ወደኋላ እንዳንመለስ!

0
1163

በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ኹለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት ልክ በኹለተኛ ዓመቱ ዋዜማ ላይ መፍትሔ ያገኘ ይመስላል። ይህም የስምምነት መፈጸም ዜና ለብዙዎች ልብ እረፍትን የሰጠ ሲሆን፣ በአንጻሩ ጥርጣሬ የገባቸውና ‹እውነት ነው ወይ? ተግባራዊስ ይሆናል ወይ?› ብለው የሚጠይቁና ጥርጣሬ የገባቸው ጥቂት አይደሉም። ያም ሆነ ይህ ግን፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንና ሰላም ሰፍኖ እንዲቆይ መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል። መቅደስ ቹቹ ይህን በማንሳት ሐሳባቸውን እንደሚከተለው አጋርተዋል።

ሰላምን የሚጠላ የለም። አሁን ዓለም ያለችበትን መልክ ልብ ብሎ ያየ፣ ሰውን የሚያበላውና የሚያጠጣው ምግብ ሳይሆን ሰላም ነው ብሎ በልበ ሙሉነት ሊሞግት ይችላል። ስህተትም አይደለም። ‹‹ሰላም ይኑር እንጂ በአገር ለምኖ መብላትንስ ማን ዐየበት!› ብለው ሰላምን አብዝተው የናፈቁና የተመኙ ጥቂት አይደሉም።

በተለይም ላለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በከፋ ሰላም ማጣት ውስጥ ለቆየችው ኢትዮጵያ፣ የሰላም ወሬ ብርቅ ነው። መካን ተብሎ ቆይታ በእርጅናዋ ልጅ እንዳገኘች ሴት፣ ለኢትዮጵያም ‹አለቀላት! ፈረሰች! ጠፋች! ተበተነች!› ተብሎ ሁሉም ያበቃ ሊመስል በቀረበበት ጊዜ የሚሰማ የሰላም ዜና እንደዛ ነው፤ ተአምር የመሰለ።

ከሰሞኑ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የብዙዎችን ልብ ያረጋጋ ነው። በአንጻሩ ጥርጣሬንና ፍርሃትን የተመላ ልባችን በእርግጥ እንዴትም ያለ እፎይ የሚያሰኝ ዜና ቢሰማ ለማመን መዋል ማደሩ፣ ‹ቆይ ላስብበት!›  ማለቱ አይቀርም። ይህም አዲስ ልምምድ የሚያሻው በመሆኑ፣ ‹አይ! ስምምነታቸውን ነገ አፍርሰው ተመልሰው ወደ ግጭት ሊገቡ ይችላሉ› ብለው ጥርጣሬአቸውን የሚያምኑ ላይ መፍረድን ከባድ ያደርገዋል።

‹ወተቷን አላይም እንጂ በሰማይ አለኝ› ካሉት ላም ወተት እንደማግኘት ነገሩን በተለያየ አንጻር በጥርጣሬ ያዩት አሉ። ኹነቶችን እያገጣጠሙና ‹የሙያተኛ› የመሰለ መላምታዊና ‹ትንበያ› የመሰለ አስተያየት እየሰጡ ‹ይሆናል ብላችሁ ነው?› የሚሉም ጥቂት እንዳልሆኑ እያየን ነው፤ እኔም በግሌ ታዝቤአለሁ። እነዚህም ቢሆኑ (ሌላ ተንኮል ኖሯቸው ካልሆነ በቀር) አብሯቸው የኖሩትና ባለፉት ኹለት ዓመታት ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጠሩ ክስተቶች የፈጠሩባቸው ስሜቶች ናቸው ያንን እንዲሉ ያደረጋቸው ብዬ አምናለሁ።

በዛና በዚህ፣ በብዙ እልፍ ጥርጣሬ ውስጥም ቢሆን ግን ሰላምን የመሻት ፍላጎትና ተስፋ ብዙዎች ዘንድ አለ። አዎን! ልንጠራጠር እንችላለን፤ ፍርሃትም ሊኖር ይችላል። ግን ሰላምን ለማምጣት አሁን አንደኛው በር ተከፍቷል። ሰላምን የሚሻ ሰው አንድ ቀን ደኅና ውሎ ማደሩን ያከብራልና፣ በጥርጣሬ ውስጥ ሆኖም እንኳ በተቻለ መጠን በጎውን እያሰቡ፣ መልካሙን ተስፋ እያደረጉ፣ ለተጀመረው የሰላም ብልጭታ መጉላት የድርሻን እያበረከቱ በእምነት መቆየት ተገቢ ይመስለኛል።

በነገራችን ላይ፤ ሰላም በዝማሬ የምትመጣ አይደለችም። ‹ሰላም ሰላም› ስለተባለ እና ‹ሰላምን እንፈልጋታለን! ሰላምን እንወዳታለን!› ብለን ስለፈከርን ብቻ ወይም በወረቀት ላይ በተቀመጠ ፊርማ ብቻ ሰላም አትገኝም። እንኳንና ዓለም እንዲህ የናፈቀቻት ሰላም፣ አንድ ጎረምሳ የወደዳትን ሴት አልያም አንዲት ኮረዳ የወደደችውን ወንድ ስለጠሩ ብቻ ወይም እወደዋለሁ፣ እወዳታለሁ ስላሉ ብቻ አያገኙም። በጋብቻ የሚደረግ ፊርማ እንኳ ባል ሚስትን ወይም ሚስት ባልን ‹የእኔ› ለማለት ዋስትና እንደማይሆን በብዙ ታዝበናል። ሁሉም ጥረት፣ ትጋት እና ሥራ ይፈልጋል።

ሰላም ጠባቂ ያስፈልጋታል። እንክብካቤን ትሻለች። እንደ ችግኝ ናት፣ ጠንክራ ባለቅርንጫፍና ጥላ ሰጪ እንድትሆን ተንከባካቢ ያሻታል። መኖሯ ብቻ ለመቆየቷ በቂ ማረጋገጫ አይደለም።

ወደኋላ እንዳንመለስ!

እስከ አሁን ብዙ ወደኋላ ተመልሰን እናውቃለን። ያም መመላለስ ጉዞአችንን የኋሊት አድርጎት ነው ብዙዎቻችን በትንሽ ትልቁ ተጠራጣሪ የሆንነው። ብዙ አደናቃፊ ደንጊያዎች አግኝተውን ወዳሰብንበት ከመድረስ አስቀርተዉናል። ሁላችን እያንዳንዳችን ድርሻ የሌለን፣ ጉዳዩ ሁሉ መሣሪያ በታጠቁ ወገኖች ብቻ ያለ ይመስለናል እንጂ፣ በተዘዋዋሪ ብዙውን ነዳጅ ያርከፈከፍን፣ ብዙውን ክብሪት ያቀበልን፣ ብዙውን አራግበን ያነደድን እኛም ነን።

‹ወደኋላ እንዳንመለስ ምን ይደረግ? የተደረገው ድርድርና የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ምን ማድረግ ያስፈልጋል?› እነዚህ በእርግጠኝነት ሰሞኑን በርካታ መገናኛ ብዙኀን በተለይ የመንግሥት የሆኑት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መሆናቸው አይቀርም።

ሰነም ናራጊ ትውልደ ኢራናዊና ኢንግሊዛዊት ደራሲ እንዲሁም የዓለም ዐቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅት ሥራ አስፈጻሚ ናት። ‹የሰላም ድርድር እና ስምምነት› በሚል ርዕስ ባስነበበችው አንድ የዳሰሳ ጥናት ላይ ይህን በተመለከተ ‹ከቃላት ወደ ተግባር› በሚል ንዑስ ርዕስ፣ በጽሑፍ የተደረጉ ስምምነቶችና ፊርማዎች እንዴት ወደ ተግባር መሄድ እንደሚገባቸው የሚያስረዳ ጽሑፍ አካትታለች። እኔም ከንባብ በተረዳሁት መልኩ በዛ ጽሑፍ የተነሳውን ሐሳብ ላጋራችሁ።

የሰላም ስምምነቶችን የመተግበሩ ኮሮኮንቻማ መንገድ ብዙውን ጊዜ ዳገታማም ነው። ምክንያቱም ስምምነቶቹ ላይ የሚደረሰው ጥቂት ከማይባሉ ወራት ዝግጅትና ምስጢራዊ ከሆኑ ድርድሮች በኋላ ነው። ታድያ ስምምነቱ እስኪፈረም እና ድርድሩ ተፈጸመ እስኪባል ድረስ ሁሉም ትኩረቱን በጉዳዩ ላይ ያደርጋል። ነገር ግን ከቀደመው ይልቅ ከባድ ሆኖ የሚገኘው ስምምነቶች ከተፈረሙ በኋላ ነው።

ስምምነቶች ከተፈረሙ በኋላ ብዙዎች በብዙ ይጠብቃሉ። በእርግጥ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር አስቀድሜ እንዳልኩት የነገሩን ፍጻሜና የሰላምን መምጣት በጉጉት የሚጠብቁ እንዳሉ ሁሉ፣ ነገሩን በጥርጣሬ ሆነው የሚከታተሉ አሉ። እነዚህ ኹለቱም አካላት ግን በተለያየ አቅጣጫ ይሁን እንጂ ከስምምነቱ በኋላ አንዳች የሚጠብቁት ውጤት እንዳለ እሙን ነው።

ነገር ግን ስምምነቶች ከተፈረሙ በኋላ የሚመጣው ሰላም ስሱ ወይም በቀላሉ ሊሰበር የሚችል ዓይነት ነው። ምንአልባት ፈጽሞ ለመደፍረስ ትንሽ ኮሽታ በቂው ሊሆን ይችላል። ያም ብቻ አይደለም፣ የሰላምን መምጣት አብዝተው የሚጠሉና ኹከቱን የለመዱ፣ የወደዱና ቀለብ መስፈሪያቸው ያደረጉትም አርፈው አይተኙም። የተገኘ የመሰላቸውን ሰላም ለማደፍረስ ይለፋሉ።

ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ፣ ድርድሩን ያደረጉ አካላት መካከልም በጥርጣሬ መተያየት አይጠፋም። ጊዜ ሰጥቶ ‹ማን ስምምነቱን ለመፈጸም የመጀመሪያውን እርምጃ ይሄዳል› የሚለውን ለማየት በተደራዳሪ ወገኖች መካከል ‹የመጠበቅ› ሁኔታም ሊኖር ይችላል።

ይህን ሐሳብ በጽሑፏ ያቀበለችን ትውልደ ኢራናዊ ኢንግሊዛዊቷ ሰነም ናራጊ፣ እንዲህ ባለ ወቅት መተማመንን ለመገንባት ‹ለሰላም ዝግጁ ነኝ› የሚል ተጨባጭ የሆነ ማረጋገጫ መስጠት ወሳኝ ነው ስትል ትመክራለች። ከእነዚህም ለምሳሌ ተኩስ አቁም አንደኛው ነው።

ቢሆንና ቢሳካ፣ እንደውም ድርድር ወይም ስምምነት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ እንዲህ ያሉ ለሰላም ዝግጁ የመሆን ማሳያዎች ቢተገበሩ ብላለች። ባይሆን እንኳ በንግግር ወቅት አልያም ከስምምነት በኋላ ግን በፍጥነት ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገቡ ጉዳዮች ቸል ሊባሉ እንደማይገባ ነው የመከረችው።

ቀጥላ በጸሑፏ ያስቀመጠችውን ቃል በቃል በመተርጎም ላስቀምጠው፤ ‹‹በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ብዙውን ጊዜ በወረቀት የተደረጉ ስምምነቶች ወርደው የሰዎች ሕይወት ውስጥ ለመታየት ይዘገያሉ። እንዲህ ያሉ ስምምነቶች ወደ ትግበራ በሚያመሩ ጊዜ ባልተሳኩባቸው ወይም በከሸፉባቸው አጋጣሚዎች፣ የቀደመውን ግጭት መልሰው መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን ግጭቱን ከነበረበት ከፍ እንዲልና የተባባሰ እንዲሆን ጭምር አድርገዋል፤ ሊያደርጉም ይችላሉ። የተገነባው መተማመን ከፈረሰም፣ የባሰ አለመረጋጋት ይነግሣል።››

ምንአልባት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አጥኚዋ መነሻ አድርጋ ጉዳዩን ካነሳችባቸው ክስተቶች አንጻር የተለየ ሊሆን ቢችልም፣ ደውሉ ለሁሉም መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ሐተታ መሠረት እንዲህ ያሉ የሰላም ስምምነቶች ተግባራዊነት ላይ በሚገባ ካልተሠራበት፣ ወደ ባሰ ችግር ሊያስገባ የሚችል እንደሆነ ነው።

እኛን ማለትም እንደ ዜጋ እና እንደ ብዙኀኑ ሕዝብ አካል እንዴት ይመለከተናል? ጥሩ ጥያቄ ነው። የጥላቻ ንግግር ዛሬ ላይ ብዙዎችን በብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ከአንደበት የሚወጣ ቃል ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ለማስረዳት ብዙ ብሂል ያለን ሕዝብ ብንሆንም፣ አንዱንም ከልባችን አኑረን ለንግግራችን ጥንቃቄ ስናደርግ አልታየንም።

እናም ወደኋላ እንዳንመለስ ሁላችን ከጥላቻ ንግግር መቆጠብ፣ ለሰላም የሚሆነውን ሁሉ መደገፍ ያሻናል። ሰላም በሰሜኑ ብቻ ሳይሆን በአራቱም አቅጣጫ ያስፈልገናልና፤ ያንን ሰላም አንድ በአንድ ለማምጣት ከትላንት ይልቅ ነገን በማየትና በማሰብ፣ በተስፋና በጽኑ እምነት ሆነን ወደፊት መሄድ ይጠበቅብናል። ኢትዮጵያን ብሎ መሞኘት ተሸናፊነት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ሞኝ አያሰኝምና፣ ቢያሰኝም ግድ ሊሰጠን አይገባምና፣ ይህን ፊታችን የቀረበውን ሰላም ‹እንደ እርግብ የዋህ፣ እንደ እባብ ብልህ› ሆነን አጥብቀን ይዘን በማጽናት እንበርታ!


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here