የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ማስቆጠሩን ተከትሎ ስለሂደቱ ብዙ እየተባለ ነው፡፡ ከአነሳሱ ጀምሮ እስከ ሦስተኛ ዙር ስለነበረውና አሁንም ስላለው መልክ በርካቶች የየግላቸውን አስተያየት ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም በርካታ ንግግሮች በተፋላሚዎቹ ወገኖች በኩል ስለመደረጉ ቢነገርም፣ ሠሞኑን በደቡብ አፍሪካ እንደተካሄደው ተስፋ የተጣለበት አልነበረም፡፡ የድርድሩን ውጤት ነገር ፣ በግጭቱ ውስጥ ስላሉ ወገኖች ተሳትፎ እንዲሁም ከቀደሙ ታሪኮች መማር ስለመቻል አለመቻሉ የጦርነቱን ዳራ ከአጠቃላይ የሰሜኑ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር በማነጻጸር ሂደቱን ከቀጣይ ትንበያዎች ጋር አዋህደው ግዛቸው አበበ በጽሑፋቸው እንዲህ ከትበውታል፡፡
ጥቅምት 23 እና 24 የብልጽግና መንግስት መገናኛ ብዙሐን ሰሜን ዕዝን አንረሳውም የሚል ፕሮግራም በሰፊው እያስተናገዱ ሲሆን፣ የሕወሓት ድምጽ የሆኑት ትግራይ ቲቪና ድምጺ ወያነ ደግሞ ጀኖሳይዳዊ ጦርነት በትግራይ ሕዝብ ላይ የተከፈተበትን ሰኔ 24ን እንዘክረው የሚሉ ፕሮግራሞችን እያስተናገዱ ውለዋል። ሰኔ 24/2013 በሰሜን ዕዝ ካምፖች ላይ የተጀመረው አሰቃቂ የጠላትነት ስራ በመላ ትግራይ፣ በአፋር፣ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በወልቃይትና በጠለምት አካባቢዎች በምስኪን ጎጃዋ ውስጥ እስከተደፈረችውና ሕይወቷን እሰካጣችው ሕጻን ኢትዮጵያዊት ድረስ ማንንም ሳይምር ስቃይና ሰቆቃን እየጋ ወደ ሁለት ዓመት ቀጥሏል።
በዐስር ሽህ ወይም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖች ጠላቴ-ጠላቴ ተባብለው በጦር ሜዳዎች ወድቀዋል ተሰንክለዋል፣ የጦር መሳሪያ ያልያዙ ምስኪኖችም በየፈሰራቸው ሆነ ተብሎ ተረሽነዋል ወይም በበራሪ ጥይት ተገድለዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ የቢሊዮኖች ብር ዋጋ ያለው የግለሰቦችና የመንግስት ንብረት ተዘርፏል ወድሟል፣ ብዙዎች ክብራቸውን ለሚያሳጣ ጥቃት ተጋልጠዋል፣ ከብቶች እንኳ አሳዛኝ ሰለባ ከመሆን ያላመለጡበት ጦርነት ሰፋ ባለ የሰሜን ኢትዮጵያ ምድር ተካሂዷል።
ይህ በከፍተኛ ደረጃ ደም የሚያፋስስ ጦርነት በመቀጠል ላይ እንዳለ ‘ውይይት’ የመካሄዱ ወሬ እየተሰማ ሰንብቷል። ውይይቱ የተካሄደው በብልጽግና መንግስትና የብልጽግና ፓርላማ አሸባሪ ብሎ በፈረጀው በሕወሓት መካከል ነው። ብልጽግና ትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት መንግስት የለም የሚል አቋም በመያዙ በውይይቱ የተካፈለው ሕወሓት የትግራይን ህዝብ ወክሏል ሊባል አይችልም። የብልጽግና መንግስት ሕወሓትን እየደመሰሰውና ትግራይን እየተቆጣጠረ መሆኑን መናገሩን ሳያቋርጥ፣ ሕወሓትም ትግራይ የወራሪዎች መቀበሪያ እየሆነች መሆኑን መናገሩን ሳይተው ነው ድርድር የቀጠለው።
ደቡብ አፍሪካ ላይ የተጀመረው ድርድር እንደታሰበው በሥድስት ቀናት የሚቋጭ ሳይሆን ቀርቶ የመቀጠሉ ወሩ እየተሰማ ነበረ። ለተጨማሪ ሦሥት ቀናት ድርድሩ እንደቀጠለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርድሩ የውጭ ጣልቃ ገብነት የበዛበት መሆኑን ጠቅሰው ምሬት አሰሙ። በዐስረኛው ቀን ግን ከአደራዳሪዎች በኩል ብዙዎች ያልጠበቁበት ነገር ተሰማ። በድርድሩ ስምምነት ላይ ተደረሰ ከማለት ይልቅ ሕወሓት እጅ ሰጠ የሚያስብል መግለጫ በኡሁሩ ኬንያታና በሌሎች አደራዳሪዎች ታጅበው በቀረቡት በአባሳንጆ በኩል ይፋ ተደረገ። የሕወሐቱ አቶ ጌታቸው ረዳ አርኪ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰው ስምምነቱን ለማሰናከል የሚጥሩ ወገኖች እጆቻቸውን እንዲሰበስቡና ሰላም ወዳድ ወገኖች ሁሉ ለስምምነቱ ሙሉ ስኬት ትብራቸውን ያደርጉ ዘንድ ሲማጸኑ ተሰምተዋል።
ይህን የስምምነት ዜና ይፋ መሆን ተከትሎ የተከሰተ አንድ አስገራሚ ነገር አለ። ዲጂታል ወያነ የሚባሉት የሕወሓት አክቲቪስቶችና ሌሎች ወደ ሕወሓት የሚያጋድሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችና መገናና ብዙሐን ሁሉ እስከ ጫፍ ሰዓት ድረስ ሲያስተጋቡት የነበረውን የትግራይ ጦር በመረጠው ቦታ ጠላቶቹን እየደመሰሰ ነው የሚል ያላባራ ወሬና የትየለሌ የኢትዮጵያና የኤርትራ ክፍለ ጦሮች መደምስ ወሬ እርግፍ አድርገው ትተው እንኳን ደስ አለን የሚል መልዕክት አስተጋብተዋል። የሕወሓት መገናኛ ብዙሐንም ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም በደቡብ አፍሪካው የ10 ቀናት ውይይት ጄኖሳይዳዊውን ጦርነት ለማቆም ስምምነት ላይ ተደረሰ የሚል ዜና አሰምተዋል።
ይህ ዜና በትግራይ ቲቪ እና በድምጺ ወያነ የዩትዩብ መስኮት መዘርጋቱን ተከትሎ እንኳን ደስ አለን፣ እውነት ያድርገው፣ ፉከራ እናቁምና ለተግባራዊነቱ ሁላችንም እንስራ፣ የትግራይ ሕዝብ በጥይትና በረሀብ መሞቱ ሊያበቃ ነው ወዘተ…. የሚሉ የደስታ መግለጫ አስተያየት መስጫውን አጨናንቆት ታይቷል።
የስምምነቱን ይፋ መሆን ተከትሎም ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድም የሰላም መድረኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አደራዳሪዎችና ለሌሎች ወገኖች ምስጋና አቅርበው የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት የሚባለውን ይህን የድርድር ውጤት መግለጫ ተከትሎ አሜሪካንና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ብዙዎች የደስታ መልዕክት አስተጋብተዋል። የተባበሩት መንግስታት መሪ የሆኑት እንቶኒዮ ጉተሬዝ ደስታቸውን ገልጸው ዝርዝሩን ማየት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሕወሓት ትጥቅ መፍታትና ከባድ መሳሪያዎቹን በሙሉ ማስረከብ እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱ፣ የሕወሓት መዋቅር በየደረጃው መፈራረስና በየመዋቅሩ ፌደራል መንግስቱ የሚወክለው አስተዳደር እንደሚሰፍን መፈረሙ ወዘተ… ብዙዎች በቀላሉ ይሳካል ብለው ያልገመቱትና አንዳንዶችም ጭራስ ይሆናል ብለው ያላሰቡት ነገር ነው። ትግራይ ውስጥ የታጠቀ ሕወሓታዊ ኃይልም ሆነ አስተዳዳራዊ መዋቅር እንደማይኖር ስምምነት ላይ ተደርሷል መባሉ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ፣ ለማመንም ያስቸገረና ሕወሓቶች ላይ ላዩን የተስማሙ መስለው ውስጥ ውስጡን የሚሸርቡት ሴራ ይኖር ይሆን የሚል ጥያቄ ለማንሳት ያስገደደ ነው።
ተወደደም ተጠላም በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ፣ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በወልቃይትና በጠለምት አካባቢዎች እንዲሁም ሰፋ ባለ የአፋር አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ የተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ኢትዮጵያውያን በጥይት የሚረግፉበት፣ ኢትዮጵያውያን የሚፈናቀሉበት፣ ኢትዮጵያውያን በታጣቂዎች ክብራቸውን የሚነፈጉበት፣ ኢትዮጵያውያን ሃብትና ንብረታቸውን የሚያጡበት፣ አገሪቱም ቢሆን የትየለሌ ሃብቷን የምትከሰክስበት ጦርነት ስለሆነ የሰላም ስምምነት ፍንጭ መሰማቱ ብዙዎችን አስደስቷል። ነገር ግን፣ ችግሩ ውስብስብና ብዙዎች የየራሳቸውን ጥያቄ ይዘው የገቡበት ስለሆነ ትግበራው አጠያያቂ ጉዳዮችን ያካተተተ እንዳይሆን ስጋትን እየጋረጠ ነው።
ድርድሩ በብልጽግና መንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረገ ስለሆነ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በርካታ ቡድኖች ምን አቋም ይይዛሉ ብሎ መጠየቅ ተገቢና የስምምነቱን ተግባራዊነት፣ እንዲሁም ዘላቂነትና ተናፋቂ የሚደርግ ነው። የአማራ ሕዝብ፣ የአፋር ሕዝብ፣ የኤርትራ ሕዝብና መንግስት፣ የአገውና ቅማንት ሕዝብ ወዘተ…. በዕሳቱ ዳር የሚገኙ ናቸውና በርካታ ጥያቄዎች ይኖራቸዋል።
ሕወሓት የፌደራሊስት ኃይሎች ብሎ ያደራጃቸውና ያስታጠቃቸው፣ ትግራይ ውስጥ ጽሕፈት የተከፈተላው የአገው፣ የቅማንትና የአፋር ኃይሎች መኖራው ይታወቃል። ሕወሓት ኦነግ-ሸኔን፣ የጋምቤላና የጉምዝ ነጻነት ኃይሎች የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖችንም እንደሚረዳና በፌደራሊዝም ስም የራሱን አጀንዳ አሸክሞ አሐዳዊ የሚሉትን የብልጽግናን መንግስት እንዲፋለሙ እንደሚደልላቸው ይታወቃል። እነዚህ ኃይሎች ከጦር ሜዳ ዝናቸው ይልቅ በሕዝብ ላይ በሚፈጽሙት ግፍውና ሰቆቃ የሚታወቁ ናቸውን፣ ከዚህ በኋላስ ዒላማ የተደረጉት ሕዝቦች እፎይታ ያገኛሉ ብሎ ማሰብን ከባድ ያደርጉታል። ከዚህ ስምምነት በኋላ እነዚህ ኃይሎች በዚሁ ቁመናቸውም ሆነ በሌላ መልክ የግፍና የሰቆቃ ስራቸውን እንደማይቀጥሉ ብሎም ወደ ሽምቅ ውጊያ እንደማይገቡ ማረጋገጫ ማግኘትም ወሳኙ ነጥብ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በክልሉ ውስጥ እስረኛ ሆኖ፣ መውጫና መግቢያ ተከልክሎ፣ የዕርዳታ ምግብና መድኃኒት በጭንቅ እየደረሰው፣ በቁንቁንም እየተሰፈረለት ባለበት ሁኔታ ነውና የፕቶሪያው ስምምነት የተፈረመው፣ ይህ ስምምነት የሕወሓት አውራዎችን በስተርጅና ወደ ቆላማ በረሀዎችና ወደ ሰዋራ ዋሻዎቻው ከመሰደድ ከማዳን ያለፈ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ ብዙም ግልጽ አይደለም። ትግራይ ውስጥ በአቋማቸው ከሕወሓት ብዙም የማይለዩ ነገር ግን ትግራይን መገንጠልና ራሷን የቻለች አገር የማድረግ ግብ ይዘው የሚውረገረጉ ቡድኖች መኖራቸው ይታወቃልና የፕሪቶርያው ስምምነት ለእነሱስ ምን ትርጉም ይኖረዋል ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። እነዚህ የትግራይ ቡድኖች ይነሱም ይብዙም ብዙዎች ወጣቶች የሆኑበት ተከታዮች አሏቸው።
ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ምድር ገብቶ እየተዋጋ የመሆኑ ጉዳይ እያወዛገበ የነበረ ጉዳይ ነው። ከኤርትራ አቅጣጫ ወደ ትግራይ ውጊያ የከፈቱት እርቃናቸውን ወደ ኤርትራ ሸሽተው የኤርትራን ወታደራዊ ልብስ ለብሰው ተመልሰው ወደ ውጊያ የገቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንጅ ኤርትራውያን አይደሉም ሲባል ቆይቶ በመጨረሻ ላይ የኤርትራ ጦር ራሱን ለመከላከል ሲል ወደ ግብግቡ መግባቱና በኋላም ወደ ኤርትራ መመለሱ በይፋ ታምኗል።
አሁንስ ከጥቅምት 2015 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት የኤርትራ ጦር ተሳትፎ እያደረገ ነውን? በብልጽግናም ይሁን በኤርትራ መንግስት በኩል ይህን በሚመለከት የተባለ ነገር ባይኖርም ሕወሓትና በርካታ የውጭ መገናኛ ብዙሐን ኤርትራ በ2013 ካሰማራችው በእጥፍ የሚበልጥ ኃይል አሰማርታ በመሳተፍና በጦርነቱ ውጤት ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ይናገራሉ። የኤርትራ መንግስትም ሆነ የኤርትራ መንግስት ንብረት የሆኑት ኤሪቲቪና ድምጺ ሐፋሽ (የኤርትራ ሬዲዮ) የኤርትራን መሳተፍም የሚመለከትም ሆነ ትግራይ ውስጥ ስለሚካሄደው ጦርነት እንድም ቃል ሳያሰሙ ነው ወራት የተቆጠሩት።
ሰኔ 2013 የብልጽግና መንግስት አንዴ ለእርሻ ስራ ሲባል ሌላ ጊዜ ደግሞ አለኝታ የሚሆን ደጀን ህዝብ ፍለጋ መከላከያ ከትግራይ መውጣቱን ሲገልጽ የኤርትራ መንግስት በቀጥታ በፕሬዘደንት ኢሳያስ በኩል ምክክር ሳይደረግበትና የኤርትራ መንግስት ሳያውቀው የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ መውጣቱን በቅሬታ መልክ ለኤሪቲቪ ቃለ ምልልስ ባካሄዱበት አንድ አጋጣሚ አውስተውት ነበረ። አሁንስ ይህ የፕሪቶሪያው ስምምነት ለኤርትራ መንግስት ምን ዓይነት ትርጉም ይኖረው ይሆን?
ኤርትራ-አስመራ ውስጥ የኤሪቲቪና የድምጺ ሀፋሽ (የኤርትራ ሬዲዮ) አባላት የሆኑ ጋዜጠኞች በግላቸው ተደራጅተው በከፈቱት ‘ኤርትራ ሚዲያ ኔት-አስመራ’ (EMNA) በተባለው የዩትዩብ መስኮት በኩል በመካሄድ ላይ ስላለው ጦርነት ከፋናና ከዋልታ፣ ከኢቲቪና ከአዲስ ቲቪ ባልተናነሰ መንገድ ብዙ ዝግጅቶችን እያቀረቡ ነው። ይህ ሚዲያ በቀጥታ ስለ ኤርትራ ጦር ተሳትፎ የሚለው ነገር ባይኖርም፣ በመመዝገብ ላይ ያለው ድል የኤርትራ ጦር ድል መሆኑን የሚገልጽ ዝግጅት በተከታታይ በማቅረብ ላይ ነው። ይህ ሚዲያ የጥቅምት 2015 ጦርነት ከተጀመረበት ቀን ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ዕለት ድርስ ካቀረባቸው በርካታ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ ብቻ ይህን ጦርነት የማይመለከትና ወዲ ትኩል ስለተባለው ታዋቂና ኤርትራዊ አርቲስትና ታጋይ ታሪክ የሚተርክ ክፍል ሶስት ትረካ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ትረካ ቀደም ብለው ከተለቀቁት ሁለት ክፍሎች ለየት ብሎ የተዘጋጀና ድምጻዊው በባድመ ጦርነት ወቅትና ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ባዜማቸው ጸረ-ሕወሓት የቅስቀሳ ስራዎቹ ላይ ሰፊ ትኩረት ያደረገ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
ሌሎቹ ግን በቀጥታ ከዚህ ጦርነት ጋር ወይም ሕወሓት እንዲጠፋ ያለ ምኞትን (ፍላጎትን) መሰረት አድርገው የተዘጋጁ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ ‘ኤርትራ ትድምስሰኒ ኣላ’ (ኤርትራ እየደመሰሰችኝ ነው) ብሎ ሕወሓት በማማረር ላይ መሆኑን የሚገልጸውና በተዘዋዋሪ ሕወሓት በሕዝባዊ ግንባር እየተኮረኮመ መሆኑን የሚገልጸው እንዱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘ወያነ መንእሰያት ትግራይ ለኻኺማ ትጠፈላ’ (ወያኔ የትግራይን ወጣቶች ይዛ ወደ መቃብሯ እየወረደች ነው)፣ ጭፍራ ወያነ እንታይ ኣፍረየት? ህልቂትን ጥፋትን መነእሰያት ትግራይ (ወያኔ ከጦርነቱ ምን አተረፈች? የወጣቶችን እልቂትና ጥፋት)፣ ‘አይኒ ንስሪ’ (የንስር ኣይን)፣ ‘ኣይበልናንዶ’ (ብለን አልነበረም አንዴ)፣ ‘WEYANE delete YBEHAL ALO’ (ወያኔ ዲሊት እየተደረገ ነው)፣ ‘ወያነ ኣብ ኮማ ኣትያ ትሰሓግ ኣላ’ (ወያኔ ኮማ ውስጥ ገብታ እያቃሰተች ነው)፣ ‘ወያነን ፋልሶ ዜና ዓወታቱን’ (ወያኔና የበሬ ወለደ ድል ዜናዎቹ)፣ ‘ጸሓይ ወያነ ትዓርብ ኣላ’ (የወያኔ ጸሐይ እየጠለቀች ነው)፣ እና ‘ወያኔ ራሱ በማሠው ጉድጓድ እየተቀበረ ነው’ የሚሉ ይገኙበታል።
የኤርትራ ጦር ተሳትፎ ሃቅ ከሆነ ‘የኤርትራ መንግስት የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው?’፣ ‘ብልጽግና ትግራይን ማስተዳደር ሲጀምር የኤርትራ ጦር ሚና ምን ይሆናል?’ እና ‘የኤርትራ ጦር መቼ ወይም ምን ካደረገ በኋላ ከትግራይ ምድር ይወጣል?’ ለሚሉት ጥያቄዎች የብልጽግና መንግስት ግልጽ መልስ ሊኖረው ይገባል። ከዚህ ሌላ ‘የብልጽግና መንግስት ሰኔ 2013 ትግራይን ጥሎ ሲወጣ የኤርትራ ጦር የት ነበረ? ‘የኤርትራ ጦር ከትግራይ የወጣው የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ሳይወጣ ቀድሞ ነበር ወይስ ዘግይቶ?’ ተብሎ ሲጠየቅ በሚሰጠው መልስ ላይም ብልጽግናዎች ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል።
ጥቅምት 15/2015 የሕወሓት መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለጋዜጠኞች በመግለጫ በመስጠት ስም ዛቻ ሲሰነዝሩ “…. የአማራ ወጣት ትግራይ ውስጥ ለምን ይሞታል? የአማራ ወጣት ወደ አገርህ ሂድ! …. የኤርትራ ወጣት ትግራይ ውስጥ ለምን ይሞታል? የኤርትራ ወጣት ሂድ ወደ አገርህ!….” ሲሉ ተሰምተዋል። ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከሕወሓት ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ሁለቱና ዋና-ዋናዎቹ ታላቋን ትግራይ መመስረት እና በአማራው ሕዝብ ላይ ዘላለማዊ ጥላቻን ማንገስ መሆኑን ያውቁታል።
ይህ ደግሞ የአማራውን አንገት ማስደፋት፣ አማራውን ሕዝብ ማጠልሸትና (ሥሙን ማጥፋትና) በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ማስጠላት፣ አማራውን ሕዝብ እረፍት መንሳት መሆኑ በግልጽ በማንፌስቶ-68 ውስጥ የተቀመጠ ሃቅ መሆኑን አይክዱትም ማለት ነው። ስለዚህ፣ የአማራ ወጣት እያሸነፈም ሆነ እየተሸነፈ ይህን ሰይጣናዊ ዘመቻ የመመከት ግዴታ ውስጥ የገባ ወጣት ነው። ይህ ማንፌስቶ ሆነ ተብሎ ካርታ ተስሎለት እንዲታይ ባይደረግም፣ በሐተታ መልክ የተጠቀሰው የትግራይ መሬት ነው የተባለ ምድር ከየት እስከ የት እንደሚከነዳ ግልጽ ነው።
የታላቋ ትግራይ ግዛት ከወሎና ጎንደር፣ ከአገውና ከአፋር፣ ከኤርትራና ከጅቡቲን ሰፋፊ ምድሮችን ገምድሎ ሊወስድ በሚችል መልኩ ሊተረጎም እንደሚችል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ ሌላ ቅማንት ማለት አገው ነው- አገው ማለት ቅምንት ነው የሚል ወሬ በሕወሓቶችና ሁለቱን ሕዝቦች እንወክላለን በሚሉ የሕወሓት ተላላኪዎች ስለሚነዛ፣ የታላቋ ትግራይ ምድር ጎንደርን በሰፊው የሚውጥ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ፣ አማራው ወጣት ‘ወደ አገርህ ሂድ’ ሲባል ‘አገሬ ከየት እስከ የት ነው?’ ብሎ መጠየቁ ግድ ነው። በሌላ በኩል ማንፌስቶ-68 የትግራይ ምድር ትግርኛ ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ ያለበትን ምድር ሁሉ ያጠቃልላል ስለሚል ታላቋ ትግራይ ደቡብ ኤርትራን (ሠራየን፣ ሐማሴንን፣ አካለጉዛይን) ያጠቃልላል ማለት ነው። ዐፋርኛ ተናጋሪዎች ያሉበት ምድር በሙሉ የትግራይ ነው ስለሚልም፣ አሰብ የሚገኝበት ደቡባዊ ቀይ ባህር የሚባው የኤርትራ አውራጃም ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ ይካተታል ማለት ነው። ስለዚህ የኤርትራ ወጣት ‘ወደ አገርህ ሂድ’ ሲባል ‘አገሬ ከየት እስከ የት ናት?’ ብሎ መጠየቁም ግድ ነው። ይህ ጥያቄ የዘላለም ጥያቄና ዝንተ-ዓለም ደም እያፋሰስ ሊኖር የሚችል ጉዳይ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሰላም የሚያመጣው ቁልፍ በሕወሓት እጅ ውስጥ ነው ያለው። ስለዚህ በፕሪቶርያው ስምምነት ሕወሓት ራሱን ወደ መቃብር ለማውረድ የተስማማ ዓይነት ስምምነት መፈራረሙን ራሱ ሕወሓት በአቶ ጌታቸው ረዳ በኩል ቢናገርም፣ ሕወሓት በቁሙም ሆነ በሞቱ ይህን ቅዠቱን እርግፍ አድርጎ መተውን፣ ማንፌስቶ-68 የሚለውን ዐብይ-ፕሮገራሙንም (መሪ ፕሮግራሙንም) ወደ መቃብር አብሮ እንደሚያርደው መናገር ይገባዋል።
ዶ/ር ደብረጽዮን የኢትዮጵያና የኤርትራና የአማራ ሕዝቦች ትግራይ ውስጥ ለሚፈጸመው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ሊሆኑ ስለሚችሉ በሰላማዊ ተቃውሞ ወይም በግብግብ የብልጽግናዎችን አካሄድ መግታት እንዳለባቸው ሲያሳስቡም ተሰምተዋል። ጥቅምት 2013 ላይ ጦርነት እንደተጀመረ ከሕወሓት መሪዎች አንዱ እና እነ ታደሰ ወረደንና እነ ምግበይን ይዘን ቆመናል እነሱ ደግሞ እነ ገዱ አንዳርጋቸውንና እነ አባ ዱላ ገመዳን ይዘው ተሰልፈዋል ብሎ አሽሙር ሰርቶ ነበረ። ስለ ኦሕዴድና ብአዴን ዋና ዋና ሰዎች ማንነት እየተነተነ ሶፍትዌራቸውን ያወለቁባቸው ሮቦቶች መሆናቸውንና የሕወሓት መሪዎችን ልዕለ ሰብዕነትም ተናግሯል። በአንዳንድ ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች ሮቦቶች ፕሮግራማቸው ተዛብቶ ወደ አውዳሚ ጸረ-ሰው አሸንጉሊትነት ሲቀየሩና ሰሪዎቻቸውን ጨምሮ የሰውን ልጅ ሁሉ ሲተናኮሉ እንደሚያሳዩት ሁሉ፣ በወቅቱ በትግራይ ሕዝብ ላይ ለደረሰው አስከፊ ሰቆቃም የሮቦቶቹ ጌታ የሆነው ሕወሓት ተጠያቂ መሆኑን ዶ/ር ደብረጽዮን ግምት ውስጥ አስገብተውት ይሆን?
ኦሕዴድ፣ ኢሕዴን/ብአዴንና ሌሎች የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ሁሉ የተፈጠሩት በሕወሓት ነው። የነዚህ ድርጅቶች ይስሙላ መስራቾችና ዋና ዋና መሪዎች በሕወሓት ሙሉ ፈቃድና ዕውቅና ተመልምለው ለዚህ የበቁ ናቸው። አባዱላ ገመዳና ዐብይ አሕመድ የተባሉትን ሰዎች አሳምሮ የሚያውቃቸውና ለዚህ ደረጃ ያበቃቸው ሕወሓት እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ አይደለም፤ ደመቀ መኮንንና አለምነህ መኮንን የተባሉትንም ሰዎች አሳምሮ የሚያውቃቸውና ለዚህ ደረጃ የበቃቸው ሕወሓት እንጂ የአማራ ሕዝብ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦችና ጓዶቻቸው ለሚፈጽሙት ነገር ሁሉ ተጠያቂው ሕወሓት እንጂ ሕዝብ አይደለም።
ሕወሓት ‘ጉድጓድ ስትቆፍር ጥልቅ አታድርገው፤ የሚገባበት አይታወቅምና!’ የሚለውን ብሂል ችላ ብሎ መኖሩ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በሕዝብ ላይ በመጨረሻም በራሱ ላይ ቃላት ሊገልጸው የማይችል ችግር መጋረጡ ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ማንም ሊዘነጋው የማይገባው በተለይም የትግራይ ምሁራን ሊዘነጉት የማይገባ ሃቅ በትግራይ ሕዝብ ላይ ለደረሰው የሚሰረዝና የማይሰረዝ በደል ሁሉ ዋናው ተጠያቂ ራሱ ህወሐት መሆኑን ነው።
የጽሑፉን አዘጋጅ ግዛቸው አበበን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


