የመንግሥት ያለህ!

0
698

በቅርቡ የተከሰተውን ግጭት መነሻ በማድረግ መንግሥት የሕዝብ ደኅነት እና የአገር ሉዓላዊነት መጠበቅ እንዳልቻለ የሚተቹት መላኩ አዳል፥ ችግሮቻችን ለመውጣት፣ የማያዋጣ የእርስበርስ ንትርክና የሐሰት ትርክታችንንና የባሕል ጦርነቱን አቁመን፣ በሳይንስና ምክንያታዊነት የሚመራ መንግሥታዊ ተቋም እንዲኖረን ያስፈልጋል ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

መንግሥት አገርን አገር ከሚያደርጉ አካላት (መሬት ወይም ግዛት፣ ሕዝብና መንግሥት) መካከል አንዱ ነው። መንግሥት ሰዎች ባላቸው ራስ ወዳድነትና በተፈጥሮም ውስጥ ያለው ሀብት ውስንነት ምክንያት ደካሞች በጠንካሮች እንዳይበሉ ለሕዝብ ደኅንነት በሕዝብና የመሪነት ብቃት ባላቸው ሰዎች በተደራጀ ማኅበረ-ፖለቲካ ድርጅት መካከል የሚደረግ ውል ነው። መንግሥት የሕግ አውጭ፤ የአስፈፃሚና ዳኝነት (ፍትሕ አካል) ያሉት ተቋም ነው። ካጠፋ በሕግ ተጠያቂ የሆነ ነፃ ሚዲያን ከሕዝብ የመገናኛ መንገድ አድርጎ ይጠቀማል። መንግሥት የሥርዓት አስከባሪነት ሚና የሚኖረው፣ ብሎም አስተዳደራዊ ቢሮክራሲ፤ የፍትሕ አካል፣ ወታደራዊ ተቋም፣ ርዕዮተ ዓለም አመንጭ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት ያቀፈ አካል ነው።

መንግሥት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና የሚመራበትን ርዕዮተ-ዓለም ከሲቪሉ ኅብረተሰብ ፍላጎት አንጻር ይቀርጻል። በሚያቋቁመው የአስተዳደር ሰንሰለት፣ ፖሊሲዎች የሚተረጎሙበትና የተግባራዊነታቸውም አፈጻጸም የሚቆጣጠርበትና የሚገመግምበት መንገድ ያደራጃል። መንግሥት ከሕዝብ ባገኘው ውክልና መሠረት በራሱ ያለውጭ ኀይል ግፊት የመወሰን አቅም ያለው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ድንጋጌዎችን፣ ሕጎችንና ስምምነቶችን፣ ተቋማትንና ፖሊሲዎችን የአገሩን ሉዓላዊነት እስካልነኩ ድረስ የሚቀበል ነው።

በተጨማሪም መንግሥት ከሌሎች መንግሥታት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ዓለማቀማዊ ግንኙነት መመሥረት የቻለ ማኅበረ ፖለቲካዊ ድርጅት መሆን ይኖርበታል። መንግሥት ከሕዝብ የተዋዋለውን ውል አፍርሶ አምባገነን የመሆን ዕድል አለው። በዚህ ጊዜ የገዥ መደብ ይፈጥራል። መንግሥት የተሰጠውን ኀላፊነት በብቃት ካልተወጣ ደግሞ ደክሟልና የሕዝብን ደህንነት፣ የአገርን ሉዓላዊነትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማስጠበቅ አይችልም። አሁን በኢትዮጵያችን ያለንበት ሁኔታ ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል መንግሥት አለን ለማለት አስቸጋሪ ከሆነበት ደረጃ ደርሰናል። ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ አስተዳደሮች ተግባራቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም። እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉም የጎጡ ንጉሥ ሆነዋል፣ በተለይም ፖለቲከኞችና ባለሚዲያ ሰዎች።

አማራው፣ አገር ሰርቼ የሰጠሁ ነኝና ክብር ይገባኛል፤ ትግሬው፣ ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ነጻ ያወጣኋችሁ ነኝና ክብር ይገባኛል፤ ኦሮሞው፣ ለዘመናት ተጨቁኛለሁ እንዲሁም ወያኔን ከሥልጣን ለማባረር ታግያለሁና ክብር ይገባኛል ይላሉ። ሁላችሁንም ላበረከታችሁት እናማሰግናለን፣ ክብርም ይገባችኋል። ግን ማንኛችሁም ብትሆኑ እንድትገዙን አንፈልግም። ከትናንትና ላይ ቆማችሁ፣ የነጋችንን ተስፋ፣ ህልም፣ ደስታና ሐዘናችንን አትቀሙን። በማይረባ ፖለቲካ ስንባላ፣ በሚሊዮኖች ሥራ አጥ እና ረሃብተኛ እንዲሁም በ51 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ተጭኖብናል፣ ግብጽ እኛን – በኛው ልታጠቃን ትሸርባለች።

ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ እያለች፣ የቀድሞ ካድሬዎች፣ የፖሊስና የደኅንነት አባላት እየሠሩ ያሉት በየክልሉ ካሉ ጥቅማቸው ከተነካባቸው አጋሮች ጋር በመተባበር አገሪቱን ከዘጠኝ መበተን ነው። ለዚህም ሕወሓትና ጋሻ ጃግሬዎቹ የዘረፉትን ብር በመጠቀም እየሠሩ ነው። በትግራይ ክልል ባለሥልጣናትና አክቲቪስቶች የፌዴራል መንግሥቱን በሁሉም ሕዝብ ቅቡልነትን ለማሳጣት እየተሠራ ያለው ሥራ ሕዝቡ በኹለተኛው ዘመነ መሣፍንት የሚኖር አስመስሎታል። ኦነጎቹ ከሕወሓት ጋር በማብር የአገር ማፍረሱን ሥራ ገፍተውበታል። አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች መሥራት ሲኖርባቸው፣ የዶ/ር ዐብይ መንግሥት ግን በአስተዳደር ቦታዎች የኦነግ ካድሬዎችን በመሰግሰግ ላይ ነው።

የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆነው ሰው ከተማዋን የኦሮሞ ለማድረግ ትምህርት በኦሮምኛ፣ ከከተማው ውጭ ለመጡ ኦሮሞዎች የመታዎቂያ፣ የመሬትና የቀበሌ ቤቶችን አድሏል። እነዚህ የኦነግ ካድሬዎች የአገር አንድነት በደማቸው የሌለ፣ ተረኞች መሆናቸው እየተስተዋለ ነው። ይህም የሚያሳየን የመሪው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚናገረውና የሚተገብረው የተለያየ መሆኑን ነው። እናም የእርምት ሥራ አሁኑኑ መደረግ ይኖርበታል። አንዱ የአገሪቱ ችግር በእምነት ሰበብ በራሱ መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ አክራሪ ኦነጎች ናቸውና።

የኦሮሞ ልኂቃን ቀኝ ተገዝተናል፣ የብሔር ጭቆና ደርሶብናል፣ አሁን ደግሞ አከርካራያችን ተሰብሮ ነበር ይላሉ። የእነዚህ ሰዎች የዝቅተኝነት ስሜት በሽታ የበለጠ ያገረሸበት ወቅት ላይ ነን። የሚገርመው ይህን ተራ ንግግርና ተግባር የሚፈጽሙት መሪ መሆናቸው ነው። ይህ የኦሮሞ ልኂቅ፣ አገርን ለመምራት የሚያስፈልገው የሥነ ልቦና ዝግጅት የሌለው፣ ዴሞክራሲ፣ የመንግሥት አስተዳደርና ሥልጣን ምን እንደሆነ ያልተረዳ የተረኞች ስብስብ ነው። በመሆኑም አገራችንን ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳያስገባት ያሰጋል።

የኢትዮጵያ ችግር፣ ከምንም በላይ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሊቀ መንበርነት በሚመሩት በዚሁ የኦሮምያ ክልል ውስጥ ነው። የደኅንነትና የፍትሕ አካላትም የችግሩ አካል ሲሆን አይተናል። ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል መንግሥቱ ፖሊሲዎች የሚጣሱት፣ ግድያው፣ መፈናቀሉ፣ ቤተ ክርስቲያን ማቃጠል፣ አከርካሪያቸውን ሰብረናቸዋል፣ የመንገድ መዝጋት፣ አዲስ አበባ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የመከልከል፣ የሰው መፈናቀል፣ የተረኝነትና የይዋጣልን ፖለቲካ የሚያካሒዱትና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ የማወክ ወንጀልም የሚፈጽሞት ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የኦነግ/ኦህዴድ መሪዎች ናቸው። የጥላቻ መንገድ የሰበኩት፣ መንጋውን ያደራጀው፣ የከተማ ቦታ የሚያስወርረው፣ አሁንም እንደ ፖለቲካ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙበትና ለንብረትና ሕይወት መጥፋት ተጠያቂው የኦዲፒ/ኦነግ አመራር ነው።

እየተደረገ ያለው መግደል እንደ ማስፈራሪያ በወሰዱ፣ ዝም ማለትን እንደ ፍርሃት በቆጠሩ፣ መገንጠልን እንደ አማራጭ በሚያቀነቅኑ፣ ከዝቅተኝነት ስሜት የተነሳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። ሰው ገድሎ የሚጎትተው፣ የሚሰቅለው፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያቃጥለው፣ የሚዘርፈው፣ የሚያፈናቅለው ምን አደረገ? በነገራችን ላይ ልጆቹ የሚያደርጉት ምን እንደሆነ፣ የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት አያውቁም። የሚፈጽመው እንዲያደርግ ለ50 ዓመታት በእነዚሁ ዘረኛ ፖለቲከኞች ሲሰበክ ያደገውንና የሰለጠነበትን ጥላቻ ነው።

እነዚህ ድርጊቶች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይጠበቁ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የቀሩ እንቅስቃሴዎች ናቸው። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ቤተ ክርስቲያንም ለማፍረስ የተቻላቸውን እያደረጉ ነው። የዘመኑ መሪዎች ያልተረዱት ትልቅ ነገር፣ ሃይማኖት ባሕል መሆኑንና እሱን መንካት ኅብረተሰብን ለማፍረስ መሞከር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ ቅድሚያ እራሳቸውን የሚያፈርሳቸው መሆኑን አለመረዳታቸው ነው። በዚህ ከቀጠሉ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲጻፍ፣ እንደ 16ኛው ክፍለ ዘመን ችግር በፈጠረው የኦሮሞ እንቅስቃሴና የማይነኩ የሕዝብ እሴቶችን ለመናድ በመሞከሩ እንደተኮላሸ ይሆናልም።

በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ሁሉንም ነገር ለእኛ ካልሆነ አገር ይፈርሳል፤ የትናንትናው ሁሉ ስህተት ነው በሚሉ የግራ ፖለቲከኞች የሚመራ ፖለቲካ ነው። ይህንንም የሚያደርጉበት ምክንያት አላቸው፣ የመሀከሉና የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች አገር ወዳድና የአገር መፍረስ ጉዳይ ፊታቸው ሲቀርብ የፖለቲካ ጥቅማቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው። ይህን የማጭበርበር ሥራ የሚሠሩት ተወዳድረው የፖለቲካም ሆነ ሌላ ሥልጣን የመያዝ አቅም እንደሌላቸው ስለሚያውቁ ነው። እናም መንጋን አሰልፈው ሥልጣንን መያዝና የሕዝብን ሀብት መቦጥቦጥ ያልማሉ። የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ የአገርን ሰላም ማሳጣትና ሁሉንም የኔ ነው ማለት። ስለዚህም ይህን የፖለቲካ አካሔድ ተረድቶ፣ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግና ወደ ዴሞክራሲና እኩል ተጠቃሚነት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማጠንከር ያስፈልጋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ ኢሕአዴግን አዋህጀ የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲን (ኢብፓ) በመመስረት የመሀሉን ፖለቲካ በመቆጣጠር የአገሪቱን ፖለቲካ በማስተካከል፣ ለልማት የሚሠሩ ፓሪቲዎች እንዲፈጠሩ እሠራለሁ እያለ ነው።

እኛም እየጠየቅን ያለነውና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሆ ብለን የተቀበልነው ለዚሁ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ግራ ዘመም ጽንፈኛ ፖለቲከኞች፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚስተናገዱባትን ነጻነት፣ ፍትሕ እንዲሁም ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ሆና ማየት አይፈልጉም። እንዲያውም ኦዴፓ በተራኛነት እና በቁጥር ብዙ ትርክት ተመስርቶ የኦሮሞ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ካልተመሰረተች በቀር የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ አይመለስም፤ ያ ካልሆነ አገር ይፈርሳል እያሉም ነው፡፡ ለዚያም ነው፣ የኦዴፓን የመደመር እሳቤ እና የኢሕአዴግ ውህደት አምርረው የሚጠሉት፡፡ የኢሕአዴግ ውህድ ፓርቲ ሆኖ መምጣት፣ የመሪዎችንን የፖለቲካ ዥዋዥዌና ይህን ጠባብ ብሔርተኝነት ሊቀንሰው ብሎም ሊያስቀረው ይችል ይሆን? እንደኔ ይህ ውህደት በደንብ ታስቦበትና ጥናትን መሠረት ያደረገ ከሆነ፣ በሕወሓትና በኦዴፓ/ኦነግ ውስጥ የተሰገሰገውን አክራሪ ጠባብ ብሔርተኛ ወንፊት ሆኖ በመለየት፣ አገር አጥፊውን ከአገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ በመለየት የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት መሰረት የሚሆንበት ዕድል ይኖራል ብዬ አምናለሁ።

የጠበቅነው ለዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምስረታ የሚያስፈልጉ ተቋማት በበቂ ሁኔታ እየተገነቡ እና ሕጎች እየወጡ አይደለም። ከኦሮሞ ልኂቃን እየሰማንና እያየን ያለነው ግን የግእዝ ሥልጣኔን በገዳ ስርዓት እንተካለን፣ የሥልጣን ተረኝነት፣ ኢትዮጵያን በኦሮሞ አምሳል እንቀርጻለን፣ የኩሽ ኅብረትን እንመሰርታለን፣ አማራና ትግሬ እንዲሁም ኦርቶዶክስ ተከታዮችን ከሥልጣን ማራቅና ማጥቃት እና ኦሮሞ አቃፊ ነው መፈክርንና ስብከትን ነው።

መታወቅና መሆን ያለበት ግን፣ ኢትዮጵያ ሁሉን አቃፊ እንድትሆን መሥራት እንጂ፣ ኦሮሞ ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራትና ኦሮሞ አቃፊ ነው መፈክርን አይደለም። ኦሮሞ የሚጠበቅበት እንደማነኛውም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት በኢትዮጵያዊነት መዕቀፍ ውስጥ ታቃፊ መሆን ብቻ ነው። የውህደት ፓርቲ ከተመሰረተ አማራ ይጠቀማል የሚል ያለመተማመን ሊገታ የሚገባው ዋናው ችግራችንም ነው። በታሪክ መነታረካችንን አቁመንም፣ ከታሪክ መማር መጀመር ይኖርብናል።

በተጨማሪም፣ በሐሳብ አሽናፊነት የምናምንና የአውንታዊ ነገሮች ደጋፊ ልንሆን ይገባል። ይህ ብቻ ነውና ወደ እድገትና ብልጽግና ሊያደርሰን የሚችለው። የቀረው ደካማ ሒደት ለአገር እድገት ምን ይጠቅማል? ከአለንበት የበለጠ ከመደህየት ውጭ ምን ያመጣል? አማራውስ በሁሉም በኩል በጽንፈኞች ታፍኖም ቢሆን የጋራ የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትኑረን እንጂ ሌላ ምን አለ? ከዚህስ የተሻለ ምርጫ ከየት አለ? እናም ወደ አቅላችሁ፣ ወደሚያዋጣው ተመለሱ፣ ተዋሃዱ፣ በናንተ ፓርቲ ሰዎች አስተዋጽኦም ዴሞክራሲ ይገንባ፣ ሕዝብም የሚመካበት አገር ይኑረው። ነገር ግን ይህን እውን ለማድረግ የሚጠበቅበት ነገር አለ። ይኸውም የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች ለማስደሰት እየሔዱበት ያለው የዥዋዥዌ ፖለቲካ፣ የአገርን አንድነትና ሰላም እያወከ እያየ በተሳሳተ መንገድ የመቀጠሉን ስህተት ለሕዝብ ማመን፣ ይቅርታ መጠየቅና ማስተካከል፤ በባሕል ላይ እየተደረግ ያለውን የማጥፋት ዘመቻ ማስቆም፤ ኬኛንና ከጎረቤት ክልሎች ጋር የሚፈጥሩትን ጠባጫሪነት ማስቆም፤ ለመንግሥታቸውና ለአገሪቱ ሕዝብ ሰላም ቀናኢ በመሆን የኹለተኛውን መንግሥት መዋቅር ማፈራረስ፤ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እና ተገንጣይ ብሔርተኞች ቦታቸውን እንዲይዙ ማድረግ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን ውሕደቱ የውሸትና ለሥልጣን ብቻ ሰለሚሆን እና እየሔደበት ያለው መንገድ ከስህተትነት ስለማይወጣ ሥልጣንን ይዞ መምራት የህልም እንጀራ እንደሚሆን እሙን ነው። እናም ለሥላጣኑም፣ ለአገሪቱም የሚሆነውን ይመርጣል ብለን እንጠብቃለን።

ችግራችን የምንመራበት አስተሳሰብ የዘረኛ ሰዎች ውጤት መሆኑ ነው። የዘር ፖለቲከኞች አደለም ለዘመናዊነት ሊሰሩ የሌላው አገር ሕዝብ ታሪኩን ከፍ ለማድረግ ሲጣጣር እነሱ ያለውን ማሳነስ ይቀናቸዋል። ከጋራ እሴቶቻችን፣ ብሔራዊ ጀግኖቻችንና ምልክቶቻችን ይልቅ ልዩነቶቻችን ላይ ጠንክረው ይሠራሉ። የተሳሳተ የታሪክ ትርክት በመተረክ ሕዝብን ያሳስታሉ። ዋናው ዓላማቸው ሥልጣንን መያዝ ብሎም የራሳቸውን ከርስ መሙላት ብቻ እንጂ የሕዝብን ችግር መፍታትና የአገርን ህልውናም መጠበቅ አይደለምና። የአገርን ማንነት ባገናዘብ መንገድ ርዕዮትን፣ ፖሊሲንና ስትራቴጂን ነድፎ አገርን መምራት የማንችል ደካሞች ነን።

የእኛ ትልቁ ችግራችን ከታሪክ መማር አለመቻላችን ነው። ከድንቁርና፣ ችጋር፣ በሽታና ጦርነት የምንወጣበት፣ የተሻለ ምርታመነት፣ የሀብት ክፍፍልና የአገር አንድነት የሚጠናከርበት መንገድ መፈለግ ሲገባ፣ የአለችውን ትንሽ የአገር ሀብት ለመቀራመት መንገድ መፈለጉ ጎልቶ ታይቷል። አንዱ መንገድ ባለፉት 50 ዓመታት ያየነው የእኛ-እነሱ የዘውጌ ፖለቲካ በመከተል ወደ ሥልጣን መምጣት መቻል ነው። ይህ መንገድ ለትንሽ ሆዳሞች ከርስ መሙላት ሆኖ ካልሆነ፣ ለብዙሃኑ ሕዝብ ከትናንት የባሰ ችግርንና የሰላም መጥፋትን እንጂ ሌላ ያመጣለት የለም።

ለአገር ሰላም ሲባል ከአሁን በፊት የሄድንበትን መንገድ መድገሙ፣ እና አንድን ብሔር ወይም ቡድን ለችግራችን ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ይቁም። የተረኝነቱም ጉዳይ አዋጭ ስላልሆነ በንጭጩ ሊገታ ይገባል። መከባበሩም ሊጠናከር ይገባል። ከችግሮቻችን ለመውጣት፣ የማያዋጣ የእርስበርስ ንትርክና የሐሰት ትርክታችንንና የባህል ጦርነቱን አቁመን፣ በሳይንስና ምክንያታዊነት የሚመራ መንግሥታዊ ተቋም እንዲኖረን ያስፈልጋል። የሁሉም ጎሳ ልኂቃን የጋር ርዕዮት የሚፈጠርበትን መንገድ ማሰብና ሐሳቦችን በሚዲያዎችና በፖለቲካ መድረኮች ማቅረብና ወደ ስምምነት መድረስ ይገባል። እናም እንደ አገር ማድረግ ያለብን ፖለቲካውን አሁኑን ማስተካከልና ኢኮኖሚው ላይ ከመሰረታዊው የግብርና ስራና ሌሎችንም ዘርፎች ጀምሮ መሥራት ነው። እንደ አገር ማድረግ ያለብን ፖለቲካውን አሁኑን ማስተካከልና ኢኮኖሚው ላይ ከመሰረታዊው የግብርና ሥራና ሌሎችንም ዘርፎች ጀምሮ መሥራት ነው። እኛ የምንፈልገው በልተን እንድናድር የሚያደርገን፣ ከዓለም ጭራነት የሚያወጣን፣ የጋራ ርዕዮትና የሚተገበር ሕግና መንግሥታዊ ሥርዓት ነው። ምክንያቱም ሕዝብን ከፖለቲካዊ በደል የሚታደገው የዘውግ ብሔርተኝነት ሳይሆን የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባትና እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ መኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሁሉም ተገፍቶ ወደ ራሱ ብሔር ስለሚገባ ክፍፍሉ የበለጠ ጎልቶ የጋራችንን ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይወስዳት ያሰጋል።

የተዳከመው የታችኛው የአስተዳደር መዋቅር መጠናከር፣ ስርዓት አልበኞችን ለሕግ ማቅረብና የሕግ የበላይነት የሚጠበቅበትን፣ የሕዝብ ሰላም የሚከበርበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ያለዚያ ግን እንደ ውሻ ‘ጃስ’ የሚባል ቡድን ይዞ ሕዝብን እያስፈራሩና እየገደሉ፣ ሰላማዊ የምርጫ ሒደት ብሎም የሥልጣን ሽግግር ይኖራል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። የፕሬስ ሕግን ተከትለው የማይሠሩ የሚዲያ አካላት ተጠያቂ ይሁኑ፣ ሁሉም የመንጋ ቡድኖች ተጠያቂነት ባደራጇቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በኩል ይፈፀም፣ ፌዴራላዊ መንግሥቱ አወቃቀሩ ይስተካከል፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለው አስተዳደር ይስተካከል።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here