ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎች አሁን ባሉበት አማራ ክልል ሥር ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የፌዴራሉ መንግስት በአፋጣኝ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቋል።
አብን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በመግለጫውም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረገው የሰላም ሥምምነት በንቃት እየተከታተለ እና አቋሙን በየጊዜው እያሳወቀ መቆየቱ ገልጾ፤ ሥምምነቱ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ያሉት መሆኑን ለመረዳት መቻሉን ገልጿል።
”በሰላም ሥምምነቱ ላይ ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ስለመሆኑ እውቅና ማግኘቱ፣ የሽብር ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ መሰል የሽብር ቡድኖች ስምሪት ላለመስጠት፣ ላለማገዝ እና ላለመተባበር ግዴታ የገባበት መሆኑ፣ ሥምምነቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕግ አግባብ በሽብርተኝነት በተፈረጀ አንድ ታጣቂ ቡድን መካከል የተደገረ ስለመሆኑ የተረጋገጠበት መሆኑ፣ የሽብር ቡድኑ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱ እና የሰላም ንግግር መድረኩን ወደ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ለመቀየር የተደረገው ጥረት የከሸፈበት መሆኑ ከሚጠቀሱ የሥምምነቱ ጠንካራ ጎኖች ውስጥ ናቸው፡፡” ሲልም በመግለጫው አስታውቋል።
“ይሁንና የሰላም ሥምምነቱ እጥረቶች ያሉበት ስለመሆኑም ፓርቲያችን ለማስተዋል ችሏል” ያለው አብን፤ ከእጥረቶቹ ውስጥ አንዱ የወልቃይት እና የራያ ጉዳይ መሆኑን አንስቷል።
በዚህም የወልቃይት እና የራያ ጉዳይ ውድ ዋጋ የተከፈለበት የማንነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ያለው እና የአገራችን ኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት የሚረጋገጥበት ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ እንዲያዝበት አሳስቧል፡፡
አክሎም ”የአማራ ሕዝብ ክፋይ የሆኑት እና ከ30 ዓመት በላይ በአማራዊ ማንነታቸው ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመባቸው የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎች አሁን ባሉበት አማራ ክልል ሥር ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የፌዴራሉ መንግስት በአፋጣኝ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቋል።
ከዚህም ባለፈ፤ በሰላም ሥምምነቱ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ቡድኑ ትጥቁን እንዲፈታ መንግስት በሙሉ አቅሙ እና ትኩረት እንዲሰራ እንዲሁም መንግስት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ እያለ የሚጠራው ቡድን እና መሰል “ነጻ አውጭ” ቡድኖች የፖለቲካ ህልውናቸው እንዲከስም እንዲሰራ እና የሕግ ክልከላ ሥራ ላይ እንዲያውል ጠይቋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራ፣ አፋር እና ትግራይ አካባቢዎች መልሶ የመገንባት እና የማቋቋም ሥራ የፌደራል መንግሥቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራና እንዲያስተባብር፣ መላው ኢትዮጵያውያንም ለመልሶ ግንባታው እና መቋቋሙ ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥሪውን አስተላልፋል፡፡



