‹ኤም ፔሳ› ኢትዮጵያ እንዲገባ ፈቃድ ማግኘቱ ቴሌብርን እንደማያሰጋ ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ

0
1211

በሳፋሪኮም የሚተዳደረው ‹ኤም ፔሳ› የሚሰኘው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ሰጪ በኢትዮጵያ  አገልግሎት እንዲሰጥ መፈቀዱ ቴሌብርን እንደማያሰጋ ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

የኢትዮ ቴሌኮም የማርኬቲንግ ሥራ አስፈጻሚ ሰዒድ አራጋው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ አገልግሎት ከጀመረ 17 ወራትን ያስቆጠረው ቴሌብር አገልግሎቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለና እያዘመነ ሲሆን፣ ኤም ፔሳ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገባ መፈቀዱ ለቴሌብር ስጋት አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ማድረጉን ተከትሎ፣ በጨረታ አሸንፎ የኢትዮጵያን የቴሌኮም አገልግሎት  የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በኬንያ ስኬታማ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሆነውን  ኤም ፔሳ በኢትዮጵያ ለማስጀመር ፈቃድ ጠይቆ መንግሥት ፈቃድ ሰጥቶታል። ሳፋሪኮም በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በኬንያና ሌሎች አገሮች ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ስኬቱን በኢትዮጵያ ለመድገም እንደሚሠራም አስታውቋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ በኢትዮጵያ እንዲሠራ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ፣ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ የወራት እድሜ ላስቆጠረው ቴሌብር ፋይናንስ ብርቱ ተገዳዳሪ እንደሚሆን የዘርፉ ምሁራን ሲገልጹ ተደምጠዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ኤም ፔሳ በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የረዥም ጊዜ አገልግሎት ልምድ ያካበተ መሆኑን፣ የወራት እድሜ ላለው ቴሌ ብር ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በልምድም ይሁን በቴክኖሎጂ የተሻለ አቅም እንዳለው በማንሳት ነው።

ምንም እንኳን ኤም ፔሳ የረዥም ዓመት ልምድ ቢኖረውም ቴሌብርም በዘርፉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቂ ልምድ ማግኘቱን የጠቀሱት ሰዒድ፣ ቴሌብር ተመራጭ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት አቅራቢነቱ ይቀጥላል ብለዋል።

ኤም ፔሳ ከ15 ዓመታት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረ የገንዘብ ልውውጥ አገልግሎት ሰጪ ሲሆን፤ በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በሌሎች 6 አገራት አገልግሎቱን በማቅረብ ላይ ይገኛል። ከዚህ በፊትም በሕንድ፣ ሮማኒያና አልባኒያ ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ተፈላጊነት በማጣቱ ምክንያት አገልግሎቱን ማቋረጡን መረጃዎች ያሳያሉ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ የአገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈቀደ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚያው ላይም የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ/ር) ተገኝተው፣ ‹‹የኬንያ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ይህን እንዳስፈጽም የቤት ሥራ ሰጥቶኝ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን አገልግሎት በመፍቀዱ አመሰግናለሁ።›› ማለታቸውም ይታወሳል።

ቴሌብር እስካሁን ድረስ ከ85 ሺሕ በላይ ወኪሎችን፣ እንዲሁም 24.8 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፣ እነዚሁ ደንበኞችም 97.4 ቢሊዮን ብር አንቀሳቅሰዋል ያሉት ሰዒድ፣ ይሄ ቁጥርም እየጨመረ የሚሄድ መሆኑና ኤም ፔሳ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም እንደ አዲስ ደንበኞችን ማፍራት የሚጀምር ስለሚሆን ቴሌብርን እንደማያሰጋው ተናግረዋል።

አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ኹለት ወራት ባስቆጠሩት ቴሌ ብር ፋይናንስ ባቀረበባቸው፣ ቴሌብር መላ እንዲሁም ቴሌብር እንደኪሴ የብድር አገልግሎቶችም 256 ሺሕ ደንበኞች የ300 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት አግኝተዋል ተብሏል። ቴሌብር ሳንዱቅ ደግሞ 96 ሺሕ ደንበኞች አፍርቶ፣ ደንበኞች 304 ሚሊዮን ብር መቆጠብ እንደቻሉ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

ከአርባ የተለያዩ የውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ በተፈጸሙ የገንዘብ ልውውጦችም 1.3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ምንዛሬ ማግኘት እንደተቻለ ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በንግድ ልውውጥ በኩልም ቴሌብር ከ24 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ጋር አብሮ የሚሠራ ሲሆን፣ የንግድ ልውውጡን ከማዘመን አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝም ሰዒድ ገልጸዋል።

በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች 23ኛ ደረጃን የያዘው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 99 በመቶውን መሸፈን መቻሉ የቴሌብር ተደራሽነትን ለማስፋት ያግዛል ያሉት ሰዒድ፣ በ17 ወራት ያለው አፈጻጸም የወደፊት ተስፋው ብሩህ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here