ተጠርጣሪዎችን በማሸሽ የተጠረጠሩት ታሰሩ

0
556

ከሥራ ቀን ውጪ ጸሐፊያቸውን በማዘዝ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን ሜጀር ጀኔራል ሐድጉን ሰነድ አሽሽተዋል በሚል የተጠረጠሩት የሜቴክ የሰው ሀብት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ሰጠኝ ካሣዬ ኅዳር 10 ቀን ፍርድ ቤት ቀርበው፣ በመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው የተወሰነ ሲሆን ኅዳር 13 በዋለው ችሎት ፖሊስ በጠየቀው የዐሥራ አራት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ዙሪያ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
በዕለቱ ፖሊስ ግለሰቡ የገንዘብ አቅም የለኝም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ያቁምልኝ ማለታቸውን የሚያስተባብል እና ተጠርጣሪው የተከማቸ ሀብት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለው ተናግሯል፡፡ ‹‹በዚም በመንግሥት የቆሙላቸው ጠበቆች እንዲነሱ እና ፍርድ ቤቱን የማታለል ወንጀል ሰርተዋል›› ተብሎ እንዲመዘገብላቸው መርማሪ ፖሊሶቹ ጠይቀዋል፡፡
ተጠርጣሪው በበኩላቸው ፖሊስ ገንዘብ አላቸው ብሎ በማስረጃነት ያቀረበው የባንክ ሒሳብ መታገዱ እና አውጥተዋል የተባለውንም ገንዘብ ለሌላ ሰው መላካቸውን አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የባንክ ሒሳባቸው መታገዱ እና ያወጡትን ብር ለሌላ ሰው መላካቸው እንዲጣራ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ፖሊስ በጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ዙሪያ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ለኅዳር 20/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በሙስና እና በሰብኣዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩትን የደኅነነት መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑትን የተስፋዬ ገብረፃዲቅን ሰነድ አሽሽተዋል በሚል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ፊሊሞን ግርማይ እና ቴዎድሮስ ያዕቆብ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ የደኅነነት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሐሺም ቶፊቅ (ዶ/ር) ወደ መቀሌ በማሸሽ እና የጦር መሣሪያ በመደበቅ የተጠረጠሩት ደግሞ ባለቤታቸው ዊዳድ አሕመድ እና ሰሚር አሕመድ ናቸው፡፡
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጉዳዩን ለመመርመር የዐሥራ አራት ቀን ጊዜ ጠይቋል። የተጠርጣሪዎቹ ተከላካይ ጠበቆች ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን እና የአምስት ቀን የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱን አስታውሰው፣ በተመሳሳይ ጉዳይ በዚህ ችሎት መዝገብ ተከፍቶ ተጨማሪ ዐሥራ አራት ቀን መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙ ዐሥራ ሦስት ቀን እንደሞላቸው በመግለጽ እስካሁን በነበረው ጊዜ ፖሊስ ምርመራውን ማጠናቀቅ ይችል ነበር ብለዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ሰነዶችን እና ተጠርጣሪዎችን አሽሽተው ነበር፤ ከገቢ በላይ ሀብት በማካበት ወንጀልም እንደሚጠረጥራቸው እና ማስረጃ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም ቀደም ሲል በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡበትን መዝገብ ቁጥር 225261 ተያይዞ ኅዳር 14 እንዲቀርብ አዞ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ሰኞ፣ ኅዳር 17/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here