የመርፌ አወጋግ

0
1510

ሠሞኑን የሕዝቡ መነጋገሪያ የነበረው የድርድሩ ወሬ እየተጠበቀ በነበረበት እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለጉብኝት ጋሞ ተገኝተው እንደነበረ ሲዘገብ ነበር። የእርሳቸውን ጉብኝት ተከትሎ ከወጡ ዘገባዎች መካከል በምስል የተደገፈውና ከብትን መርፌ ሲወጉ የነበሩበት ምስል ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በየመስኩ እየተገኙ ጉብኝት ሲያደርጉ፣ ጦር ሜዳም ተገኝተው ሲያዋጉ፣ መዝናኛ ማዕከላት እየተገኙ ሲዝናኑና ኳስ ሲጫወቱ እንዲሁም ሰርግ ድግስ ላይ ሲታደሙና ሌላም ሌላም የቀደሙ መሪዎች ሲያደርጉ ያልታዩትን በርካታ ተግባራት ሲያከናውኑ ታይተዋል።

የሠሞኑ ለየት የሚያደርገው ባለሙያ መሆን የሚጠይቅና ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር መፈጸማቸው ነው በሚል በርካታ አስተያየት በምስሉ ዙሪያ ተሰንዝሯል። ቀዶ ጥገና እንኳን አልሆነ እያሉ ለማፌዝ የሞከሩ ቢኖሩም፣ የእንስሳት መብት ይከበር በማለት በፍላጎት ብቻ የሚተገበር አለመሆኑን የተናገሩም ነበሩ።

“ዶክተር የሚባሉት በእንስሳት ሕክምና ነው እንዴ” ብለው ለቀልድ ይሁን ለማወቅ የጠየቁም ነበሩ። በምስሉ ዙሪያ የተሰነዘሩ በርካታ የፌዝም ቁምነገርም አስተያየቶች ነበሩ። ከመርፌ አያያዛቸው ጀምሮ፣ የከብቱ ደኅንነትና አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይሆን ያሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በደርግ ዘመነ መንግሥት የአገር መሪ የነበሩት ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደምዕራብ ኢትዮጵያ ለሩዝ የተዘጋጀ ማሳን ሊጎበኙ ሄዱ በተባለበት ሰሞን የተወራ ተመሳሳይ ቀልድ ነበር። ከሄሊኮፍተር እንደወረዱ ወደማሳው በቀጥታ በማምራት አፈሩን ቆንጠር አድርገው በመቅመስ ለሩዝ ይሆናል አሉ ተብሎ የመሪዎችን ሁለገብነት ለማሳያት ተሞክሮ ነበር።

የአፍሪካ መሪዎች የተለያዩ ባለሙያዎች የሚለብሱትን ልብስ መልበስ እንደሚወዱ ይነገራል። የወታደር የደንብ ልብስ ዋና መገለጫቸው ሲሆን፣ የትራፊክ፣ የሐኪም፣ የአውሮፕላን አብራሪ፣ የሃይማኖት መሪ እንዲሁም የውጭ አገራትን ፋሽኖችና የተለያዩ ባሕላዊ ልብሶችን በቀን ኹለት ሦስቴም ቢሆን እየቀያየሩ መልበሳቸው የተለመደ ነው የሚሉ አሉ።

ሙያው ሳይኖራቸው እንደባለሙያ ለብሰው ውሳኔ ሲሰጡ መታየታቸው ባይገርምም፣ የባለሙያውን ተግባር ያለእውቀት ወስደው አውሮፕላን ላብርር ወይም ላክም፣ አልያም ልስበክ ሲሉ ቢያንስ በአደባባይ እንደማይታዩ ምስክር መቁጠር አያስፈልግም።

የሠሞኑ የከብት መውጊያው መርፌውን ማን እንዳቀበላቸው ወይም እሳቸው ልውጋ ብለው ስለመጠየቃቸው ምንም የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። ቢያንስ ጥጥና አልኮል ሳይዙ ምነው በግላጭ ወጓት ያሉም ነበሩ። ተወጊዋ ላም ትሁን በሬ ባይለይም፣ ሌሎችንም ሳይወጉ እንዳልቀሩ የገመቱ አሉ።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here