ከባድ ችግር ያለበት ቀላል ባቡር

0
1546

መግቢያ

የትራንስፖርት ነገር ማኅበረሰቡን ሲያማርር ይስተዋላል። የመንገድ መዘጋጋት፤ ምሽት ላይ የሚደረግ ከእጥፍ በላይ የታሪፍ ጭማሪ፤ በሰልፍና በትራንስፖርት ላይ የሚጠፋ ጊዜ እና ሌሎች መሰል ችግሮች ለተጓጓዡ ቀንደኛ ችግር መሆናቸውን ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ከከተማ ውጭ ባሉ ቦታዎች ያሉ ተጓዦች በበኩላቸው፤ ሹፌሮች እንዳሻቸው ከእጥፍም በላይ የሚጨምሩት ታሪፍ፤ በጦርነቱ ምክንያት የተሽከርካሪዎች ግዳጅ መውጣትን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት አለማግኘት፤ የጸጥታ ችግር ባለባቸው በአራቱም አቅጣጫዎች በታጣቂዎች የሚደረግ እገታና የመንገድ መዘጋት ዋነኛ ችግራቸው መሆኑን በተለይም በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ማስረዳት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

ከዚህም ባሻገር በየወቅቱ በሚፈጠር ድንገተኛ አደጋ በሰዎች፤ በንብረት እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ይስተዋላል። በተለይም በርካታ ሕዝብ በሚራወጥባት በአዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርት ምክንያት የሚከሰተው የጉዳት መጠን ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ ይገኛል።

ኹኔታውን በተናጠል ብንመለከት ከሌሎች አካባቢዎች በይበልጥ በከተማ አካባቢ ያለው አደጋ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ ይገኛል። በ2014 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ የሞቱ ሲሆን፤ ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ22 ሰዎች ብልጫ እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በተለይም በከተማ አካባቢዎች የትራንስፖርት ችግር የሚስተዋለው በመኪና ብቻ ሳይሆን በቀላል የባቡር ትራንስፖርትም ጭምር መሆኑ እየተነገረ ነው። በመሆኑም፤ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ አዲስ ማለዳ በቀላል ባቡር ትራንስፖርት ላይ የሚስተዋለውን ኹኔታ ለመመልከት ሞክራለች።

በ2014 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት የሚሰጡት ቀላል ባቡሮች በቁጥር አናሳ መሆን በባቡር ተጠቃሚዎች መጉላላትን አስከትሏል የሚል ቅሬታ ከማኅበረሰቡ በኩል እየተሰነዘረ ይገኛል። የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ 41 ባቡሮች ቢኖሩም ሁሉም አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውም እየተነገረ ነው።

የባቡር ታሪክ

የባቡር ትራንስፖርት ከትራንስፖርት አገልግሎቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል። የባቡር ትራንስፖርት የተጀመረው በ1820 በእንግሊዝ አገር መሆኑ ይነገራል። ጅማሮው በእንግሊዝ አገር ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያም በበኩሏ በባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚነት ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ እንዳላት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ በባቡር ትራንስፖርት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ በኋላም በ2008 የቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል።

የቀላል ባቡር አገልግሎት መጀመሩ የትራንስፖርቱን ችግር ከመቅረፉ ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገትና ለማኅበራዊ ለውጥም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በወቅቱ ተስፋ ተጥሎ ሲገለጽ ነበር።

ይሁን እንጂ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ከዓመት ወደ ዓመት መስተጓጎል ሲገጥመው ይስተዋላል። በ2014 በጀት ዓመት ከመስከረም እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ እንኳን ከአጠቃላይ 41 ባቡሮች መካከል አገልግሎት ሲሰጡ የነበረው 24 ብቻ ሲሆኑ፤ ይህም የሚያመላክተው ቀሪዎቹ  17 ባቡሮች ሥራ ማቆማቸውን ነው።

ቁጥራዊ ማሳያ

ከ2008 እስከ 2014 ባለው ወቅት አገልግሎት የማይሰጡ/የቆሙ ባቡሮች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንደመጣ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኙ ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

በ2008 በአዲስ አበባ ከነበሩት አጠቃላይ 41 ባቡሮች መካከል 34ቱ አገልግሎት ሲሰጡ ቢቆዩም፤ ሰባት ቀሪ ባቡሮች ቆመው ነበር። ከኹለት ዓመት ቆይታ በኋላ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች ቁጥር ከ34 ወደ 32 ዝቅ ያለ ሲሆን፤ የቆሙ ባቡሮች ብዛት ደግሞ ከሰባት ወደ ዘጠኝ ከፍ ብሎ ነበር።

በወቅቱ ዘጠኝ ባቡሮች ለመቆም የተገደዱት በመለዋወጫ እቃ እጥረትና በባቡር ‹ተሽከርካሪ ጎማ› ብልሽት መሆኑ ተመላክቷል።

በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት ማለትም በ2011 እና 2012 ከጠቅላላ 41 ባቡሮች 33 አገልግሎት ሲሰጡ ቢቆዩም፤ በእያንዳንዱ ዓመት ግን በአላቂ የመለዋወጫ እቃ እጥረትና በተሽከርካሪ ጎማ ብልሽት እንዲሁም የጥገና መሣሪያና ክህሎት አለመኖር ጋር በተያያዘ ስምንት ባቡሮች አገልግሎት መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ምንም እንኳ ከኹለቱ ዓመታት (2011 እና 2012) በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የቆሙ ባቡሮች ብዛት በአንድ ቢቀንስም በ2008 አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩ 34 ባቡሮችም አንድ ቀንሶ ወደ 33 ዝቅ ለማለት ተገዶ ቆይቷል።

ይህ በአንዲህ እያለ በ2013 እና 2014 ደግሞ አገልግሎት የማይሰጡ ባቡሮች ቁጥራቸው ይበልጥ ጨምሮ ተስተውሏል። የተቋሙ መረጃ እንደሚያሳየው በ2011/12 (በእያንዳንዱ) በጀት ዓመት 33 ባቡሮች አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን፤ በ2013 በጀት ዓመት ግን ከ33 ወደ 29 ዝቅ በማለቱ የቆሙ ባቡሮች ብዛት ከስምንት ወደ 12 ከፍ ብሏል።

ይህ በአንዲህ እያለ በ2014 በጀት ዓመት አገልግሎት የሚሰጡ ቀላል ባቡሮች ብዛት ከ29 ወደ 24 ዝቅ በማለቱ የቆሙ ባቡሮች ቁጥር ደግሞ በአንድ ዓመት ብቻ ከ12 ወደ 17 ከፍ ብሏል።

በመሆኑም በሌሎች ተሽከርካሪዎች ከሚስተዋለው ችግር በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡት ቀላል ባቡሮች አነስተኛ መሆን በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ መጉላላትን በማስከተሉ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ችግር እንደሚያመጣ እየተነገረ ነው።

የሚስተዋለው ችግር በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫና በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት አማካሪና እና የፖለቲካ ተንታኞች መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ሐሳቦች አጋርተዋል። በዚህም የምጣኔ ሀብት አማካሪው ያሬድ ገብረመስቀል፣ በትራንስፖርት መዘግየት የሚጠፋው ጊዜ በኢኮኖሚ እድገት ማሽቆልቆልን እንደሚያስከትል ማጤን ያሻል ሲሉ ጠቅሰዋል።

አክለውም አብዛኛው ሰው ግን ትራንስፖርት ውስጥ ሆኖ የሚያጠፋው ጊዜ በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን በአንክሮ እየተመለከተው አይደለም ነው ያሉት። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በሚፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ተሳፋሪዎችም ሆኑ ሹፌሮች ጊዜያቸውን በትራንስፖርት ጉዞ ላይ እያጠፉ ስለመሆናቸው ከዚህ በፊትም ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሕዝብ ማመላለሻ የከተማ አውቶብሶችን ጨምሮ ሌሎች ተሽከርካሪዎች በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ለጊዜ ብክነት የሚዳረጉ ቢሆንም፤ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ግን መንገዱ ራሱን የቻለ በመሆኑ ለትራንስፖርት ተመራጭ መሆኑን ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

አሁን አሁን ግን ባቡሮች በፍጥነት ስለማይገኙና ቁጥራቸውም አነስተኛ በመሆኑ በሌሎች የትራንስፖርት ዓይነቶች (በሕዝብ ማመላለሻ የከተማ አውቶብሶች፤ ታክሲዎች…ወዘተ) ያለው ችግር በባቡር ትራንስፖርትም እየተስተዋለ ነው የሚል ቅሬታም ሳያነሱ አላለፉም።

ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ዐስር በማይሞሉ ደቂቃዎች ውስጥ በየመሳፈሪያ ጣቢያዎች የመድረስ ፍጥነት እንዳለው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባደረገው ተደጋጋሚ ምልከታ ማረጋገጡን ሲገልጽ መቆየቱ አይዘነጋም።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውራ ባደረገችው ምልከታ አንድ ባቡር ከመሳፈሪያ ጣቢያ ለመድረስ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ እንደሚፈጅበት ታዝባለች። በመስቀል አደባባይ እና በሌሎች ቦታዎች በተዘዋወረችበት ወቅትም ያነጋገረቻቸው ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ ባቡር እስከ 20 ደቂቃ ከመዘግየቱ ባሻገር ቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ በተደጋጋሚ የመመላለስ እድሉም ጠባብ ነው ብለዋል። ጭራሽ ባቡር የማይመጣበት ቀን ስለመኖሩም ቅሬታ አቅራቢ ተሳፋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

የምጣኔ ሀብት አማካሪው በበኩላቸው፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ነው ባይ ናቸው። ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ ትራንስፖርት ዋናው ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ እየተስተዋለ ያለው በተቃራኒው ነው አሉ።

እንደ ያሬድ ገለጻ ከሆነ፤ ባቡር ከመሳፈሪያ ጣቢያ በስድስት ደቂቃ መድረሱ መልካም ሆኖ ሳለ፤ አሁን ላይ እስከ 20 ደቂቃ ቆይቶ መድረሱ ግን የሚያሳየው ከሦስት ጊዜ በላይ በሚመላለስበት ወቅት አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው። ያሉት ባቡሮች እንኳን ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት የማይሰጡ ከሆነ፤ በትራንስፖርት መጉላላት ብቻ በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ማሽቆልቅል ቀላል አይደለም።

በመሆኑም ችግሩን እንደ ትልቅ ጉዳይ ተመልክቶ ከዚህ የባሰ ሳይረፍድ መፍትሄ መፈለግ የተቋሙ ኃላፊነት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በባቡር ትራንስፖርት ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ ምክንያት የስፔር ፓርት መለዋወጫ እጥረት መሆኑን ለተለያዩ ሚዲያዎች ሲገልጽ ተስተውሏል። የምጣኔ ሀብት አማካሪው ያሬድ በዚሁ ጉዳይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ፣ ሲጀመር ተቋሙ ወደ ሥራ ሲገባ የመለዋወጫ ችግር እንደሚገጥመው ተገንዝቦ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት መፍትሄ ማበጀት ነበረበት ይላሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ ጌታሁን ይልማ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ኹኔታ እልባት አለማግኘቱ ትራንስፖርት ላይ ከዚህ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል እሙን ነው ባይ ናቸው። ወደሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተዘረጋ ያለውና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረው የአዋሽ – ሀራ – ወልድያ የባቡር መስመር በየጊዜው የኤሌክትሪክ ገመድ ስርቆት እንደሚጋረጥበት ያነሱት ተንታኙ፣ በተለይም የጦርነት ቀጠና የነበሩ ስፍራዎች ላይ ስርቆቱ ተባብሶ መክረሙን አንስተዋል።

ጌታሁን አክለውም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በከተማ የቀላል ባቡር መስመር ላይ በየወቅቱ የሚከሰተው አደጋ፣ ማለትም የባቡር ከሌሎች ተሽከርካሪዎች ጋር የመጋጨት አደጋ ትራንስፖርት ላይ ‹ከደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ዓይነት ችግር ነው ይላሉ። በመሆኑም ባለድርሻ አካላት ያለውን ክፍተት የመድፈን ግዴታ አለባቸው ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በየጊዜው በሚገጥመው ችግርና አደጋ፣ ከዚህ በፊት 13 ሚሊዮን የሚገመት ንብረት ላይ ኪሳራ እንደደረሰበትና የመለዋወጫ እቃ እጥረት ለባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ፈተና ስለመሆኑ ይነገራል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here