዎች ‹ቅድሚያ የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት ይከበር› በሚል መከራከሪያ ሐሳብ ይሞግቱታል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት የዜጎች በሕይወት መብት ባልተከበረበት ሁኔታ፣ አንድ አገር ብልጽግና እውን ሊሆን እንደማይችል በማውሳት ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦችና ተቋማት እንደሚሉት ሰብዓዊ መብት መከበርና አለመከበር የአንድን አገር ብልጽግና ሁኔታ የሚያመላክት ነው። የሰብዓዊ መብት በእጅጉ የሚከበርባቸው አገሮች በልማትም ይሁን በዴሞክራሲ እድገታቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ስለማምጣታቸውም እንደ ምሳሌ ይነሳል።

በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው የዓለም ምሳሌ የሆኑት የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በእ1998 የዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሀምሳኛ ዓመት መታሰቢያ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ተከታዩን ተናገሩ፤ ‹‹ያለ ሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ምንም ዓይነት ሰላም እና ብልጽግና ሊጸና አይችልም››

ይህ የኮፊ አናን ንግግር እስካሁን ድረስ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሲነሳ በተለይ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦችና ተቋማት ዘንድ እንደ ማንቂያ ደወል ይታወሳል።

ሞት እና ብልጽግና

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት፣ ራሱን ‹የለውጥ መንግሥት› ብሎ በሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር አሰቃቂ የንጹሐን ዜጎች ጅምላ ግድያ አስተናግዳለች። የንጹሐን ዜጎች ግድያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ተጋልጠዋል።

በተለይ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሏል።

በተለይ በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች በዜጎች ላይ የግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ የማፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። በየጊዜው በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተባባሱ ቢመጡም፣ የዜጎችን ሞትና ማፈናቀል የሚያስቆም አካል አልተገኘም። በዚህም በየጊዜው የሰዎችን ሞት መስማት እንደ ተራ ነገር የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ከሥነ ልቦና ባለሙያዎች እስከ ሰብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች ሲገልጹ ነበር።

መንግሥት ንጹሐን ዜጎችን ከታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እንዲጠብቅ በየጊዜው ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይወተውታሉ። በየአካባቢው የታጣቂ ኃይሎች ሰለባ የሆኑ ዜጎችም፣ አስቀድመው መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በየጊዜው ጥሪ ያቀርባሉ። ‹‹ይሁን እንጂ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነቱ የሆነው መንግሥት፣ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻለም›› የሚሉ ትችቶች ከየአቅጣጫው ይቀርቡበታል። ሆኖም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ይሉትን ሆኖ ንጹሐን ዜጎች በየቀኑ እየተገደሉ ነው።

ይኸው “የለውጥ መንግሥት” ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች ያወጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ በተቃራኒው በለውጡ አስተዳደር የንጹሐን ዜጎች ሞት መቆሙ ቀርቶ በየአካባቢው ተባብሶ ቀጥሏል።

ዓለም ዐቀፍ የግጭት ሁኔታ እና የክስተት የመረጃ በመሰብሰብና በመተንተን የሚታወቀው “The Armed Conflict Location & Event Data Project (ACLED)” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ይህንኑ ሥራ በኢትዮጵያ እንድሠራ በፕሮጀክት ደረጃ ያቋቋመው፣ “The Ethiopia Peace Observatory (EPO)” የተባለው ተቋም ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ከመጋቢት 24/2010 እስከ መስከረም 30/2015 ባሉት ጊዜያት 3 ሺሕ 448 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ተከስተዋል።

ተቋሙ (EPO) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የሞት ሪፖርቶችን ከሚዲያዎች ዘገባ፣ ከመንግሥትና ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርት መረጃዎችን በማሰባሰብ ያደራጀው ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 24/2010 እስከ መስከረም 30/2015 ድረስ በተደራጁ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር 19 ሺሕ 889 መሆኑን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። በግጭቶች ሕይወታቸውን ካጡ ዜጎች መካከል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች የሞቱ ዜጎች ቁጥር 8 ሺሕ 771 መሆኑን ሪፖርቱ ያመላክታል።

ሰብዓዊ መብትና ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጸምባቸው ቀዳሚ አገራት መካከል የተሰለፈች አገር ስትሆን፣ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁኔታ “ዘግናኝ እና አሳሳቢ” ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጎ) መግለጹ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተደጋጋሚ በሚያወጣው መግለጫ መንግሥት የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ይገልጻል።

እንደ ኢሰመኮ እና ኢሰመጉ ያሉ የአገር ውስጥ ሰብዓዊ መብት ተቋማት በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች በየጊዜው የሚፈጸሙ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየመረመሩ በሚያቀርቡት ሪፖርት መሠረት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግኝቶች ታይተዋል። ተቋማቱ በሚያደርጓቸው ምርመራዎች መሠረት ለመንግሥትና ለባለድርሻ አካላት የመፍትሔ ሐሳቦችን ጨምረው የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ይወተውታሉ።

ይሁን አንጂ አሁንም የንጹሐን ዜጎች በየቦታው በታጣቁ ኃይሎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ግድያዎች እየተፈጸሙ መሆኑን የተቋማቱ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

የወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ዓመታዊ የአገራት የሰብዓዊ ነጻነት ጠቋሚ ደረጃ የ2021 የሰብዓዊ ነጻነት ደረጃ ጠቋሚ ኢንዴክስ እንደሚያመላክተው፣ ኢትዮጵያ ከ165 አገራት በሰብዓዊ ነጻነት መለኪያ ሪፖርት ላይ 132ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እንደ ጠቋሚ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በእጅጉ ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።

ኢትዮጵያ ከ165 አገራት በሰብዓዊ ነጻነት ሁኔታ 132 ደረጃ ላይ የተቀመጠች፣ በሕግ የበላይነት፣ በደኅንነት፣ በእንቅስቀሴ፣ በሐይማኖት፣ በማኅበራት ነጻነት፣ በማንነት፣ በሕግ ሥርዓት፣ ሐሳብን በነጻነት በመግለጽና በመሰል መለኪያዎች ተመዝና ነው።

በቅርቡ በአዲስ ማለዳ የአንደበት አምድ እንግዳ ሆነው ቃለ ምልልስ የሰጡት ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰፊ ናቸው፣ የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በጣም አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ፣ በታጠቁ ቡድኖችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው መድረሱንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ንጹሐን መሞታቸው፣ በሕይወት የመኖር መብት ጥሰት ስለመሆኑ ኮሚሽነሩ ይገልጻሉ።

‹‹በኦሮሚያ ክልል ሰዎች የሚገደሉት በታጠቀ ቡድን ነው›› የሚሉት ኮሚሽነሩ፣ መንግሥት በመርህ ደረጃ ያንን የታጠቀ ቡድን ተቆጣጥሮ የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ይገልጻሉ። መንግሥት የታጠቁ ቡድኖችን በሕግ ተጠያቂ ካለደረገ በሕይወት የመኖር መብት እየተከበረ አይደለም የሚሉት ኮሚሽነሩ፣ በሕይወት የመኖር መብት ከተጣሰ ሌሎች መብቶች መጣሳቸው የማይቀር ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጎ) የታጠቁ ቡድኖች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ መሆናቸውን ተከትሎ ጉባኤው እንደሚያሳስበው ከዚህ በፊት በሰጣቸው መግለጫዎች ላይ የጠቆመ ሲሆን፣ እንደ እነዚህ ያሉ ተመሳሳይ ጥቃቶች አሁንም ቀጥለዋል ነው ያለው።

በተደጋጋሚ በታጣቂ ኃይሎች በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳሰቢ መሆኑንም ኢሰመጎ መግለጹ የሚታወስ ነው።

መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በየጊዜው የሚያሳስበው ኢሰመጉ በዓለም ዐቀፍ፣ በአኅጉር ዐቀፍ እና በአገር ዐቀፍ ሕጎች መሠረት መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት በማስከበር ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ፣ በታጣቂ ቡድኖች እየተፈጸሙ ያሉ እገታዎችን እንዲያስቆም፣ በተመሳሳይ ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲያቀርብ ቢወተውትም እስካሁን ተጨባጭ ለውጥ አልታየም።

የአንድ አገር ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በነጻነት እንዲኖሩ የማስቻል ኃላፊነት ካለባቸው ባለድርሻ አካላት መካከል ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስደው መንግሥት ነው። አብዲ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ይሁን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ጣሰ የሚባለው ብዙውን ጊዜ መንግሥትን ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት መንግሥት የዜጎቹን ሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታዎች ስላለበት ነው ይላሉ።

መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታም አለበት የሚሉት አብዲ፣ ማስከበር ሲባል ሦስተኛ ወገን የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጥሱ ማስከበር ማለት ነው ይላሉ። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም ማንም ቢያጠፋ ተጠያቂ የሚሆነው መንግሥት መሆኑን የሚገልጹት አብዲ፣ መንግሥት ራሱ ያጥፋ ወይም ሌላ ቡድን ያጥፋ ተጠያቂ የሚሆነው መንግሥት ራሱ ነው ይላሉ።

‹‹በሕይወት የመኖር መብትን ካየን፣ አንደኛ በሕይወት የመኖር መብት የሚጣሰው በግድያ ነው። ኹለት በርሃብ ሊጠፋ ይችላል። ሦስተኛ በጤና ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ ለሁሉም መፍትሔ የመፈለጉ ኃላፊነት ያለው መንግሥት ጋር ነው›› ይላሉ።

መንግሥት በታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን የማስቆም ኃላፊነቱን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አለመሆኑን በመጥቀስ ኢሰመጉ መውቀሱ የሚታወስ ነው። ተቋሙ መንግሥት ኃላፊነቱን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አይደለም ሲል የወቀሰው፣ በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች መቀጠላቸው አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

ከዓለም ዐቀፍ፣ አኅጉር ዐቀፍ እና አገር ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎች ላይ እንደተደነገገው፣ መንግሥት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር፣ ማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት አለበት የሚለው ኢሰመጎ፣ ይህ ሳይሆን ሲቀር እና በመንግሥት ቸልተኝነት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ሲቀሩ ዋነኛ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው መንግሥት ነው ባይ ነው።

ብልጽግና መራሹ መንግሥት በየጊዜው “ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን” ቢልም፣ ኢትዮጵያ ያጋጠማት የሰላም እጦት ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ባልቻለበት ሁኔታ፣ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ መጥራቱን የሚነቅፉ አካላት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል።

ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አስተዳደር፣ ኢትዮጵያን የሚያጸና ለውጥ እያመጣሁ ነው ይበል እንጂ፣ ለውጡ በአግባቡ ባለመመራቱ ችግሩ “ከድጥ ወደ ማጡ” መሆኑን ብዙዎች ሲገልጹ ይደመጣሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ለውጥ እያመጣሁ ነው ከሚልባቸው ጉዳዮች መካከል ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አንዱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና የፈጠረ በየወሩ እየናረ የቀጠለ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስተናገደች ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ ከሚጠራው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ከሚለው ለውጥ ጋር የሚጣጣም አይደለም የሚሉ ሐሳቦች ከፖለቲከኞች እስከ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል። ለዚህም ከሚነሱ ምክንያቶች መንግሥት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር አልቻለም የሚለው ጉዳይ አንዱና ዋናው ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

አስተያየት

  1. ጥሩ ትዘግባላቹ።ነገር ግን በሀገራችን አብዛኛውን ጊዜ የሚዘገቡት መጥፎ መጥፎ ድርጊቶችን ስለሆነ ሰው ደግሞ የሚሰማውንና የሚያየውን የመሆን እድሉ ሰፊ ሰለሆነ ለሰው ምሳሌ የሚሆኑ ጉዳዮችን አቅርቡ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here