የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ተጨማሪ በጀት ሊጠይቅ እንደሚችል አስታውቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ በሕዝበ ውሳኔው ዙሪያ ጥቅምት 10/2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቦርዱ ወቅታዊ የሆኑና በመረጃ የተደገፉ የዋጋ ጥናቶችን አካሂዶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 541.3 ሚሊዮን ብር መጠየቁን አስታውሰዋል።
ቦርዱ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ በጀት የጠየቀ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ አንዳንድ ወጪዎች ተጋነዋል በማለት 410.1 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደፈቀደ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። ቦርዱ ከጠየቀው በጀት 131.2 ሚሊዮን ብር ተቀንሶበታል።
የተፈቀደላቸውን በጀት በቁጠባ በመጠቀም ለማብቃቃት እንደሚሞክሩ የገለጹት ብርቱካን፣ ገንዘቡ ካነሳቸው ምክር ቤቱን ተጨማሪ በጀት መጠየቃቸው እንደማይቀር ተናግረዋል። ምርጫዎችን በአግባቡ ለማስፈጸም ገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ብርቱካን፣ አግባብነት የሌለው ወጪ አልጠየቅንም ብለዋል። በተፈቀደው ገንዘብም መሥራት የሚቻለውን ያህል እንደሚሠሩ ተናግረው፣ ገንዘብ የሚያንሳቸው ከሆነ ምክር ቤቱን የበጀት ጭማሪ ከመጠየቅ ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
ከ3.1 ሚሊዮን በላይ መራጮች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ሕዝበ ውሳኔ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች የሚደረግ ሲሆን፣ ስድስቱ ዞኖችና አምስቱ ልዩ ወረዳዎችን በአንድ ክልል ለማደራጀት የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ነው።
ይህን ሕዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም 18 ሺሕ 750 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች እንደሚያስፈልጉ በመግለጫው ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ 2013 በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የአስፈጻሚነት ሚና የተወጡ 9 ሺሕ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም ፍቃደኛ ሆነዋል። ቀሪ የሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን ለማሟላት ምልመላ እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጹት ብርቱካን፣ የሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ እንዳሉም ተናግረዋል።
ቅሬታ የሚቀርብባቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችንም ጉዳያቸውን በማጣራት በማስረጃ ላይ የተደገፈ እርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹት ብርቱካን፣ በቅርቡ ይፋ በሚደረግ የኦንላይን አማራጭ አማካኝነት ማንኛውም የሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚቀበሉና እንደሚያጣሩ ተናግረዋል።
ጥር 29/2015 እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ በተያዘለት ሕዝበ ውሳኔ፣ ከ3.1 ሚሊዮን እንደሚበልጡ የተገመቱትን መራጮች ከታህሳስ 06 እስከ 25/2015 ባሉት ቀናት ውስጥ ለመመዝገብ የታቀደ ሲሆን፣ 3 ሺሕ 756 የምርጫ ጣቢያዎችም ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል
የሕዝበ ውሳኔ ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት ሕዝበ ውሳኔ ከሚደረግባቸው አካባቢ የሥራ ኃላፊዎች ፈጣን ምላሽ እንዳላገኙ የተናገሩት ብርቱካን፣ ምርጫውን ለማስፈጸም የሚደረጉ ሥራዎች ላይ መጓተቶችን እየፈጠረ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ ከሥራ ኃላፊዎቹ ጋር እንደተነጋገሩና ችግሮችን ለመፍታትም እንደተስማሙ ገልጸዋል
ሕዝበ ውሳኔው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናወን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ብርቱካን፣ ከአገር ውስጥ የሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ ታዛቢዎችም እንደሚታዘቡት ገልጸዋል። ከሌሎች አገራት የተውጣጡ ታዛቢዎችን እንዲታዘቡ መጋበዝ የመንግሥት ድርሻ እንደሆነ ገልጸው፣ እስካሁን ድረስ ሕዝበ ውሳኔውን ይታዘባል የተባለ የውጭ ታዛቢ አለመኖሩንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ በፊት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኹለት የክልልነት ሕዝበ ውሳኔዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም እስካሁን ድረስ ይህን ሕዝበ ውሳኔ ጨምሮ ኹለት የክልልነት ሕዝበ ውሳኔዎች እንደሚካሄዱ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



