ከኅዳር 15/2015 ጀምሮ ኢትዮጵያ ለኬንያ 500 ኪሎ ቮልት የኤሌትሪክ ኃይል መላክ እንደምትጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ጋር የኤሌትሪክ ኃይል ለመሸጥ ስምምነት ማድረጓ የሚታወቅ ሲሆን፤ ወደ ኬንያ የሚላከው የኤሌትሪክ ኃይልም በተደረገው ስምምነት መሠረት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ማብራሪያ ገልጿል።
የኢትዮ- ኬንያ የማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ስቴሽን ፕሮጀክት በ334 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው ተብሏል።
የግንባታ ሥራው በ2008 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት እስከ 2000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስታወቁ ይታወሳል።
አምባሳደር መለሰ ዓለም አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ የተለያዩ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራትና ድርጅቶች በመልሶ ግንባታውና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015