የአምቦው ተቃውሞ በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ

0
703

ጥቅምት 11/2012 የተቀሰቀሰው ሁከት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞችና እና በተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ያደረሰውን ጉዳት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ስንከታተል ነበር የቆየነው፤ አልፎም አንዳንዶቻችን የዓይን እማኝ ለመሆንም በቅተናል።

የቆሰለው ቆስሎ፣ የወደመው ወድሞ ፣ የጠፋው ሕይወትም ጠፍቶ አንጻራዊ መረጋጋት በሚታይበት በዚህ ሰሞን ታዲያ፣ የኦዲፒ ላዕላይ አመራሮች ተከፋፍለው ከፍተኛ ግጭት በተከሰተባቸው የኦሮሚያ ከተሞች እንዲሁም በሐረር ከተማ ተገኝተው ሕዝብን አወያይተዋል፤ ከሕዝብ የተሰነዘረውንም ሐሳብ ተቀብለዋል። በተለይ ደግሞ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ በሐረር ያደረጉትን ጉብኝት እያነሱ ሲጥሉ፣ ትችትና ነቀፌታቸውንም ሲያሰሙ ሰንብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ በሐረር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ያመሩት ወደ ምዕራብ ሸዋ አምቦ ከተማ ነበር።

በዚህ የሕዝብ ውይይት ላይ ታዲያ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦቦ ሽመልስንም የሚጨምር ነበርና የኦዲፒ አመራሮች የአምቦ ጉብኝት በቁጥር ሦስት ከፍ እንዲል ሆኖ ነበር። ሐሙስ፣ ጥቅምት 20/2012 ማለዳ በሔሊኮፕተር ወደ አምቦ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባልደረቦቻቸው ከአምቦ ነዋሪዎች ግን የለመዱት ”በጋ ነጋ ዱፍተኒ” (እንኳን በደህና መጡ) የሚል አቀባበል አልነበረም የጠበቃቸው። ሕዝባዊ ውይይቱ ይደረግበታል ወደ ተባለው አዳራሽ አካባቢ ተቃውሞው በርትቶ ”ዳውን ዳውን ዐብይ” የሚሉ መፈክሮችም እንደተሰሙ በርካቶች በፌስ ቡክ እና በትዊተር ገጻቸው ላይ ሲቀባበሉት ተስተውሏል።

በርካቶች ከስፍራው በቀጥታ የተቀረጹ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመመርኮዝ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ወጣቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባልደረቦቻቸው ጋር ለመወያየት ወደ አዳራሽ የሚገባው ሰው እየተመረጠ መሆኑ እና ይህም ትክክለኛውን ማኅበረሰብ ካለማማከሉም በላይ የኦዲፒ ካድሬዎች ብቻ እንዲገቡ ተደርገዋል ሲሉ አስተጋብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሔዱበት አምቦ እንደ አካሔዳቸው የተመለሱ ሲሆን በርካቶች ግን ከነበረው ጠንካራ የተቃውሞ ሰልፍ የተነሳ ለመንቀሳቀስ ተቸግረው እንደነበርም በርካቶች በማኅበራዊ ገጾች መረጃውን ያገኙበትን ምስል በማጋራት ሲያስተጋቡ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here