ጠላትና ወዳጅ ብለን ስንፈርጅ እንጠንቀቅ!

0
1514

ኢትዮጵያ አገራችን በረጅም ዘመን ታሪኳ በርካታ ጠላቶችንና ወዳጆችን አፍርታለች። በጊዜ ሂደት ጠላቷ የነበረ ወዳጅ እየሆነ ሲገለባበጥ የቆየ ቢሆንም፣ እንደአገራቱ ኃያልነትና መውረድ ሳትቀያየር ማንም ላይ በክፉ ሳትደርስ ዘመናትን አልፋለች።

ዘመናዊው የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደሚለው አንድ አገር ቋሚ ጠላትም ሆነ ወዳጅ አይኖረውም። ይህ ቢሆንም ግን አገራችን ኢትዮጵያን ዘላለማቸውን እንደጠላት ዕያዩዋት፣ ባዘነችበት ጉዳይ ሲደሰቱ ስትደሰትም ዐይናቸው የሚቀላ አገራት አሁንም እንዳሉ ይታወቃል። ዘመን አመጣሹ አስተሳሰብና የመንግሥት ሥርዓት ሲቀያየር፣ ደመኛችን ናቸው ብሎ ሕዝቡ የሚገምታቸው በሩቁ እንዲሆኑና በውስጥ ጉዳያችን እንዳይገቡ ከሚታሰቡ አገራት ጋር የተለያዩ መንግሥታት ወዳጅነት ለመመሥረት ሞክረው ሳይሳካላቸው እንደቀረ አሁን ካለንበት የዲፕሎማሲ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፋንበትን የሌላን ድርሻ የማንመኝ እንደሆንን ማንም ዜጋ ቢጠየቅ የሚመሰክረው ነው። የትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የበዝባዥነት ጥቅል አስተሳሰብ ባለመኖሩ የሌላን ንብረት እንደ ግል ሀብት የመቁጠር ዝንባሌም የለም ማለት ይቻላል። እንደምዕራባውያኑም ሌላን በመጨፍለቅ ወጥ ዓይነት አስተሳሰብና ቋንቋ፣ እንዲሁም ባህል እንዲኖር ላለመደረጉ አሁንም ድረስ ያሉ ጥቂትም ቢሆኑ የየራሳቸውን ይዘው የቆዩት ማኅበረሰቦች አመላካች ናቸው።

ሌላን የመንካትም ሆነ የመግዛት ፍላጎት የሌለንን ያህል፣ ሌላው አስተሳሰቡንም ሆነ ጉልበቱን ሊያሳርፍብንና ሊጭንብን ሲመጣ አለን የምንለውን እንግዳ ተቀባይነት ወደጎን ትተን እንደአመጣጡ እንመልሳለን። ይህ ሂደት እንደየወቅቱ ኹኔታ ጠላት ብናፈራበትም የወጉንንም ሆነ ጉድጓድ ምሰው መውደቃችንን የሚጠብቁትን የዘላለም ጠላት ከማድረግ እንቆጠባለን። ደጋግመው የወረሩንን ግብጽን፣ ቱርክን እና ጣሊያንን እንኳን የምንግዜም ጠላት ማድረግ የማይቻለን መሆናችንን ከምግባራችንና ባህላችን መመልከት ይቻለናል።

የዘለዓለም ጠላት ማድረጉ አስፈላጊ ነው ማለት ባይቻልም፣ የእኛን በጎ የማይመኙትን የሁልጊዜ ሸረኞችን ማመንና በእነሱ ሳቢያ የማይሆን መቧደን ውስጥ መግባት እንደሌለብን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ውስጣቸው ጥላቻ እንዳለባቸው የምናውቃቸውን የምዕራቡም ሆኑ የምሥራቁ ጎራ፣ አልያም የመካከለኛው ምሥራቅም ይሁኑ የአፍሪካ አገራትን የምናስቀምጥበት የታማኝነት ደረጃ ሊኖረን ይገባል። ኹኔታዎች እስካልተቀያየሩ ድረስ ለረጅም ዘመናት መስፈርት የምናደርገው የታሪካችን ነፀብራቅ የሆነ መመሪያ ሊኖረን ይገባል።

‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም› ነውና ብሂሉ፣ ደጋግመው እየወጉን እንርሳ ማለት ሞኝነት ነው። ከደጃፋችንም ያለውን ዛፍ እንድናሳድግ እያደረጉ ሲደርስ እየመጡ እንዳይቆርጡትም ብልጠት ከብልሃት ጋር ያስፈልገናል። ሕፃን የያዘውን ይዞ ለሌላ እንደሚያለቅሰው እኛ እናልቅስ ባይባልም፣ መርሃችን መሆን ያለበት እልህ ወይም የግል ስብእና ግንባታና ፍላጎት ሳይሆን የአገር ጥቅም ብቻ መሆን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

የቅርቡን እንኳን ብንመለከት፣ ከዓባይ ግድብ ጋር በተገናኘ እንደወዳጃችን ከጎናችሁ ነን ሲሉ የነበሩ የክህደት ሊባል የሚችል ተግባራቸውን ደጋግመን ተመልክተናል። የወዳጆችን ድጋፍ እንዳናገኝ በማድረግ ብቻም ሳይሆን፣ ያለንንም እንድናጣ ያልቆፈሩት ጉድጓድ እንዳልነበር አሁንም የምንመለከተው ነው።

ሽንፈትን እስከመጨረሻው የሚቀበል አስተሳሰብ ያለው ሰውም ሆነ ማኅበረሰብ ስለሌለ፣ ለጊዜው ሳይሳካላቸው ዝም ቢሉም ስንወድቅ ምሳር ሊያበዙብን እየተዘጋጁ መሆኑን ልንረዳ ግድ ይለናል።

የምዕራባውያኑ ጎራ በተለይ፣ ዓላማቸው የአገራቸውን ጥቅም ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ማዘዝም ስለሚዳዳቸው ክብርን መሠረት ያደረገ ቅርርብ ወሳኝ እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል። ሰው የሚከባበረው ራሱን የሚያስከብር እስከሆነ ድረስ በመሆኑም፣ ምንም ድሃ ብንሆን ስብእናችንን መሸጥ እንደሌለብን ልንገነዘብም ይገባል። ድሃ ነው ብለን ግለሰብን በሁሉ ነገር አሳንሰን እንደማንፈርጀው፣ እኛም አላግባብ መፈረጅም ሆነ ሌላን በዘላቂነት ፈርጀን አገራዊ ዓላማችንን ከማሳካት ወደኋላ ማለት እንደሌለብን መረዳት አለብን።

“በቃ” ወይም “ኖ ሞር” በሚለው እንቅስቃሴ የምዕራባውያኑን ተፅእኖ ከማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ውስጥ ለማላቀቅ የተደረገው ሙከራ ፍሬ ሳያፈራ፣ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል የተቀለበሰበት ኹኔታ ሊደገም እንደማይገባ ልንረዳ ግድ ይለናል። የሕዝብ ስሜትም ሆነ ሠልፍ የግል ፍላጎትን ማስፈጸሚያ ሳይሆን ዘላቂ አገራዊ አጀንዳን ማራመጃ መሆን ይኖርበታል።

እንደአገር ጠላት ብለን ለሕዝብ የምንፈርጃቸውንም ሆነ ወዳጃች ናቸው የምንላቸውን በአደባባይ ለሕዝብ ማመላከት ከመንግሥትም ጭምር ላይጠበቅ ይችላል። ማኅበረሰብ አንቂዎችም ሆኑ ተደማጭነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕዝቡን ስሜት መንዳት ሳይሆን፣ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሲጓዝ ጥቅሙን አሳልፎ እንዳይሰጥ ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘም ይሁን በግድቡ ምክንያት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስቀደም የሚሠራ አገርም ሆነ ዓለም ዐቀፍ ተቋም እንደማይኖር መረዳት ያስፈልጋል። ኹሉም ቅድሚያ ለራሱና ለመሰል ወገኑ እንደሚቆም ተረድቶ፣ ለወቅቱ የፍረጃ ፖለቲካ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

ከውጭ አገራት ጋር ባለ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በውስጥ ጉዳዮቻችንም ሆኑ ሽኩቻዎቻችን ቅድሚያ የአገር ጥቅምን በመቀጠልም የሕዝብ አብሮ መኖርን ታሳቢ ያደረጉ ገለጻዎችን መጠቀም ያስፈልጋል።

እገሌ ማኅበረሰብ የእነ እገሌ ጠላትም ሆነ ወዳጅ ነው ብሎ በደፈናው ማስቀመጡ አብሮ ለመኖር ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ ማነጻጸር ብቻ ሳይሆን፣ የኅብረተሰቡ አካል የሆኑ በተለይ ተደማጭ የሆኑ ግለሰቦችን ጭምር የእገሌ ወይም የእነ እገሌ ጠላት ወይም ደጋፊ ነው ብለን በጅምላ ከመናገርም መጠንቀቅ ይገባናል።

እንደ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትም የአገራችንን የፌዴራልም ሆኑ የግዛት መንግሥታትን ተቋማትም ሆኑ አገልጋዮች መፈረጁ አደገኛ መጨረሻ እንደሚኖረው ተረድተን ላልተገነዘቡ ማሳወቅ እንደሚኖርብን አዲስ ማለዳ ትመክራለች።

‹ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ አቃተን› እንደተባለው፣ በቀላሉ የሾምነውንም ሆነ ያሞገስነውን ለመንቀፍና ትክክለኛ ምግባሩን አሳውቀን ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ምን ያህል አዳጋች መሆኑን ለሁሌም ለማንም ቢሆን ተመሳሳይ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here