ኬሚካልና ውበት

0
1050

የሰው ልጅ ስለውበቱ መቼ መጨነቅ እንደጀመረ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ እርስ በርሱ ተዋልዶና ተባዝቶ አብሮ መኖር ሲጀምር፣ በልጦና የተለየ ሆኖ ለመታየት ሲጥር መሆኑን መገመት ይቻላል። ውበትን መጠበቅ የሴት ወይም የወንድ ብቻ ተብሎ የሚፈረጅ አለመሆኑን በተለያዩ አገራት ካሉ የመዋቢያ መንገዶችም መረዳት ይቻላል።

በአገራችን ጭምር ገላቸውን ለማሳመር ጭቃን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ በርካታ ወንዶች የመኖራቸውን ያህል፣ ሸክላን ጨምሮ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መዋቢያዎችን በስፋት የሚጠቀሙ በርካታ ማኅበረሰቦችን መመልከት ይቻላል። መዋቢያ ማለት ሰውነትን የሚቀባቡት ነገር ብቻ ሳይሆን፣ አለባበስንም ሆነ አበጣጠርን አልያም ፀጉር አሰራርንም የሚጨምር በብዙ ዘርፍ የሚታይና ሰፊ ጥናት የሚሻ ጉዳይ ነው።

ተፈጥሮን ብንመለከት እንኳን የተለያዩ አእዋፍት፣ ዶሮን እና የመሳሰሉ እንስሳት ጭምር ራሳቸውን ሲያስውቡ እንመለከታለን። ለምሳሌ ከአእዋፋት አብዛኞቹ ወንዱ ውበቱን ጠብቆ በመልኩ ሴቶችን ማማለል ስለሚጠበቅበት ላባውንም ሆነ ገጽታውን ተንከባክቦ ያቆያል።

የሰው ልጅም እንደአፈጣጠሩ የተለያየ ጠባይ ቢኖረውም፣ ውበትን ከመጠበቅ አኳያ መገለጫው ይለያይ እንጂ ኹሉም ማኅበረሰብ ይጠቀማል ማለት ይቻላል። ቀይ አፈርን በቅባታማ ፍሬ አቡክተው ሹሩባ ፀጉራቸውን የሚለቀልቁ፤ ከንፈራቸውን ቀደው እያሰፉ ሸክላ የሚወጥሩ፤ ትልልቅ ብረትና ዶቃ አስውበው የሚያደርጉ፤ እርቃን ገላቸውን ወንዝ ወርደው በነጭ ዥንጉርጉር የሚያስዉቡ፤ ፀጉራቸውን ጋርሶ ተቆርጠው የሚታዩ፣ ጎፈሬያቸውን በቅቤ የሚያብረቀርቁ፣ የተለያዩ እጽዋትን ተጠቅመው ራሳቸውን የሚያጥኑ፤ እንሶስላና ሂና የሚቀቡ እንዲሁም የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ጭምር ቀምመው ሰውነታቸውን በጥሩ መዓዛ የሚያውዱ ማኅበረሰቦች እዚሁ አገራችን በሰፊው ይገኛሉ።

ለአንዱ ማስዋቢያ የሆነው ለሌላው መመላለጫ ሊሆን ቢችልም፣ ዓላማውና ዕይታው ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ፀጉርን ማሳደግ የውበት መገለጫ የሆነበት ማኅበረሰብ የመኖሩን ያህል መመለጥም በተመሳሳይ ውብ የሚያስብልበት ማኅበረሰብ አለ። እንደአስተሳሰቡና ባሕሉ ኅብረተሰቡ የተለያየ አመለካከት ቢኖረውም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየተመሳሰለ መምጣቱን መመልከት ይቻላል።

ከአለባበስ ጀምሮ አብዛኛው ማኅበረሰብ የየራሱን ባሕልና ወግ እየተወ የምዕራባውያኑን እየተከተለ ስለመሆኑ የኅብረተሰቡን የየእለት አለባበስ መመልከቱ በቂ ነው። ቀላል ርካሽና ተለይቶ የማያስቀር ወጥ የሆነ አለባበስም ሆነ ባሕል እየተንሰራፋ ሲመጣ፣ አስተሳሰብም ስለሚመሳሰል የውበት መገለጫም እንዲሁ ወጥ መስፈርት ወደመኖሩ ማምራቱ አይቀሬ ነው።

መወፈር የጥሩ ሁኔታ መገለጫ መሆኑ እየቀረ ቀጭንነት ዘመናዊነትና የቁንጅና መለኪያ እየሆነ መምጣቱንም ለኪነጥበብም ሆነ ለፋሽን የሚመረጡትን ተመልክቶ መረዳት ይቻላል። አለባበስና የሰውነት አቋም ብቻም ሳይሆን፣ የፀጉር ሁኔታም እንዲሁ ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱን መመልከት ይቻላል። በቀደመው ዘመን ወንዱም ሴቱም ረጃጅም ፀጉር እንደነበራቸው ከቆየ ታሪኮችና ምስሎች እንረዳለን።

በአገራችን አብዛኛው ማኅበረሰብ ወንድ አጎፍሮ ሴት ደግሞ ሹሩቤ መሆን የሚጠበቅባት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ተደበላልቆ ይታያል። ጀግንነቱን ካስመሰከረ ንጉሥ በስተቀር ወንድ ሹሩባ መሠራት የተከለከለ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ፋሽን ተብሎ ማንም እንደፈለገ ይሠራዋል። እንዲሁ መኳኳልንም ቢሆን ለሴት ብቻ ማን አደረገው ብለው ለውበታቸው ከአብዛኛው ሴቶች በበለጠ የሚጨነቁ ወንዶችም እየበዙ ይገኛሉ።

ውበትን ለመጠበቅ ለዘመናት ጥቅም ላይ የሚውለው ከተፈጥሮ የተገኘ ማስዋቢያ እንደመሆኑ ብዙም ሳይቀየር እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በስፋት ሲያገለግል ቆይቷል። ካለፈው ምዕተ ዓመት ወዲህ ግን ዘመናዊ የሚባሉ ሰው ሠራሽ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተከትሎ ለማስዋቢያ ኢንዱስትሪው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ሰው ሠራሽ የኬሚካል ይዘት ያላቸው መዋቢያዎች ለአጠቃቀም ምቹ የመሆናቸውና በቀላሉ ተዘጋጅተው ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የሚችሉ ቢሆንም፣ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው ሲነገርም ይደመጣል። እንደሰው ቆዳ ዓይነት ተመሳሳይ ምርቶች የተለየ ውጤት ሊያስገኙ ከመቻላቸው ባሻገር፣ በጊዜ ሂደት ቆዳንም ሆነ የሰውነት አካልን እየጎዱ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ሲደረግ ይሰማል።

የውበት መጠበቂያዎች በስፋት ስለሚመረቱ፣ ጉዳት ካስከተሉም መጠነ ሰፊ ስለሚሆን እንደምግብ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ እንዲሆኑ ከመገምገም ባለፈ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው እንዳያልፍም ክትትል እንዲደረግ ይመከራል።

ይህም ቢሆን ግን ከማስዋቢያዎቹ ተፈላጊነት አንፃርም ሆነ ከዋጋቸው አኳያ የተለያዩ ምርቶች ተመሳስለው እንደሚመረቱ፣ እንዲሁም የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና ፈቃድ ያላገኙትም ገበያ ላይ ሲውሉ ይታያሉ። ይህም ኬሚካል አዘል መዋቢያዎችን አደገኛነት ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል።

የዘመናችን ሰዎች ለውበታቸው ሲሉ ከሚጠቀሙባቸው የተፈጥሮ ነገሮች ይልቅ ሰው ሠራሾቹ እጅግ እየበዙና ለመከታተልም እጅግ አስቸጋሪ እየሆኑ መምጣታቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ለቆዳም ሆነ ለፀጉር እንዲሁም ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቅባቶችንም ሆኑ ሳሙናዎችንና ማንኛውንም ንጥረነገሮች የመፈተሽ ተግባር በተለያዩ ተመራማሪዎች እየተካሄደ ይገኛል።

ስለውበት መገለጫና ስለኬሚካል ማስዋቢያ ይህን ያህል ያልናችሁ በዘመናችን በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል የፀጉር ማስዋቢያ ካንሰር ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ሰሞኑን ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተከትሎ ነው። ሴቶች ፀጉራቸውን ቀጥና ለስላሳ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ኬሚካል ላይ ነው ጎጂ ንጥረነገሮች ተገኙ የተባለው።

በጥናቱ መሠረት የሴቶች መራቢያ አካል ላይ የሚከሰት ካንሰርን ሊያመጣ ይችላል የተባለው ሁሉም ዓይነት የፀጉር ማስዋቢያ አይደለም። የፀጉር ቀለም፤ ፐርም እና ቀለም ማስለቀቂያ የመሳሰሉት ላይ ካንሰሩን የሚያመጣ ምንም ዓይነት ንጥረ ነገር አለመገኘቱን አሳውቀዋል።

በሽታው ሊከሰትባቸው የሚችሉት ፀጉርን ቀጥ ማድረጊያ ኬሚካልን አልፎ አልፎ የሚጠቀሙት ሳይሆኑ፣ አዘውተረው የሚገለገሉበትን ነው ሲሉ ተመራማሪዎቹ መናገራቸውን ‹ዘ ዊክ› የተሰኘው ድረ ገጽ አስነብቧል።

ኬሚካሉን በዓመት ከአራት ጊዜ በላይ የተጠቀሙ ሴቶች ከማይጠቀሙት በላይ በዮትሪን ካንሰር የመጠቃት እድላቸው በእጥፍ እንደሚጨምር የአሜሪካው ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሄልዝ ተመራማሪዎች ይፋ ማድረጋቸው ተነግሯል። እንደጥናቱ ከሆነ፣ እድሜያቸው ከ35 እስከ 74 የሆናቸው ከ33 ሺሕ በላይ ሴቶች በምርምሩ የተካተቱ ሲሆን፣ ለ11 ዓመታት በተደረገላቸው ክትትል 378 ላይ ካንሰሩ ተገኝቷል።

እንደጥናቱ ውጤት ከሆነ ኬሚካሉን የሚጠቀሙት የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይጠቁማል እንጂ ምንም ኬሚካሉን ካልተጠቀሙትም 1 ነጥብ 64 በመቶ የሚሆኑት በዩትሪን ካንሰር ተይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን በተለምዶ ተጠቃሚ የሆኑትን የመያዝ እድሉ 4 ነጥብ 05 በመቶ ነው ብለዋል።

ዩትሪን ካንሰር ከሌሎች ከተለመዱት የካንሰር ዓይነቶች የተለየ ነው ማለት ባይቻልም የተለመደ አይደለም። ከአጠቃላይ የካንሰር በሽታዎች 3 በመቶውን የሚይዘው ይህ በሽታ በሴቶች መራቢያ አካል ላይ ከሚከሰቱት የተለመደው ሲሆን፣ እያደር እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ፀጉራቸው ከርዳዳ የሆነባቸው ጥቁሮች የበለጠ ምርቶቹን ስለሚጠቀሙ በዚህ የመራቢያ አካል ካንሰር የመጠቃት እድላቸውም ይበልጥ ሰፊ መሆኑ ተመላክቷል። ይህ በአሜሪካ የተደረገ ጥናት እንደመሆኑ ዓለም ዐቀፍ ይዘቱ ምን እንደሚመስል የበለጠ ጥናት የሚፈልግ ነው ተብሏል።

በምርምሩ መሠረት ፀጉር ቀጥ ማድረጊያ ኬሚካሉን የሚጠቀሙ ሴቶች ለዩትሪን ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው በእጥፍ ይጨምራል ተባለ እንጂ የትኞቹ ምርቶች የበለጠ ጎጂ ናቸው አልተባለም። በኬሚካሉ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮች የተጠቀሱ ሲሆን፣ ሴቶች በሚቀቡበት ወቅት ወደ ሰውነታቸው ዘልቆ ስለሚገባ ለጉዳት ያጋልጣቸዋል ተብሏል።

ፀጉርን ቀጥ የሚያደርግ ኬሚካል ለካንሰር አጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው የሚል የጥናት ውጤት እስካሁን ይፋ ሆኖ አያውቅም። ነገር ግን፣ የፀጉር ቀለምን በዘላቂነት የሚቀይር ማቅለሚያ ኬሚካል ለጡትና ለማሕጸን ካንሰር እንደሚያጋልጥ ከዚህ ቀደም ይፋ ተደርጓል።

ከሰሞኑ ይፋ የተደረገውን ይህን ጥናት ተከትሎ አንዲት በካንሰር የተጠቃች አሜሪካዊት ሴት ግዙፍ የሆነ የማስዋቢያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያን ከሳለች። ለበሽታዬ መንስዔ የሆነ ምርት ሸጦልኛል ብላ ክስ ስለማቅረቧ ሬውተርስን በመሳሰሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ቢዘገብም፣ የክሷ ተቀባይነትም ሆነ ውጤታማ ስለመሆኗ መነጋገሪያ ሆኗል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here