በሕገወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውር የተጠረጠሩ 665 ሰዎች ለወንጀል ምርመራ መተላለፋቸው ተገለጸ

0
1086

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን 665 ተጠርጣሪዎች ለምርመራ አሳልፎ መስጠቱ ተገለጸ።

አገልግሎቱ ከሕገ ወጥ የውጭ አገራት ገንዝብ ማስተላለፍ ወንጀል ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 665 የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ስለማገዱ ባሳለፍነው መስከረም 30/2015 አሳውቆ ነበር።

ይህን ተከትሎም በገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ፣ ኹሉንም ተጠርጣሪዎቹን ለሕግ ምርመራ አሳልፎ መስጠቱ ተገልጿል።

በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ተሳትፎ አላቸው ተብሎ የባንክ ሒሳባቸው የተዘጋባቸው 665 ተጠርጣሪዎች ለወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ ዮናስ ማሞ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ለምርመራ ተላልፈው የተሰጡት አካውንታቸው እንዲታገድ ከተወሰነበት መስከረም 30/2015 በኋላ መሆኑን ዮናስ ተናግረዋል። በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች አካውንት ተዘግቶ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ለወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን የጠቀሱት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊው፤ ምርመራ እንዲያደርግ ተጠርጣሪዎቹ ተላልፈው የተሰጡበት ተቋምም እንደ ወንጀሉ የሚለያይ ነው ብለዋል። ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለፌዴራል ፖሊስ የተላለፉ ስለመኖራቸው ተገልጿል።

በሕገ ወጥ መንገድ የሚገኝን ገንዘብ ሕጋዊ የማስመሰል ድርጊት ከወንጀልነቱ ባሻገር ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመደገፍ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፤ የባንክ ሒሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ ከተደረጉት በተጨማሪም የማጣራት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉም ተጠቅሷል።

ዮናስ አክለውም፣ በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ተሳትፈዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ሌሎች አካላት መኖራቸውን ለማወቅ አገልግሎቱ እየሠራ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ መስከረም 27/2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሕገ ወጥ የሐዋላ ሥራ የተሰማሩ 391 የሚሆኑ ሰዎችን ስለመዝጋቱና በሐዋላ አስተላላፊዎቹ ላይ ክስ ለመመሥረት የግለሰቦችን ሥም ዝርዝር ለፍትሕ ሚኒስቴር አሳልፎ መሰጠቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረት በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በኩል 665 እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ በኩል በተደረገ ቁጥጥር 391 በአጠቃላይ 1 ሺሕ 56 በሕገ ወጥ የገንዝብ ዝውውር ተጠርጥረው የባንክ ሒሳባቸው እንደተዘጋና ወደ ሕግ ተላልፈው እንደተሰጡ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ፣ በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር የተሰማሩ ሰዎችን ለሚጠቁሙ አካላት ወሮታ እንደሚሰጥ ሲገልጽ የሰነበተ ሲሆን፤ ስለ ወሮታው መመሪያም ሰሞኑን ማብራሪያ ሰጥቷል።

በዚህም በውጭ አገር ገንዘብ ዝውወርና በባንክ ከተፈቀደው ገንዘብ በላይ ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን የጠቆመ 15 በመቶ፤ ሕገ ወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺሕ ብር ወሮታ እንደሚከፍል አስታውቋል።

በተያያዘም ተቋማት በቀን ከ200 ሺሕ ብር እንዲሁም ግለሰቦች ደግሞ በቀን 100 ሺሕ ብር በላይ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ነው ብሔራዊ ባንክ መግለጫ የሰጠው።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here