1- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እያደረጉት በሚገኘው ውይይት ላይ “እንዳንሳተፍ ተደርገናል” በሚል የአምቦ ከተማ ወጣቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።ውይይቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በአምቦ ዋና አውራ ጎዳና ላይ የተሰባሰቡ ወጣቶች ተቃውሟቸውን በግልጽ ሲያሰሙ ተደምጠዋል። “ቄሮዎች በስብሰባው ላይ መሳተፍ ነበረባቸው” የሚል ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የነበሩት ወጣቶች “የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየው ቄሮ እንጂ አሁን በስብሰባ ላይ የተሳተፈው አካል አይደለም” ማለታቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል።(ዶይቼ ቬለ)
……………………………………………………………..
2–ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረውና ልናከብረው የሚገባ ቀይ መስመር ተጥሷል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።ፕሬዚዳንቷ በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አደጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን ያሉ ሲሆን የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………..
3-አዲሱ የስደተኞች ሕግ ለስደተኞች ዋስትናን የሚሠጥ እና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲበለጽጉ የሚረዳ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ተናግረዋል።በተቀባይ አገራት ስደተኞች በካምፕ ውስጥ ብቻ ከታጠረ ሕይወት ወጥተው ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን እነሱን በሚያሳትፉ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲካተቱ እና በዘላቂነት ሕይወታቸው መቀየር እንዲችሉ መታሰቡን ገልጸዋል።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………..
4-ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ፌስቡክን ለመክሰስ እያሰበ መሆኑን ተናገረ።በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜዉ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች የከፋ ጉዳት እንዲያደርሱ የማህበራዊ የትስስር ገጾች በተለይም ፌስቡክ ትልቅ ሚና እነዳለዉ ገልጿል።የኢትዮጵያ መንግስት ፌስቡክ እያደረሰ ላለው ጥፋት የማይከስ ከሆነ እኔ መክሰሴ አይቀርም ብሏል።በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ፌስቡክን ለመጠየቅ በቂ ነው በማለት ተናግሯል።(ፋና ብሮድካሰቲንግ)
……………………………………………………………..
5-በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው የቀረቡ ምሁራንና ግለሰቦች የሚያሰራቸው አካል እንዳላገኙ ተናገሩ።የእምቦጭ አረም ለማጥፋት በሚሊዮን ብሮች ወጪ ወጥቶባቸው የተገዙ ማሽኖችም ያለ ሥራ እንዲቆሙ መደረጋቸዉን ተናግረዋል።(ቪኦኤ)
……………………………………………………………..
6-የኢትዮጵያ ከተሞች በየዓመቱ የ5 ነጥብ 4 በመቶ የሕዝብ ቁጥር እድገት እያስመዘገቡ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገልጸዋል።ለሕዝብ ቁጥር አድገት እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰዉ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የሰዎች ፍልሰት መሆኑ አስታዉቀዋል።(107.8 ኤፍ ኤም)
……………………………………………………………..
7-ትዊተር በመላው ዓለም የፖለቲካ ይዘት ያላችው ማስታወቂያዎችን ሊያግድ መሆኑን የገለፀ ሲሆን, ማስታወቂያዎቹ ከሚፈለገው ቦታ መድረስ እና ተደራሽ መሆን ያለባቸው በራሳቸው እንጂ በገንዘብ ተገፍተው መሆን እንደሌለበት ኩባንያው አስታውቋል። “ለንግድ ተቋማት በበይነ መረብ ማስተዋወቅ አቻ የሌለው የማስታወቂያ ስልት ቢሆንም ፖለቲካ ላይ ሲመጣ ግን የራሱ አደጋዎች አሉት” ሲሉ የተናገሩት የድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ጃክ ዶርሴይ ናቸው።በቅርቡ ተቀናቃኙ ፌስቡክም የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን እንደማያግድ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።(ዋልታ)
……………………………………………………………..
8- በመጭው ቅዳሜ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚካሄደውን የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ “ወንፈል” የተባለ የተራድኦ ድርጅት ያዘጋጀው ሲሆን ሩጫው በአማራ ክልል ጎንደርና ባሕር ዳር ለሚያስገነባቸው የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህር ቤቶች ገቢ ለማሰባሰብ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የድርጅቱ ገንዘብ ያዥ ዶክተር ይንገሥ ይግዛው ተናግረዋል።በገቢ ማስገኛ መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ቢልልኝ መቆያ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ። በገቢ ማሰባሰቢያዉ ላይ 100 ሺሕ ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)



