በሩብ ዓመቱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

0
927

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ909 ሚሊዮን ብር አድጓል

በ2015 አንደኛ ሩብ ዓመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው የገቢ መጠን ጋር ሲነጻጸር ከ909 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው። በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ተናግረዋል።

በዚህም በተያዘው አንደኛ ሩብ በጀት ዓመት ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ከውጭ አገር ዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንት ገቢ የሆነ 62 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በ8100 አጭር መልዕክት 38 ሚሊዮን ብር በላይ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ660 ሚሊዮን የላቀ በድምሩ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው ያሳወቁት።

በ2013/2014 በጀት ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ909 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ባለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት የተገኘው ገቢ 287 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንደነበር አውስተዋል።

በዚህ ዓመት መስከረም ወር ከ535 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 449 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጭ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህ ሩብ ዓመት የተገኘው ገቢ በጣም ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፣ ይህም የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን በትኩረት በመሥራት ሊገኝ መቻሉ ተጠቁሟል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ እስካሁንም (እስከ መስከረም 30/2015 ድረስ) ከ18 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ለማወቅ ተችሏል።

የተገኘው ገቢ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነትና ልማት ያላቸውን አቋም የሚያመላክት ነው የተባለ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል።

እስካሁን ከ175 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የህዳሴ ግድቡ፣ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከ55 እስከ 60 ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ እንደሆነ እና አጠቃላይ ግንባታው እስከሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ድረስ ይጠናቀቃል መባሉ የሚታወስ ነው።

እንዲሁም ከ5 ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት በአፍሪካ ትልቁ ግድብ እንደሚሆን የተገለጸው የህዳሴ ግድቡ፣ እስካሁንም ኃይል ማመንጨት በጀመሩ ተርባይኖች አማካኝነት ከ500 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በላይ እያመነጨ እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እየተገነባ ያለውና ከተጀመረ ከዐስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው የህዳሴ ግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ከ87 በመቶ የላቀ መሆኑ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here