በኢትዮጵያ ግብር ለመክፈል በዓመት ሶስት መቶ ሰዓት ይባክናል

0
818

በኢትዮጵያ አንድ ግብር ከፋይ ግብሩን ለመክፈል ሶስት መቶ ሰዓታትን በዓመት ውስጥ እንደሚያጠፋ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት ላይ አስታወቀ።
በመጪው የአውሮፓዊያኑ አመት 2020 ንግድን ለመጀመር ምቹ የሆኑ አገራትን ስም ዝርዝር ያወጣው ሪፖርቱ በተለያዩ ዘርፎች አገራትን የመዘነ ሲሆን፤ በዚህም ረገድ ኢትዮጵያን በግብር አከፋፈል ቀልጣፋነት ጋር በተገናኘ ሶስት መቶ ሰዓታትን የምታባክን አገር አድርጎ 190 የዓለም አገራት ውስጥ 132 ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል።

ከግብር አከፋፈል ቀልጣፋነት በተጨማሪም ንግድን ለመጀመር ካለው ምቹነት አኳያም 168 ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ብድር ከሚገኝባቸው 190 አገራት ውስጥ 176ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ውስጥ 57 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 102 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አዲስ ማለዳ በቀደመው ዕትሟ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

በግብር አሰባሰቡ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት 250 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደታቀደ የገቢዎች ሚንስትር ይፋ አድርጓል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጰያ ለትናንሽ አልሚዎች በምታደርገው ከለላ ከዓለም 189ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቋል።
ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ አገራት 10 ነጥቦችን መሰረት በማድረግ ደረጃ የሚወጣላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ በኹለት ነጥቦች በማሻሻል በአጠቃላይ ከነበረችበት የ161ኛ ደረጃ 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፣ ይህም አመርቂ እዳልሆነ ይህንን ለማሻሻል እንደሚሰራ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here