ኢንቨስትመንት ባንክ ሴቶችን ለማበረታት አንድ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ፈቀደ

0
636

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ወደ አንድ ቢሊየን ብር የሚጠጋ፣ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ሴቶች በኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ለመጨመር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ወሰነ። ብድሩ መንግሥት ሴቶች በኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተለያየ ተግባራትን እያከናወነ በሚገኝበት ወቅት መሆኑ ሚናውን ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።
የባንኩን ወሳኔውን ተከትሎ ባለፈው ሐሙስ በሸራተን አዲስ በተደረገ ዝግጅት በፋይናንስ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዘዳንት ወርነር ሆይነር (ዶ/ር) መካከል ተፈርሟል። ብድሩ ሴቶች በግሉ ዘርፍ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመርና አገሪቷ ከዛሬ አምስት ዓመታት አንስቶ እየተገበረች ላለችው ለሴቶች ሥራ ፈጠራ ልማት መርሐ ግብር ይውላል ተብሏል።
የተገኘው የፋይናንስ አቅርቦት ለሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች የብድርና የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ፣ ስለ ኢንዱስትሪ ዘርፍና ሌሎች የአኗኗር ዘይቤ ሥልጠናዎች ለመስጠት ይውላል። በተጨማሪም ብድሩ በገጠርና በከተሞች በሴቶች ለተያዙ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በተለይም ማስያዣ በማጣትና በሚጠይቁት ብድር አነስተኛ መሆን ምክንያት በንግድ ባንኮች ያልተካተቱ ሴቶችን ለመደገፍ ብድሩ ይውላል ሲል የኢንቨስትመንት ባንኩ ገልጿል።
በሌላ በኩል መንግሥት ለዓመታት የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር ብዙ ተግባራትን ቢያከናውንም በኢኮኖሚ ያላቸውን ሚና ባቀደው መልክ ለመጨመር አልቻለም። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች አሁንም ከ70 በመቶ በላይ በሴቶች የተያዙ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ ያሳያል። ለዚህ እንደምክንያት የሚገለጸው ንብረቶች በወንዶች መያዛቸውና ሴቶች በቤት ሥራዎች መጠመዳቸው ነው።
ይህንን ችግር መንግሥት እንደተረዳ የጠቆሙት የፋይናንስ ሚኒስትሩ አሕመድ የአውሮፓ ኢቨስትመንት ባንክ የሰጠው ብድር የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የሴቶች ተጠቃሚነት ከመደገፉም በላይ የፋይናንስ እጥረቱን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የባንኩ ፕሬዘዳንት ወርነር በበኩላቸው እንደገለጹት ብድሩ የሴቶችን ችግር በመፍታት ድህነትን ከአገሪቷ ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። “የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋፋትና በሴቶች የተያዙ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ብድሩ ሴቶች በኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ብለዋል። በተጨማሪም ሁሉን ዐቀፍ ፕሮጀክት ላይ መሥራት ባንኩ እንደሚፈልግ የገለጹት ወርነር ኢትዮጵያ ለፆታ እኩልነት እየሠራች መሆኑን ጠቁመዋል። “ባንኩ የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶች አቅም እንዲጎለብት የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የዛሬ ብድሩም የድጋፉ አካል መሆኑን አመልክተዋል። በቅርቡ መንግሥት በካቢኔ መዋቅር ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ማድረጉ ለፆታ እኩልነት ቁርጠኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ከወር በፊት የፓርላማ አባላት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚኒስትሮችን ሹመት ሲያፀድቁ ከ20 ካቢኔ አባላት ሴቶች ግማሽ ያህሉን ሹመቶች አግኝተው እንደነበር አይዘነጋም።
ባለፈው ሳምንት መንግሥት ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በተጨማሪ ሌላም የፋይናንስ ድጋፍ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ማግኘት ችሏል። የልማት ባንኩ የ123 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ያፀደቀ ሲሆን ለተያዘው ዓመትና ለሚቀጥለው ዓመት ለአገሪቷ መሠረታው የአገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም እንደሚውል ታውቋል። ድጋፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነውን የሰው ሀብት ልማትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታን ለማፋጠንና ዘላቂ ለማድረግ ያግዛል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here