የብሽሽቅ ፖለቲካ ይብቃን!

0
1616

አገራችን ኢትዮጵያ ቁልቁል ከተጓዘችበት ጎዳና መልሳ ሽቅብ መውጣት የሚያስችላትን መንገድ ለመያዝ ማሰቧን ከሰሞኑ የተገኘው የድርድር ውጤት ያመላከተ ነው። ወደ ሰላምና እድገት የሚያመራውን ዳገት መንገድ መመልከቱ ብቻውን ወደ ላይኛው ከፍታ ስለማይወስድም፣ በአንድ እርምጃ በጋራ በመራመድ መውጣቱን ልንጀምረው ግድ ይለናል።

እንደአገርና እንደሕዝብ ለለውጥ የምንከተለው አቅጣጫ ወሳኝ እንደመሆኑ፣ አብሮ መጓዙም ቶሎ ለመድረስም ሆነ ልዩነት ኖሮ መቃቃር ተፈጥሮ መልሶ ላለመንከባለል ወሰኙ ምዕራፍ ነው። ወደ ሰላም የሚመራው ስምምነት አብሮ ለመጓዝ አንድ እርምጃ እግርን አንስቶ ለመርገጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የውጤቱ አቀባበልም ሆነ አተረጓጎም ለበጎም ሆነ ለክፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ሊታመን ይገባል።

በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ተደረሰ የተባለው የተኩስ ማቆምና የትጥቅ መፍታት ስምምነት፣ በዘላቂነት ስለመቀጠሉ እርግጠኛ መሆን ባያስችልም፣ በራሱ የሰው ሞት እንዳይቀጥል በማድረጉ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሚደገፍ እርምጃ መሆኑን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

ስምምነቱ እንዲቀጥልና ወደተሻለ ደረጃ እንዲያመሩ በፖለቲከኞች የተደረሰው ስምምነት ወረቀት ላይ ስለሰፈረ ብቻ ውጤት ያመጣል ማለት ዘበት ነው። ለስምምነቱ መዝለቅም ሆነ ለሰላም መምጣት የመሪዎች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ የሕዝቡ ድርሻም የጎላ እንደሆነ ሊታወቅ ግድ ይላል።

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የታጠቁት አካላትም ሆኑ ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ሥልጣን ያለው የመንግሥት ኃላፊነት የጎላ ቢሆንም፣ ሁሉም ኅብረተሰብ የየራሱን ሚና ሊወጣ ግድ ይለዋል። ይህ የሚሆነው በጉዳዩ በቀጥታ በመሳተፍ ብቻ ሳይሆን፣ ከስምምነቱ አተረጓጎም ጀምሮ ምን ሊያስከትል እንደሚችል የግል አስተያየትንም ሆነ መላምትን ከማስቀመጥ በመቆጠብም ሊሆን ይችላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካን ለተከታተለ፣ የወዳጅን ድጋፍ ማዕከል ያደረገ ሳይሆን በጠላትነት የተፈረጀን አመለካከት መሠረት ያደረገ መሆኑን መመልከት ይቻላል። አብዛኛውን የማኅበራዊ ሚዲያ ተቺዎችንም ሆኑ የማኅበረሰብ አንቂ የሚባሉትን ተደማጭነት ያላቸውን ግለሰቦች አስተያየት ከተመለከትን፣ ጠላት ያሉትን ያናደደ ወዳጅ ይሆናል፣ እነሱን (ባላንጣቸውን) ያስደሰተ ወገናቸውም ቢሆን እንደጠላት የሚታይበት አስተሳሰብ ስር መስደዱን መረዳት ይቻላል።

ቅራኔና የባላጋራ አመለካከት ለደስታም ሆነ ለራስ ሀዘን ወሳኝ በሆኑበት በዚህ ዘመን ለሰላም ድርድሩም ሆነ ለውጤቱ የሚሰጠው አስተያየት ለመጪው አተገባበርም ሆነ ለወደፊቱ ታሪክ የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

የስምምነቱ ይዘት ምንም ይሁን ምንም፣ አንዱ ወገን ደስተኛ ሆኖ ሊታይበት ከሞከረ ሌላኛው ራሱን እንደተሸነፈ ሊቆጥረው እንደሚችል ግልፅ ነው። ጠላቴ ብሎ የሚያስበው ወገን እንደተሳካለት ከገመተ፣ የተጎዳ የሚመስለው ብዙ ነው። እቃ ልንገዛ ዋጋ ጠይቀን ሲወደድብን መልሰን በምናቀርበው ቅናሽ ዋጋ ላይ ሻጩ ወዲያው ከተስማማ፣ “ምነው ዝቅ ባደረግን” ብለን እንደምንቆጨው፣ አሁንም ለስምምነቱ የሚሰጠው ምላሽ ወሳኝ እንደሚሆን ልንረዳ ግድ ይለናል።

ገና ባልተወሰኑ ጉዳዮችም ሆነ፣ “ይህ ሊሆን ይችላል” እያልን መላምት በማስቀመጥ ራሳችን ግራ ተጋብተን ሌላውንም ማወናበድ እንደሌለብን ልንረዳ ይገባል። የተፈረመው ስምምነት የማይለወጥ መንፈሳዊ ቃል እንዳልሆነም ተረድተን፣ መቼም ሊሻሻልና ስምምነት ሊደረግበት እንደሚችል በማመን፣ ቢያንስ ሞትን በኹሉም ወገን በማስቀረቱ ሁላችንም ልንደሰትበት ይገባል።

የአሸናፊነት መንፈስ የአንድ ወገን ብቻ ከሆነ የእርቁንም ሆነ የአተገባበሩን ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ሁላችንም እንዳሸነፍን ካልወሰድነው፣ ፖለቲከኞቹ ራሳቸውን እንዳሸነፉ ቢቆጥሩ እንኳን ውጤታማ አያደርግም። ማንም ስለራሱ ጥሩ አመለካከት ቢኖረውም፣ እንደተሸናፊም ሆነ እንደከሃዲ በሌላው ወገኑ ቢቆጠር ደስ የሚለው የለም።

“የመጨረሻዋን ሳቅ የሚስቅ” እየተባለ እርስ በርስ በመተላለቃችን ሲሳለቅ የነበረ ሁሉ፣ ተደብቀው ሲስቁ የነበሩ የጋራ ጠላቶች ሲከፋቸውና ሲያዝኑ ሲመለከት እኛ ኢትዮጵያዊያን በሰዎች ጅምላ እልቂት እንደማንደሰት ሊረዳ ግድ ይለዋል። ስንት ሰው ሞቶ፣ ስንት ቤተሰብ ሕይወቱ ተናግቶ የጠፋው የሕዝብ ሀብትን ለመተካት የማንችልበት የኢኮኖሚ ችግር ላይ ሆነን ለመሳቅም ሆነ ለመደሰት ይቅርና ለማልቀስ እንባ የሚያጥረን ጊዜ ነበር መሆን የሚገባው። ይልቁንስ፣ መተላለቃችንን በዚህ ስላስቆምክልን ተመስገን ብለን ፈጣሪን የምናመሰግንበት ጊዜ ነው መሆን የሚገባው።

ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ የመጣበት መንገድ ግን ዘላቂነቱን ወሳኝ ያደርገዋል። በጉልበት የሚመጣ አልያም ተቀናቃኝን በሙሉ በማስወገድ የሚመጣ ውጫዊ ሰላም ሊኖር ቢችልም፣ ከሕሊናም ሆነ ከታሪክ ተጠያቂነት ስለማያስመልጥ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም። በጋራ ፈቃደኝነት በስምምነት የተደረሰና አንዱን ተሸናፊ ሌላውን አሸናፊ የማያደርግ ሲሆን፣ ሊዘልቅ እንደማይችል ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የተደረገውን የቪዬና ስምምነት ከግምት በማስገባት መረዳት ይቻላል።

ተወዳጇ አቀንቃኝ ማሪቱ ለገሠ ‹እንደው ዘራፌዋ› በሚለው በአንድ ሙዚቃ ሥራዋ፣ የሽንፈት ሰላም ጥሩ እንዳልሆነ የገለጸችበት መንገድ አለ።
ሰላም ሰላም ቢሉ፣ ሰላም ለአፍ ይሞቃል
በትግል ያልተገኘ፣ ተጦርም ይልቃል
የሽንፈት ሠላም ግን ተሽብር ይከፋል…

መሸናነፍን በስፖርታዊ ግጥሚያም ሆነ በትምህርቱ ዓለም እየተወዳደረ ለምዶት ላደገ ማኅበረሰብ ስሜቱን ማስቆም አዳጋች ቢመስልም፣ በትንሽ በትንሹ ከተጀመረ ወደመተባበርና ወደ ጋራ ደስታ የማያመራበት ምክንያት አይኖርም።

“የሞተ ተጎዳ፣ ድሃው ሞቶ ቀረ፣ እነሱማ ምን ጨነቃቸው” የሚሉና ይህን የመሳሰሉ ግጭትን የሚጠምቁ አስተያየቶችን፣ እንዲሁም የብሽሽቅ ፖለቲካን ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ኹላችንም ማቆም እንዳለብን አዲስ ማለዳ ታምናለች። “ስምምነቱ ከጦርነቱ በፊት ወደነበርንበት ሁኔታ ነው የሚመልሰው” እያሉ፣ መልሶ ወደ መፋጠጥና ግጭት የሚወስድን አመለካከት በማራመድ ተደራዳሪዎቹ ላይም ሆነ ተከታዮች ላይ ጫና ለማሳደር የሚሞክሩም ሊቆጠቡ ይገባል።

እስከአሁን የሄድንበት እርስ በእርስ የመሰዳደብ ሁኔታ የት እንዳደረሰን ተረድተን ወዴት መጓዝ እንደምንፈልግ የምንወስነው እኛው ነን። የግድ የሚቀጣን ወይም የሚከለክለን ካላገኘን ብለን፣ በምንወደው ወገን እንዳይደረግ የምንፈልገውን ሌላው ላይ አለማድረጉ ጥሩ መመዘኛ ቢሆንም፣ መከባበር ከጀመርን ወደ መዋደድ ለመሄድ እንደሚቀለን ግልፅ ነው። “እንቻቻል” እየተባልን፣ ሌላው ምንም ባደርግ ይችለኛል የሚለውን አስተሳሰብ አሽቀንጥረን ጥለን፣ የወደድነው እንደሚወደን የጠላነውም እንደሚጠላን መገንዘብ ይኖርብናል። ዱላ ከሰበረው ይልቅ ቃል የሰበረው አጥንት ተጠግኖ እንደማይጠግግ ተረድተን፣ ለምንናገረውም ሆነ ለምንጽፈው ነገር ደግመን እንድናስብበት አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here