‹ግጥም በጃዝ› በኂስ መነጽር

0
1188

‹በጃዝ የታጀበ ግጥም› ብለው ይጠሩት ነበር፣ ዛሬ ላይ ግጥም በጃዝ ተብሎ እንደ አንድ ‹ዘውግ› የሚታወቀውን የግጥም አቀራረብ መንገድ። ይህ ‹ዘውግ› መቼና የት፣ እንዴትስ ተጀመረ ብለን ስንጠይቅ፣ ላንግስተን ህዩዝ የተባለ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ አንጋፋ ገጣሚ እንዲሁም በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1920ዎቹ የተነሳውን የጥበብ ዘርፍ እንቅስቃሴ (Harlem Renaissance) መልስ ሆነው እናገኛለን።

በወረደ ትርጉም ‹የሀርለም ህዳሴ› የተባለው እንቅስቃሴ፣ በርካታ የጃዝ ሙዚቃ የሚቀርብባቸው ቤቶች በሚገኝባት በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በምትገኘው ሀርለም የተጀመረ ነው። እንቅስቃሴውም የእውቀትና የባህል ሽግግርን ያለመ ሲሆን፣ ይህም አፍሪካ አሜሪካዊ ጥበባት ላይ ያተኮረ ነበር። ይልቁንም በጊዜው ከነበረው የከፋ ዘረኝነት እና ጥቁሮች ከሚደርስባቸው ተጽእኖ አንጻር፣ ጥቁር አሜሪካዊያን ራሳቸውን የሚረዱበትን ዕይታ መልክ ለማስያዝ ብሎም በጊዜው እየተባባሰ የነበረውን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማሻሻል ያግዛል በሚል እምነት የተደረገ ነው።

ገጣሚው ላንግስተን ታድያ የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነበር። ወትሮም እጅግ የሚወደውን ጃዝ በዚህ እንቅስቃሴ አጋጣሚ ከግጥም ጋር አዋህዶ አቀረበው። ይህንንም ሲያደርግ የአፍሪካ አሜሪካዊያንን ባህል ማጉላትና ቀሪው ዓለም ግጥሙን ከጃዝ ጋር እንዲሰማ ለማስቻል፣ በዛም ከሚነሳው የግጥም ጭብጥ በተጓዳኝ ጃዝ እንደ ጥቁር አሜሪካዊ ሕዝብ ቅርስ እና የፈጠራ ሥራ እውቅና እንዲያገኝ በማሰብና በማመንም ይመስላል።

ታድያ ላንግስተን ብዙ አዳዲስ ጆሮ ማግኘት ችሏል። ተጽእኖ መፍጠር የቻለም ሲሆን፣ የተለየ አፍሪካዊ ቀለም ለመፍጠር የነበረው ፍላጎት የተሳካለት እንደሆነም በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ዘገባዎች ያስረዳሉ። እሱን ተከትሎም ብዙዎች በዛ መንገድ ሄደዋል፤ ግጥም በጃዝም እንደ አንድ ዘውግ ተቆጥሮ ተቀባይነት አግኝቷል። ታሪኩ ከዚህም የሰፋ በመሆኑ፣ አንባቢ ይህን በተመለከተ በግሉ ቅኝት እንዲያደርግ አዲስ ማለዳ ትጋብዛለች።

ግጥም በጃዝ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ‹ግጥም በጃዝ› ተብሎ የሚጠራው ይህ ዘውግ ከተዋወቀና ከተለመደ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። በጉዳዩ ላይ የዘርፉ አጥኚዎች ያደረጉት ጥናት እምብዛም አይታይም። በምን መረዳት እና ዓላማ እንደተዋወቀ፣ በግጥም ላይ ያለው ፋይዳም ሆነ እንደ ዘውግ በምን መልክ ተይዞ እንደቆየ በዝርዝር ሲጠቀስ ብዙም አልተሰማም። ጉዳዩ ለጥናት ብዙ እድሎች ያሉት እንደሆነ አያጠራጥርም።

ይህን ካመላከቱ መድረኮች አንዱ ባሳለፍነው ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 በአዘማን ሆቴል ተካሂዷል። በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ‹ኪነጥበብን ለማሳደግ ኂስን ባህላችን እናድርግ› በሚል መሪ ሐሳብ፣ በግጥም በጃዝ ይዘት፣ ጭብጥ እና አቀራረብ ላይ በቀረበ ኂሳዊ ትንተና መድረክ ላይ ነው ጉዳዩ የተነሳው።

በመድረኩም የሻው ተሰማ (የኮተቤው) ኂሳዊ ምልከታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ የተለያዩ ሐሳቦች በጉዳዩ ላይ ተነስተው ውይይት ተደርጓል። ግጥሞች ቀርበዋል፣ መነባንብ ተደምጧል።

የሻው ተሰማ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በተለያዩ መድረኮች የቀረቡ የጃዝ ግጥሞችን በመለየት ከተለያየ አንጻር አስቃኝተዋል። በዚህም የግጥሞቹን ባህርያት፣ አንድምታቸውን፣ የገጣሚያኑን አቀራረብ፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ከሙዚቃው ጋር ያላቸውን ጥምረትና ውህደት፣ ክዋኔያቸውን እንዲሁም ያሉና የታዩ ክፍተቶችን አንስተዋል።

በዛም ካነሷቸው ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን እናውሳ።

የግጥሞቹን ባህርያት በተመለከተ ብዙዎቹ የጋራ የሆነ የሚያመሳስል መልክ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህም በግጥም በጃዝ መድረኮች የሚቀርቡ ግጥሞች በአብዛኛው በወል ቤት የተገጠሙ መሆናቸው አንዱ ነው። ከተለመደው የወል ቤት ወጣ ብለው የሚያቀርቡ እምብዛም አይታዩም።

ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር ብዙዎቹ የተሳካላቸው ሲሆኑ፣ በተጓዳኝ ግን በብዙዎቹ የሚቀርቡት የግጥም ጭብጦች፣ የመነሻ ሐሳባቸው ‹በአየር ላይ ያሉ ስሜቶች ናቸው› ሲሉ የሻው ገልጸዋቸዋል። አንድምታቸውን በሚመለከትም፣ ከቅርጽ እና ከአገላለጽ አንጻር በግጥም ላይ እመርታ ያሳዩ ሲሆኑ፣ ከመጠን አኳያ ዘለግ ያሉ ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሻው እንዳስቀመጡት፣ ከአቀራረባቸው ሳቢነት የተነሳ የግጥሞቹ ርዝመት ለአድማጭ ላይሰማ ወይም ላይቆረቁር ይችላል። ሳይታወቀውም ሳይሰለች ግጥሞቹን ለመስማት እንደሚያስችለው ጠቅሰዋል።

ከጭብጥ አኳያ አብዛኞቹ ግጥሞች ቀቢጸ ተስፋ የሚታይባቸው፣ ጨለምተኝነት የሚስተዋልባቸው መሆኑ ተነስቷል። ተስፋን የሚያሳዩ ቢሆኑ እንኳ ከበዛ ጨለማና ምሬት የሚነሱ ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን ከአገር ፍቅር እና ከመቆጨት ስሜት የሚያያዙ መሆናቸው እንደሚያስታውቅ ነው የሻው ያወሱት።

የግጥሞቹ አቀራረብም በጃዝ ከመሆኑ በተጓዳኝ በአብዛኛው ልዩ ክዋኔም ያለው ነው። በሙዚቃ ከመታጀቡ አንጻር ውዝዋዜን ያካተተ፣ አንዳንዴም ቀረርቶና ፉከራ የታከለበት ነው። አቅራቢዎችም ወረቀት ሳይዙ በቃላቸው ማቅረባቸው የተለመደ ነው። ከዛም በተጓዳኝ ሙዚቃውን እና የግጥሙን ጭብጥ ለማገናኘት የሚጥሩም አሉ። ባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ለግጥሙ ዋና ግብዓት ሲሆኑ፣ ስዕላትና ባህላዊ ቁሳቁሶች፣ የብርሃን ጥበባትም የማበልጸጊያ ግብዓቶች ናቸው ሲሉ የሻው ዘርዝረዋል።

በእነዚህ የግጥም ይዘቶችና አቀራረቡም ላይ የሚስተዋሉ የጎደሉ ወይም የሚቀሩ ጉዳዮችን ‹የሚስዋሉ ቀርነቶች› ብለው አስቀምጠዋል። ከነዛም መካከል ጨለምተኛነት የመብዛቱ ነገር አንደኛው ነው። ከዛም አልፎ የጥንቱን ብቻ ማድነቅና ነባራዊውን ሁሉ መኮነን እንደሚስተዋል፣ ይህም ተገቢ እንዳልሆነ መክረዋል። ሚዛናዊ መሆን እንደሚገባና መጥፎ ከሚመስሉ ኹኔታዎችም ውስጥ በጎ ነገር ለማመላከት መጣር ያሻል ብለዋል።

ከዛም ባለፈ የገጣሚዎቹ የስሜት ቅኝት ምስስሎች እንደሚስተዋል ጠቁመዋል። መነሻ ጭብጣቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ በውስጣቸው የሚገኘው ፍሬ ሐሳብ ከዓመታት በኋላ ቢታይ ይህ ነው የሚባል ላይሆን እንደሚችልም በመጥቀስ፣ ያንንም ‹ነዲዳቸው የሚንበለበል ነገር ግን ፍህም የማይወርዳቸው› ሲሉ ገልጸዉታል።

አዲስ ዕይታዎችን ማቅረብ ብሎም ርዕሰ ጉዳይ መረጣ ላይ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው። እንዲሁም ግጥሞቹ በሙዚቃ ወይም በጃዝ በሚቀርቡበት ጊዜ ከሙዚቃው ጋር መዋሃዳቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ይህ የሚጠበቅ ውህደት ብዙ ጊዜ ተፈጥሮ እንደማይታይና ሳይጣጣም ሲቀር እንደሚስተዋል የሻው ሳያነሱ አልቀሩም።

በመደምደሚያቸውም ግጥም በጃዝ የግጥምን ጥበብ እድገት እንደሚያግዝ፣ በጃዝ መቅረቡም የተደራሲዎች ግጥምን የማጣጣም አቅም እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል። መጽሐፍ ለማሳተም የሚቸገሩ ገጣሚዎች ሥራዎቻቸውን ለአድማጭ እንዲያቀርቡ እድል እንዲያገኙ አስችሏል። በመድረኮቹ የሚታዩ ግብዓቶችም የሚቀርቡ ግጥሞች እንዲወደዱና እንዲጎሉ ያደርጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ብዙውን ጊዜ አከራካሪ ሆኖ የሚነሳው ‹ግጥም የራሱ ዜማ አለው። በሙዚቃ (በጃዝ) ሊታጀብ አይገባም› የሚለው ሙግትም በዚህ መድረክ ተነስቶ ነበር። ይህን በሚመለከትም ግጥም በጃዝ መቅረቡ የግጥምን ጥበብ አሳነሰው ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም፣ የሻው በዚህ ዕይታ እንደማይስማሙ አስረድተዋል። ‹‹በእኔ ዕይታ ጥበባት ሲዋሃዱ ወይም ሲዳቀሉ መጣጣም ከቻሉና ያም የሰመረ ከሆነ፣ አንዱ አንዱን ያበለጽገዋል እንጂ አያጠፋውም›› ብለዋል።

በውይይቱም ከመድረኩ ጎልተው የተሰሙ አስተያየቶች ይህንኑ ግጥም ራሱን የቻለ ሆኖ ሳለ በሙዚቃ መታጀቡ ስለምን ነው የሚለው ዕይታ አንዱና ዋናው ነው። ‹ግጥም በሙዚቃው ውስጥ ተውጧል!› ‹መጽሐፍ ከመግዛት ይልቅ እንዲህ ባሉ መድረኮች ላይ መታደምን የሚመርጡ ሰዎች ተበራክተዋል!› ‹ጃዝ የራሱ የሆነ ባህርያት ያለው በመሆኑ በራሱ ሊተዉ ይገባል!› ‹ግጥሞቹ በጣም ረዛዘሙ!› ‹ግጥሙን ነው ጃዙን፣ የትኛውን ነው የምንሰማው?› ‹ግጥሙን ለመስማት ይህ ይፈትነናል› የሚሉና መሰል ሐሳቦች ከታዳሚዎች ከተሰጡና ከተነሱ መካከል ናቸው።

የሻው ይህን በተመለከተ ዕይታቸውን ሲያካፍሉ፣ ሰው ከወርቅ የሚበልጥ ፍጡር ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን በወርቅ ይደምቃል። ግጥምን በጃዝ የሚለውም እንደዛው ነው ሲሉ አስረድተዋል። ምሳሌ እስከ ፍጻሜ አያጸናምና፣ ባቀረቡት ምሳሌ ዋናው ግጥም በሆነበት አውድ ላይ የሚታይ ነው ብለዋል። የግጥሞቹ መርዘምም እንደ አድማጩ ፍላጎትና ምርጫ የሚወሰን መሆኑን አንስተዋል።

ከመድረኩ መልስ ለዘርፉ ባለሞያዎችና ለታዳሚዎች ኀሠሣ ይሆን ዘንድ፣ ጃዝ የሙዚቃ ሥልት ምን መልክ አለው፣ አሁንስ ምን ላይ ነው? ግጥም በጃዝ ተብለው የሚቀርቡ ሥራዎች ግጥሙን ከሙዚቃው አጣጥመዋል ወይ? አድማጮችሽ ሙዚቃውን ነው ወይስ ግጥሙን የሚያደምጡት? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች በይደር የቆዩ ናቸው። ሰፊ ጥናት የሚፈልጉ መሆናቸውም እሙን ነው።

ስለመድረኩ

የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጀው ይህ የኂሳዊ መድረክ፣ በሥነጽሑፉ ዘርፍ ሦስተኛውና ለ2015 የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ቀደም በአፈወርቅ ገብረኢየሱስ (ጦቢያ) እንዲሁም በደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ሥራዎች ዙሪያ የቀረቡ የኂስ መድረኮች ነበሩ። ከዛም ባለፈ በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በኪነሕንጻና መሰል የጥበብ ዘርፎች ዙሪያ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መድረኮች ተካሂደዋል።

በቢሮው የኪነጥበባት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰርጸ ፍሬስብሐት በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የሥነ ጥበብ እድገት በከያኒዎች ወይም በፈጠራ ባለሞያዎች ብቻ የሚመጣ አይደለም። ይልቁንም የሥነጥበባዊ ጉዞ አቅጣጫ፣ ልማት ጥፋቱን፣ ረብ ክስረቱን የሚጠቁመው ኂሳዊ ኃይል ሊከተለው ይገባል።›› ብለዋል።

ይህም ሥራዎቹን አትቶ፣ ተርጉሞ፣ አንድምታ አበጅቶ ኢ-መዋቲ የሚያደርጋቸው ኂስ ነው ያሉት ሰርጸ፣ ኂስ ነቀፋም ሆነ ውዳሴ አለመሆኑን ደጋግመው አንስተዋል። ነገር ግን፣ በኹለቱ መካከል ያለ ሦስተኛ መስመር እንደሆነ ጠቁመዋል።

አንድ የጥበብ ባለሞያ በሕዝብ ልብ ውስጥ ሙሉ ሥልጣን ማግኘት የሚፈልግ ከመሆኑ አንጻር፣ በኀያሲዎች የሚነሱ ነጥቦች ምንም እንኳ ምክንያታዊ ቢሆኑ፣ የባለሞያን መሻት እንደሚያደናቅፉ የ‹ጥርጣሬ አቧራዎች› ይታያሉ። በዚህም የተነሳ በኹለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ጠብ የማያጣው እንደሆነ ሰርጸ አንስተዋል። ሆኖም ግን በኀያሲ የሚነሱ ነጥቦች እውቀትን የሚጨምሩ በመሆናቸው፣ ለሥነጥበብ እድገት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው በአጽንዖት ያመላከቱት።

በመድረኩ መቋጫ ላይ ሐሳባቸውን ያነሱት የቢሮው ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ በቀጣይ ጥናት ማድረግ፣ መወያየትና የግጥም በጃዝን መልክ በሚገባ ማወቅ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ቢሮው የሚሠራው ቀጣይ ሥራ እንዳለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲሠሩበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here