ስርዓት አልበኝነቱን ማቆሚያ የት ይሆን!?

0
654

ለሰሞኑን ግጭት መነሻው ለውጥ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ኢሕአዴግ በሕዝቦች መካከል አንብሮት የነበረው የከፋፍለህ ግዛ ውጤት ነው የሚሉት ግዛቸው አበበ፥ ወጣቶቹ ወደ እርስበርስ መናቆር ከማምራታቸው በተጨማሪ ምንም ዓይነት የጠራ ዓላማና ስትራቴጂ፣ ተጋፋጭነትና ቁርጠኝነት ሳይኖራቸው ስለሚንቀሳቀሱ ለሕዝቦቻቸው ሰቆቃዎችን እያሸከሙ መጥተዋል ይላሉ። ግዛቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ እና ለኢትዮጵያ ቆሚያለሁ የሚል ቡድን ትንንሽ የሚመስሉ ችግሮችን ከመፍጠርም ሆነ የተፈጠሩ ችግሮችን አቃልሎ ከማየት ታቅቦ ለሰላም፣ ለሕዝብ ደኅንነት ለአገር ሕልውና ሊሠራ ይገባዋል ሲሉ ይሞግታሉ።

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ስርዓት የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም የከፋፍለህ ግዛ ብቻ ሳይሆን ከፋፍሎ ማናቆር ስልትን እየተጠቀመ እስከ 2010 መዝለቁ ይታወቃል። ለዚህ ስልት ስኬት ደግሞ ኦሮሞውን እንደ ቦምብ አማራውን እንደ ዒላማ በማድረግ ኹለቱን ትልልቅ ሕዝቦች በማጋጨት ባላጋራን (ተቃዋሚን) የማዳከም ተገቢነት ታምኖበት ጥላቻዎች ሲዘሩ፣ ጥላቻዎች፣ ግጭቶችንና መፈናቀሎች ሲወልዱ 27 ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ይህ የቦምብና ዒላማ ሴራ የሚያከትለው ውድመት ዒላማ ከተደረገው ከአማራው ሕዝብ አልፎ ራሱን ኦሮሞውንም ግዳይ እያደረገ መዝለቁ የሚካድ አይደለም።

የሕወሓት/ኢሕአዴን የብሔር የብሔረሰቦች ነጻ አውጭነት ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ሲነገር የነበረው ‘….ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ሕወሓት ከአማራ ብሔራዊ ጭቆና ነጻ አወጣው…’ የሚለው ተረክ የፈጠረው እሳቤ ቢሆንም ባለፉት 27 ዓመታት ‘…የአገራችን ግዙፍ እስር ቤቶች ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኗል…’ እስኪባል ድረስ ኦሮሞ ወገኖቻችን ሰለባ ሆነው ኖረዋል። እስር ቤቶች ከ14 እስከ 80 ዓመት ዕድሜ የሆናቸው ኦሮሞ ወገኖቻችንን አጉረው ጉድ አስብለዋል። ባለፉት 27 ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች አንዴ በኦነግነት ሌላ ጊዜ በአልሸባብነት ከ2008 ጀምሮ ደግሞ በቄሮነት ተፈርጆ ለሞት፣ ለስደትና ለእንግልት ተዳርጓል። ኦሮሞ ወገኖቻችን ነጻ ወጥታችኋል በተባሉበት በ27 ዓመታቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን ክፉኛ መጎዳታቸውን መካድ አይቻልም። ከዚህ ሌላ የጉዳቱ አድማስ ቦምብና ዒላማ በተደረጉት በኦሮሞና በአማራ ሕዝቦች ላይ ተወስኖ የቀረ አልሆነም። ሌሎች ብሔረሰቦችም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የስርዓቱ ሰለባዎች ሆነው ኖረዋል።

ለዚህም ነው ሁሉም ከሁሉም ብሔረሰቦች የተውጣጡ ወጣቶች ስርዓቱን እያማረሩና በየአጋጣሚው እየታገሉት የኖሩት። የስርዓቱ የከፋፍለህ ግዛ ሴራ የረቀቀና ከየብሔረሰቡ በተውጣጡ ግለሰቦችና በየብሔረሰቡ ሥም በተድበለበሉ ተለጣፊ የፖለቲካ ቡድኖች ጭምር የታገዘ ስለነበረም ትግሉ መራርና ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ ሆኖ ታይቷል። የከፋፈለህ ግዛው ሴራና ክፍፍሉ እንዲነግስ ለማድረግ ሲባል የተፈጠሩና እየተጋነኑ የተነዙ ሐሰተኛ የጨቋኝ-ተጨቋኝ፣ የአሳዳጅ-ተሳዳጅ፣ የዘራፊ-ተዘራፊ ወዘተ… የፈጠራ ታሪኮች መላው የአገሪቱ ሕዝብ አንድ ሆኖ ስርዓቱን መታገል እንዳይችል ከማድረጉም በላይ ብዙዎች ተቃዋሚወች ነን ባይ ግለሰቦችና ቡድኖችም የእነዚህ የሐሰት ወሬዎች ሰለባወች ሆነው በመገኘታቸው፣ እነሱንና ሕዝባቸውን የሚለበልበውን እሳት ችላ ብለው ከመቶና ከኹለት መቶ ዓመታት በፊት ‘ነበረኝ’ የሚሉትን ቁስል ለመፈወስ የሚራወጡ የዋሆች ሆነው ከርመዋል። በእርግጥ አንዳንዶቹ ከእሳቱ ርቀው በሌላው ለመለብለብና መንደድ የታጋይነትንና የጀግንነትን ካባ ለመጀቦን የበቁ፣ ከማንም በላይ አሳቢና ተቆርቋሪ ተደርገው የሚወደሱ ብልጦች ሆነው ታይተዋል።

አሳዛኙ ነገር ይህን ስርዓት እንቃወማለን የሚሉ ወገኖች ክፍፍል ውስጥ ገብተው እርስ በርሳቸው ከመናቆራቸው በተጨማሪ ምንም ዓይነት የጠራ ዓላማና ስትራቴጂ፣ ተጋፋጭነትና ቁርጠኝነት ሳይኖራቸው ስለሚንቀሳቀሱ ለሕዝቦቻቸው ተጨማሪ ሰቆቃዎችን እያሸከሙ ኖረዋል።

በገሀድ እንደሚታወቀው፣ በውጭ አገራት በተለይም አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ ሆነው አገር ቤት ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ለትግል እያሰማሩ መሆኑን ሲነግሩን የነበሩ ብዙ አክቲቪስቶች ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ተከትሎ፣ የጉሮ ወሸባዬው ብዛት በእነሱ ጀግንነት ትግሉ የተጠናቀቀ አስመስሎ ስላሳያቸው አንድ ሚስጢራቸውን ሹክ ብለውናል። እነዚህ የትግል መሪዎች በመገናኛ ብዙኀን ላይ ቀርበው የተነሱላቸውን ጥያቄዎች ሲመልሱ ‘አናርኪዝምን’ (ስርዓት አልበኝት) እንደ ስትራቴጂ ይጠቀሙ እንደነበረ በግልጽ ተናግረዋል። ይህ ስትራቴጂ በየሰበቡ ብጥብጥን በመፍጠር ነውጥን ማንገስ፣ በነውጥም የመንግሥትን ወንበር መነቅነቅ ይቻላል በሚል እሳቤ አድርገው ይከተሉት እንደነበረ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ይህን ስትራቴጂ ለማራመድ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራወች፣ ትምህርት ቤቶች (ዩንቨርስቲዎችን ጨምሮ)፣ የገበያ ቦታዎች፣ ሕዝብ በአደባባይ የሚውልባቸው የበዓል ቀናት ወዘተ…ተመራጭ የትግል ቦታዎችና አጋጣሚዎች ተደርገው እንደነበረ ሁላችንም እያየነው የኖርነው ጉዳይ ነው። እነዚህ አታጋዮች በግልጽ ባይነግሩንም የአናርኪዝሙን እሳት ለማፋፋም የዘር፣ የጎሳ፣ የሃይማኖትና የመሳሉት ልዩነቶችን እንደ ነዳጅ አድርገው መጠቀማቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ይህን መሰሉ አካሔድ የሕወሓት/ኢሕአዴግን ስርዓት እንዳናጋውና ለውጡ መምጣትም መንስኤ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን አካሔዱ ከእሳቱ ርቀው ላሉት ግለስቦችና ቡድኖች እንደ ጨዋታ የሚቆጠር ቢሆንም ሕዝብን እና አገርን ዋጋ እንዳስከፈለና የዚያን ጊዜው አባዜ አሁንም አልለቅም ብሎ በመላ አገሪቱ ችግር እያስከተለ መሆኑ የሚካድ አይደለም።

ለውጡ መጥቶ ተደምረናል ተብሎ ከተነገረ በኋላም ቢሆን እነዚህንና እነዚህ የመሰሉ ጅምላ ጥላቻ የሚያስፋፉ አካሔዶች በተዘዋዋሪና በገሃድ ሲሰነዘሩ ሰምተናል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ወደ ተግባር ሲመነዘሩ እያየን ነው።

በውጭ አገራት ሆነው ወጣቶቹን ለዓመጽ ሲያነሳሱ የነበሩ አክቲቪስቶች ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ተከትሎ ሲያራምዱት የነበረው ስርዓት አልበኝነት፣ ዘርን/ጎሳንና እምነትን መሰረት አድርጎ የተዘራው ጥላቻ ያስከተለውን ትርፍና ኪሳራው አስልተው ተከታዮቻቸው በዚህ የለውጥ ጊዜ ውስጥ ሊደርጉት ስለሚገባው ማስተካከያ ምንም ዓይነት ትምህርት ወይም ምክር ሲሰጡ አልታዩም። አንዳንዶቹም ፈጥነውም ሆነ ዘግይተው የቀድሞውን ስልታቸውን ተጠቅመው ለውጡን ለማዳከም፣ የለውጡን መንፈስ ለማደፍረስ ብሎም ለውጡን አደጋ ላይ እስከ መጣል የደረሰ ችግር ለመፍጠር በቅተዋል። እንዲያውም ቀድሞውንም ቢሆን ለዓመጽ ይመቻሉ ተብለው ግጭትንና ኹከትም ለማራመድ ጥቅም ላይ ውለው የነበሩት ዩንቨረሲቲዎች፣ ስታዲዮሞችና ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው አጋጣሚዎች በቋሚነት የኹከት አዝመራ የሚዘራባቸውና ግጭቶች የሚዘወተሩባቸው ሆነው በመታየት ላይ ስለሆኑ ስርዓት አልበኝነቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስፋትና ኀይል እየሠራ መሆኑን ያሳያል። በ2011 ስቴዲዮሞችና ዩንቨርስቲዎች ከኹከትና ከግጭት ሳይጸዱ ዓመቱን አሳልፈዋል። ስታዲዮሞች የመዘላለፊያና የመደባደቢያ አምባዎች ሆነው ሲታዩ ዩንቨርስቲዎች ደግሞ ምሁር ልጅ የሚጠባበቁ ወላጆችን አስከሬን አሳቅፈዋል።

በውጭ ሆነው የስርዓት አልበኝነትን አካሔድ ሲያቀነቅኑ ከነበሩ መገናኛ ብዙኀን ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ወደ አገር ቤት ገብተው በቀድሞው አካሔዳቸው መመላለሳቸው አልበቃ ብሎ እዚሁ አገር ቤት የነበሩና ያሉ መገናኛ ብዙኀንም በተመሳሳይ ሚዛኑን የሳተ አካሔድ መንጎድ ጀምረዋል። አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን አጋጣሚዎችን እየተጠባበቁ በቋሚነት የሚጠሯቸው እንግዶች የሰየሙ ይመስላል፤ እነዚህ ወደ ሚዲያዎቹ ብቅ ባሉ ቁጥር ጥላቻቸውን ለመደበቅ ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ሳያደርጉ ያሻቸውን ሲናገሩ ይሰማ። መገናኛ ብዙኀን የአንዱን ስርዓት አልበኝነት ኮንነው የሌላውን ሲያሞካሹ እየተሰሙ ነው። መንገድ ዘግተው እህልና በግ ከመኪና እያወረዱ የሚዘርፉ ወጣቶችን ‘…. እነ እንቶኔን በረሃብ ለመቅጣት የሚተጉ ጀግኖች…’ እያለ ያወድሰው ሚዲያ በሌላ በኩል መንገድ ዘግተው የሕዝብ ማጓጓዣ መኪኖችን ጉዞ የገቱ ወጣቶችን ‘….በሽተኞች ወደ ሕክምና ቦታ እንዳይደርሱ ያደረጉ አረመኔዎች….’ ሲል ይኮንናል።

በሌላ በኩል ደግሞ እህልና ፍየል ከመኪና አውረደው የዘረፉ ወጣችን ‘…ሌቦች…’ ብሎ ያብጠለጠለው ሚዲያ ብዙ ቤተሰቦችን ላባቸውን ጠብ አድርገው ካፈሯቸው የጋራ መኖሪ ቤቶቻቸው እያስወጡ፣ የሰው ቤት ነጥቀው የእነሱ መኖሪያ ያደረጉ ወጣቶችን ‘…..ለክልላቸውና ለጎሳቸው ተቆርቋሪዎች…’ ብሎ ያወድሳቸዋል። ይህን መሰሉ አካሔድ ስርዓት አልበኝነትን በዘርና በጎሳ መነጽር በማየት የማበረታታት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሚያስረዳ ጉዳይ ነው።

በቅርብ የተከሰተውና ከ60 በላይ ለሚሆኑ ወገኖቻችን ሕልፈት ሰበብ የሆነው አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተት አልቆም ያው ስርዓት አልበኝነት የወለደው ጥፋት ነው። ይህ አሳዛኝ አጋጣሚ ኢትዮጵያችን መጠነ ሰፊ የሆኑ የዘር፣ የጎሳና የሃይማኖት ግጭቶችን በቀላሉ ሊያቀጣጥሉባት በሚችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች መዳፍ ውስጥ እየወደቀች መሆኑን የሚያሳይ ፍጻሜ መሆኑን አሌ ማለት አይቻልም። አንድ ግለሰብ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ የተከሰተው ይህ እልቂት ከየቤታው የወጡ ወጣቶች ሕይወትን ያህል ነገር እንደ ዋዛ በድንጋይና በስለት የቀጠፉበት አጋጣሚ ስለሆነ በአሁኑ ወቅት እልቂቶችን እንዲከሰቱ ማድረግ ምን ያህል ቀላል ድርጊት ተደርጎ እየታየ መሆኑን የሚያሳይ ነው። የኦሮምያ ክልል የፖሊስ ኮሚሽነር ለአንድ የውጭ ሚዲያ በስልክ በሰጡት መረጃ መሰረት፣ በኹለት ቀን ግጭት ከሞቱት 67 ሰዎች መካከል ከ13ቱ በስተቀር ሌሎቹ በድንጋይና በስለት የተገደሉ መሆናውን ገልጸዋል።

ችግሩ በዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በቡራዩና በአሸዋ ሜዳ አካባቢ የተቀሰቀሱና የተለያዩ ወገኖችን ዒላማ የደረጉ ግጭቶች መላ ስላልተበጀላቸው፣ ወንጀለኞች ባለመቀጣታቸውና ሕገወጥነት በመበረታታቱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ ከቡራዩው አሳዛኝ የጭካኔ ዘመቻ ቀጥሎ በርካታ ተመሳሳይ ግጭቶች ዘርን፣ ጎሳንና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው እየተቀሰቀሱ፣ የሕይወትና የአካል ግብር ሲያስከፍሉ እየታዘብን ከቆየን በኋላ የአሁኑን የጥቅምት አጋማሹን ችግር ለማስተናገድ ተገድደናል።
ሰኔ 16/2010 ከተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ጀምሮ እስከ ሰኔ 15/2011 የባለሥልጣናት ግድያ ዘመቻ እስከተካደበት ጊዜ ድረስ በጣም ብዙ በመሳሪያ የታገዙ፣ በግለሰብ ወይም በሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በመላ አገሪቱ ሊባል በሚችል ደረጃ (በምዕራብ ኦሮምያ፣ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ሸዋ፣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች፣ በሲዳማ፣ በጉጂ ዞን፣ በኮንሶ ወዘተ….) ተካሒደው ብዙ ሕይወት ቀጥፈዋል።

ብዙዎቹን እኩይ ዘመቻዎች ተከትሎ ያልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ሰነዘሩ ወይም ተጠርጣዎች ተያዙ የሚል ወሬ በመንግሥት አካላት በኩል ከሰማቱ በስተቀር ለብዙዎቹ ጥፋቶች ተጠያቂ የተደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍርዳቸውን ሲያገኙ አይታይም። በሌላ ኀይል የሰለጠኑና የታጠቁ ግለሰቦችና ቡድኖች ጦርነት አከል ጥቃቶችን ማድረሳቸው ቢነገርም ያ ሌላ ኀይል በይፋ አለመገለጹ እንዳለ ሆኖ ብዙውን ጊዜም የተላኩ የተባሉት አጥቂዎች ማንነትም ይፋ ሳይደረግ ይቀራል። ይህ ደግሞ ሕዝብ መንግሥት በሌለበት አገር በመኖር ላይ እንደሆነ ሆኖ እንዲሰማው እያደረገ ነው። አዲስ አበባና ኦሮምያ ውስጥ ግርግርና ኹከቶች ሲቀሰቀሱ ግለሰቦች ወይም ሆ ብለው የወጡ ወጣቶች አካባቢያቸውና ቤታቸውን ለመጠበቅ እንዲነሳሱ ሲያርግ ታይቷል። የዚህ ዓይነቱ አካሔድ አገሪቱ ወደ መጠነ ሰፊ የእርስ በርስ ግጭት እየተንደረደረች መሆኑን አመላካች መሆኑን መካድ ተገቢ አይደለም።

የዚህ ዓይነቱ የወጣቶች በቡድን ደረጃ መፋጠጥና መጋፈጥ የመንግሥትና የሕግ አስከባሪ አካላት ችላ ባይነት የወለደው አደገኛ አካሔድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የዚህ ዓይነት ፍጥጫና ግጭት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አመራሮችና ፖለቲከኞች ውስጥ ጥቂቶቹ ለአንዱ ወገን የወገነ አስተያየት ሲሰነዝሩና ዛቻ ሲያሰሙ ተሰምተዋል። ከዚህ ሌላ በአንድ ወገን ፖሊስና ወታደሮች ዝም ብለው እያዩ ነው የሚሉ የአካካቢ አስተዳዳሪዎች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ድንጋይ በያዙ ወጣቶች ላይ ወታደሮች/ፖሊሶች ተኩስ ከፈቱ ብለው የሚያማርሩ ወገኖች አየተደመጡ ነው። እዚህ ላይ ‘ሰላማዊ ሰልፍ ማለት ምን ማለት ነው?’ ብሎ ለመጠየቅ የግድ የሚል አነጋገርም ይሰማል። በሰላማዊ መንገድ መንገድ ሲዘጉ ተተኮሰባቸው፣ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ድንጋይና ዱላ የያዙ ወጣቶች ጥቃት ተሰነዘረባው ወዘተ… የሚል ምሬት መሳይ ንግግርም እየተሰማ ነው።

ሰልፍ መውጣት የሰላማዊ ትግል አንዱ ስልት ቢሆንም ድምጽ ያለውም ሆነ ድምጽ አልባ መሳሪያ ይዞ መሰለፍ ግን ሰላማዊ አይሆንም። በሰልፍ ሆኖ ድምጽን እያሰሙ ተቃውሞን ማሰማት ተገቢና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን መግለጫ ቢሆንም መንገድ መዝጋት፣ በዚያ መንገድ የተገኘን ተሸከርካሪ ሁሉ ማጥቃትና መቃጠል ግን ተቃውሞውን ሰላማዊነት የጎደለው ያደረገዋል። የሥራ ማቆም አድማ ሰላማዊ ተቃውሞ መግለጫ ቢሆንም ወደ ሥራ የሚሔዱ ሰዎችን በአመጹ የማይተባሩ ናቸው ብሎ ማስፈራራትና ማጥቃት ሲታከልበት ግን ተቃውሞው ሰላማዊ አይሆንም። በጠቅላላው ሰላማዊ ተቃውሞ የሰልፈኞቹንም ሆነ የሌሎችን ወገኖች ሰላም የማይነሳና ለአደጋ የማያጋልጥ መሆን ይገባዋል። ግጭቶችን ያስተናገዱ የአንዳንድ የአካባቢ መሪዎችና ፖለቲከኞች አስተያየት ግን ይህን ዓይነቱን እውነታ የዘነጋ ነበረ። ለመሆኑ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ወደ እምነት ተቋማት፣ ወደ ግል መኖሪያ ቤቶች፣ ወደ ፋብሪካዎችና ወደ ንግድ ስፍራዎች ሲሔዱ ሰልፉ ሰላማዊ ነበረ ተብሎ ይፈረጃልን?
ከጥቅምት 12 ጀምሮ በኦሮምያ የተከሰተውን ነገር ተከትሎ ከአንዳንድ የኦሮምያ ባለሥልጣናት፣ አክቲቪስቶችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አንደበት የተደመጠው ነገር ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖቻችን በዚያ ክልል በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ምን ያህል አስተማማኝ ነው ብሎ ለመጠየቅ የሚገፋፋና በጣም አሳሳቢ ነው። የተከሰተውን ችግር አቅልለውና በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎች ሥራ አስመስለው ለማሳየት ከመሞከራቸውም በላይ ችግሩን ተጠቂዎችና ተጎጅዎች ያስከተሉት የሚያስመስል ውንጀላ ሲሰነዝሩ እንሰማን ነው።

ስለዚህ የሌሎች ክልሎች አመራሮችና የሌሎች ብሔረሰቦች ተወካዮች የመደመር ፊደላቸውን አስቀምጠው በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የየክልላቸውን/የየብሔረሰባቸውን ተወላጆች ዕጣ ፈንታ የመወሰን ታሪካዊ ግዴታ በተጋፈጡበት ጊዜ ላይ መድረስና አለመድረሱን በጽሞናና በማስተዋል ሊስቡበት ይገባል። በባሌ ሮቤ በስብሰባ የታወጀው ሌላውን ሕዝብ የማግለልና የመመንጠር ዘመቻ፣ አንድ የአካበቢው ባለሥልጣን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ላይ ሊሸፋፍኑት እንደሞከሩት የጥቂት ሰዎች ሴራ ዱለታ አይደለም። በኦሮምያ ክልል የሚኖሩ በተለይም በቁጥር ጥቂት ሆነው የሚኖሩ ምስኪን ወገኖች ዕጣ ፈንታ በድንጋይ መወገር፣ በእሳት መቃጠል፣ በስለት መታረድ ወዘተ… ከመሆኑ በፊት ጉዳዩ አስቸኳይ ውሳኔና መፍትሔ ያሻዋል።

ታሪክ ይቅር የማይለው እልቂት በኦሮምያ ክልል በሚገኙ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ላይ ከመድረሱ በፊት የየክልሎቹ አስተዳሮችና የሕዝብ ወኪሎች ፈጥነው ሕዝቦችን የመታደግ ሥራ ሊሠሩ ይገባል። የተለመደው ተፈናቃይ መመለስ፣ በአገር ሽማሌዎች (በአባ ገዳዎች) አማካኝነት እርቅ ማድረግ፣ የሰላም ኮንፈረንስ ማካሔድ፣ የሉሲን አጽም በወጠምሻዎች አሸክሞ ማዞር፣ የኖቤል የሰላም ሽልማት ባያገኘ መመሪያ መስጠት፣ መደመር በተባለ ፍልስፍና ወደ አንድ መድረክ መምጣት ወዘተ… ወዘተ… የሚለው ጨዋታ ይቆይ፤ በጣም ይቆይ።
ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here