ዕረቡ ጥቅምት 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ከ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ተፈታኞች ገንዘብ በመሰብሰብ የፈተና መልስ ሰጥተዋል የተባሉ ርዕሰ መምህሩን ጨምሮ 5 ሰዎች ላይ ክስ መስርቷል፡፡
ተከሳሾች 1ኛ አብዱ ሸኩር ጀማል (ርዕሰ መምህር)፣ 2ተኛ ዋና ሳጅን አብዲ ዩያ (የድሬዳዋ ፖሊስ)፣ 3ተኛ መሃመድ ጠሃ አብዱላሂ (መምህር)፣ 4ተኛ ማሙሽ አካሉ ተክሌ (መምህር)፣ እና 5ኛ ሲሳይ ደስታ ሚጆና (መምህርት) መሆናቸው ተገልጿል።
ተከሳሾች ከሰኔ 28/2014 እስከ ሰኔ 30/2014 የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት፤ 1ኛ ተከሳሽ በድሬዳዋ አስተዳደር በቢዮአዋሌ ክላስተር የለገቢራ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆን፤ ለፈተናዉ ሂደት ደህንነት እና ጥበቃ በት/ቤቱ ከተመደበው የድሬዳዋ ፖሊስ አባል ከሆነው 2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የት/ቤቱ ተፈታኝ የነበሩ 57 ተማሪዎችን 2ኛ ተከሳሽ በመሰብሰብ “የፈተና መልስ ተሰርቶ እንዲሰጣችሁ ለፈታኞች (3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች) መስተንግዶ የሚሆን እያንዳንዱ ተማሪ 100 ብር እንዲያዋጣ ያልከፈለ አይፈተንም!” ብሎ በመናገር ገንዘቡን ለ1 ተማሪ እንዲሰጡ ማድረጋቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህም ከ44 ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው 100 ብር፣ ከ11 ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው 50 ብር አጠቃላይ 4 ሺሕ 950 ብር ተሰብስቦ ለ2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጥቅም የዋለ ሲሆን፤ ለተማሪዎቹ የባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ የህብረተሰብ ሳይንስ እና የስነ-ዜጋ የትምህርት አይነቶችን ፈተና መልስ በማለት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እየዞሩ ተማሪዎቹ እንዲሞሉ ያደረጉና፤ ዉጤት ይፋ ሲደረግ ኹሉም ተማሪዎች ከማለፊያ ነጥብ በታች ማምጣታቸው መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
በመሆኑ ተከሳሾች በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ክስ እንደመሰረተባቸው ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ክሱ ለተከሳሾች እንደደረሳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የድሬዳዋ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ተከሳሾች ከጠበቃ ጋር ተማክረዉ ለመቅረብ በጠየቁት መሰረት ለጥቅምት 22/2015 ቀጠሮ እንደተሰጣቸውም ታውቋል፡፡



