የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

0
912

ዕረቡ ጥቅምት 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።1. ምክር ቤቱ በቀዳሚነት የተወያየው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊና ዘላቂ የግብርና ልማት ፍላጎት በውጤታማ ምርምር ለማሳለጥ የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማልማት፣ የግብርና ምርምር ሥርዓቱን በማስተባበር፣ በመደገፍና በማበረታታት እንዲሁም ተቋማዊ ትስስርን በማጎልበት በግብርና ምርቶች ራሳችንን ለመቻል ብሎም የወጪ ንግድ ግቦቻችንን ለማሳካት ግልጽ ተልዕኮና ኃላፊነት ያለው ተቋም ማቋቋም በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡2. በመቀጠል ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣንን ሥልጣን፣ ተግባር እና አደረጃጀት ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ወቅቱ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የሚራመድ፤ የዜጎችን እና የአካባቢን ደህንነትና ጤንነት ያረጋገጠ እንዲሆን እንዲሁም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በተገቢው ወጪ፣ ጊዜ እና ጥራት መፈፀማቸውን በመቆጣጠር እና በመደገፍ የኢንዱስትሪውን ብቃትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የባለስልጣኑን አደረጃጀት እንዲሁም ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡3. በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርን እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርን ለማቋቋም በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ነው፡፡

የተቋማቱን አሠራር እና የመፈፀም አቅም ማላቅ፤ አደረጃጀቶቻቸውን ማዘመን እና ስልጣንና ተግባሮቻቸውን ግልፅ ማድረግ በማስፈለጉ፣ በተለይም ተቋማቱ የሚሰበስቡትን የጡረታ ፈንድ ትርፋማና አዋጭ መሆናቸው በጥናት በተለዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በማዋል አገራቸውን አገልግለው ጡረታ ለሚወጡ ዜጎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ቀጣይነት እና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ነባሮቹን ደንቦች ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here