የመንግሥት እና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶችን በቀጥታ ድርድር ወደ ሥራ ለማስገባት የመንግሥት እና የግል አጋርነት አዋጅ እየተሻሻለ ነው።
ኢትዮጵያ ከ2010 ጀምራ በመንግሥት እና በግል አጋርነት(መግአ) የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የጀመረች ቢሆንም፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት በአዋጅ ቁጥር 1076/2010 ላይ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ፕሮጀክቶች እየቀረቡ አልሆነም ተብሏል። በዚሁ ምክንያት አዋጁን ለማሻሻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ ማሻሻያ የቀረበ ሲሆን፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሚቀርቡ የመግአ ፕሮጀክቶች በቀጥታ ድርድር ወደ ሥራ ለማስገባት በመሻሸል ላይ በሚገኘው አዋጅ ላይ የሚገኘውን መስፈረት ባለማሟላታቸው ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን በምክር ቤቴ የመንግሥት ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ ተናግረዋል።
የመንግሥት እና የግል አጋርነት ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ለሚተዳደረው፣ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጀነራል የሚቀርቡ ፕሮጀክቶች በአዋጁ የተደነገጉ መስፈርቶችን እያሟሉ ባለመሆናቸውን ፕሮጀክቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን በረቂቅ ማሻሻያው ላይ ማብራሪያ የሰጡት ተስፋዬ በምክር ቤቱ አብራርተዋል። የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 8/2015 ባካሄደው 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ አዋጁ ከወጣ ከአራት ዓመት በኋላ በመሻሻል ላይ የሚገኘው የመንግሥት እና የግል አጋርነት አዋጅ፣ ከመንግሥት ጋር በአጋርነት የሚሰሩ የግል ባለሀብቶችን ለመምረጥ የተለያዩ የጨረታ ዘዴዎችን ይከተላል። ከእነዚህም መካከል በዋናነት ተፈጻሚ እያደረገ የነበረው ግልጽ የጨረታ ዜዴን ነበር። በዘርፉ የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችን ለመቀበል እንቅፋት ኆነዋል የተባለው ቀጥታ ድርድር በአዋጁ የተካተተ ቢሆንም፣ በቀጥታ ድርድር ለመሳተፍ በአዋጁ የተደነገጉ መስፈርቶችን የማያሟሉ ፕሮጀክቶች መመለሳቸው ተሰምቷል። በዚህም ለዳይሬክተር ጀነራሉ የሚቀርቡ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶችን ተቀብሎ ከማስተናገድ ይልቅ ለመመለስ አስገዳጅ ሆኗል ነው የተባለው።
በአዋጁ መሰረት በመንግሥት እና በግል አጋርነት የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው፣ የቀረበው ፕሮጀክት በዳይሬክተር ጀነራሉ ቦርድ ሲጸድቅና የተቀመጡትን መስፈርቶች ሲያሟላ ነው። ይሁን እንጂ፣ በአዋጁ የተደነገገው መስፈርት ከሚቀርቡ ፕሮጀክቶች ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑም አዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን የመንግሥት ተጠሪው ተናግረዋል።
አጋጥሟል የተባለውን ችግር፣ ያስቀራል ተብሎ የቀረበው የማሻሻያ ሀሳብ ከቀጥታ ድርድር በተጨማሪ፣ መንግሥት ለመንግሥት የሚኖረውን ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነት መሰረት በማድረግ የፕሮጀክቱ አገራዊ ጠቀሜታ ሲታመንበት ከግል ባለሀብቱ ጋር በቀጥታ በሚደረግ ቀጥታ ድርድር እንዲተገበር ለመግአ ቦርድ እንዲቀርብ የሚፈቅድ ነው። በግል ባለሀብት የቀረበው ፕሮጀክት ማሟላት የሚገባቸውን ዝቅተኛ መመዘኛዎች የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ስለ ፕሮጀክቱ ሀሳብ አቀራረብ፣ ጥናት እና ድርድር ሂደት የሚወስኑ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች በማሻሻያ አዋጁ ተካተዋል።
በማሻሻያው ከተካተቱት መስፈርቶች መካከል በቀጥታ ድርድር በመንግሥት እና በግል አጋርነት እንዲተገበር ለቦርዱ የሚቀርብ ፕሮጀክት ሀሳብ፣ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት ዕቅድ እና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመነ መሆን ይኖርበታል። ዝቅተኛ መስፈርት ተብለው በማሻሻያ አዋጁ ከተረቀቁት መስፈርቶች መካከል፣ በዘርፉ ሦስትና ከሦስት በላይ ፕሮጀክቶችን በማልማት የቴክኒክ ብቃት እና የሥራ ልምድ ማቅረብ፣ ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚያስችል በማስረጃ የተደገፈ የፋይናንስ ተቋም ማሳየት፣ የሚቀርበቀው ፕሮጀክት ሀሳብ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎና የአገር ውስጥ ምርት መጠቀምን የሚያበረታታ መሆን ይጠበቅበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015


