የካሾግጂ ግድያ የአሜሪካና ሳዑዲ ግንኙነትን አያሻክርም ተባለ

0
1097

• የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳዑዲ አረቢያ ያላቸውን ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቁመዋል

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ፣ ኅዳር 11/2011 በሰጡት ይፋዊ ምላሽ አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል። ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የትራምፕ መግለጫ የአሜሪካው የደኅንነት መስሪያ ቤት ሲ አይ ኤ ከግድያው ጀርባ ትዕዛዝ በመስጠት የሳዑው አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን መሳተፋቸውን ለፕሬዘዳንት ትራምፕን ማሳወቁን ተከትሎ መሆኑ ታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን በቅርቡ ሕይወቱ ስላለፈው የካሾግጂ አሟሟት የማወቃቸው ዕድል ከፍተኛ ነው ብለዋል። አክለውም የጋዜጠኛው መገደል አሳዛኝና የሚወገዝ ቢሆንም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደገውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ግን በምንም መልኩ ሊያበላሽ አይችልም ብለዋል። «የእኛ ግንኙነት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ነው» ሲሉ ትራምፕ ገልጸዋል።
ይህም የዓለም አቀፉን የሕግ ልዕልና እና ተጠያቂነት ወደጎን በመግፋት መሆኑ ከብዙዎች ተቃውሞ እንዲሰማ ቢያደርግም ትራምፕ ግን ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ማለታቸው ታውቋል። ባለፈው እሑድም እንዲሁ ከቱርክ የቀረበላቸውንና የጋዜጠኛውን አገዳደል ያመላክታል የተባለለትን ድምጽ ትራምፕ ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት የንግድ ግንኙነት በዋዛ አቋርጣ ለቻይናና ለሩሲያ ሲሳይ ልትዳርገው አይገባም ያሉት ትራምፕ ‹‹ ይሄ እጅግ በጣም ቀላለ ስሌት ነው። አሜሪካንን በድጋሜ ታላቅ የማድረግ ጉዳይ›› ሲሉ ለጋዜጠኞች በጉዳዩ ላይ የያዙትን ቁርጥ ያለ አቋም ገልጸዋል።
የቴኔሲው ሪፐብሊካን ሴናተርና የውጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢው ቦብ በርከር የፕሬዘዳንት ትራምፕን መግለጫ ተከትሎ ዋይት ሃውስ የአልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ይሰራል ብለው እንዳልጠበቁ በቲውተር ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።
ጀማል ካሾግጂ ማነው?
የ59 ዓመቱ ጎልማሳ ጀማል ካሾግጂ በአረቡ ዓለም ዝናው የናኘ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆን በሳኡዲ አረቢያ ታዋቂ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ ሰርቷል፡፡ በኋላም የሳኡዲ ሹማምንት ከፍተኛ አማካሪ በመሆን አገሩን አገልግሏል፡፡ ከመገደሉ አንድ ዓመት በፊት ግን ለሳኡዲ አረቢያ መንግሥት ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ በማቋረጥ ኑሮውን በስደት አሜሪካ ላይ አድርጓል፡፡
በአሜሪካ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ በመሆን ሙያውን የቀጠለው ካአሾጊ በሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጨቋኝ አገዛዝ በተለይ ደግሞ ራሳቸውን ‹የለውጥ ሐዋሪያ› አድረገው በሚቆጥሩትንና ተቃዋሚና ተቀናቃኞቻቸውን በማሰር በሚታወቁት የሳኡዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡
የሳዑዲ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ገብቶ ሕይወቱ ማለፉ ከተረጋገጠ ሳምንታት አልፈዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here