በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ጥቅምት 24/2013 የተጀመረው ጦርነት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጥቅምት 23/2015 በሰላም ንግግር ሊፈታ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕውሓት ቡድን መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ኹለት ዓመት ሊሞላው አንድ ቀን ብቻ ሲቀረው ነው በኹለቱም ወገኖች የተመረጡት ተወካዮች በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ባደረጉት የሰላም ንግግር ሕወሓት ትጥቅ እንዲፈታ ስምምነት ላይ የተደረሰው።
ጦርነቱ ሲካሄድ በቆየባቸው ኹለት ዓመታት ውስጥም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ይገመታል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። መሠረተ ልማቶች፤ ማኅበራዊ ተቋማት ብሎም ንብረቶች ለዘረፋና ውድመት ተዳርገዋል።
ይሁን እንጂ፣ ‹‹ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት አይቀርም›› እንዲሉ ከኹለት ዓመት ቆይታ በኋላ ሕወሓት ትጥቅ ሊፈታ በኹለቱ ወገኖች መካከል ባሳለፍነው ጥቅምት 23/2015 ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል ያለውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም ይረዳል ተብሎ በጽኑ ታምኖበታል።
በመንግሥትና ሕወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎም የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት ጀምረዋል። ለአብነትም በምዕራብ ግንባር ማይፀብሪ ወረዳ 250 የሚሆኑ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለመፍታት ተስማምተው ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄ በማቅረብ ወደ ጊዜያዊ ካምፕ እንደገቡ የተለያዩ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።
የሰላም ስምምነቱ ወታደራዊ አመራሮች በአምስት ቀን ውስጥ እንዲገኙ ያዛል በተባለው መሠረትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ታጣቂ አዛዦች ባሳለፍነው ጥቅምት 28/2015 በኬንያ ናይሮቢ እንደተገናኙና የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ውይይት እያደረጉ ነው።
ታዲያ ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለው፤ ጦርነቱ ካስከተላቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች በኋላ ቢሆንም፣ ለኹለት ዓመት ገደማ ርቆ የቆየው ሰላም ብቅ የማለት አዝማሚያ በማሳየቱ ኢትዮጵያዊያን በደስታ ሲፈነድቁ ተስተውለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ሰላም ወዳለባቸው አጎራባች ከተሞች ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችም ወደየቀያቸው ለመመለስ በቅተዋል። ያልተመለሱትም በመመለስ ላይ ናቸው ተብሏል። ከዚህም ባሻገር፣ ከኹለት ዓመት በኋላ የውሃና የመብራት እንዲሁም የስልክ አገልግሎት ያገኙ ከተሞችም አሉ። ሆኖም በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕውሓት መካከል ተደርጓል በተባለው የሰላም ስምምነት ስለወልቃይትና የራያ ቆቦ የወሰን ጉዳይ ግልጽ የሆነ ውሳኔ አለመሰማቱ እንዲሁም ጦርነቱ ያስከተላቸው ችግሮች በአፋጣኝ ምላሽ አለማግኘታቸው በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና እንደፈተናቸው ነዋሪዎቹ በመግለጽ ላይ ናቸው።
ምንም እንኳ ጦርነቱን በሰላም ንግግር ለመፍታት የሚስተዋሉት በጎ ጅማሬዎች ደስ ቢያሰኛቸውም፣ ጦርነቱ ያስከተላቸው አፋጣኝ መፍትሔ የሚሹ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች እንደተጋረጡባቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የጦርነቱ ቀጠናዎች ከስምምነቱ በኋላ
በስምምነት የመፈታት ጉዞ ላይ ያለው የሰሜኑ ጦርነት ትግራይን ጨምሮ አማራ እና አፋር ክልል ላይ ከፍኛውን ጫና አሳርፏል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር በኩል በተለይም ወልቃይት፤ ማይፀምሪ፤ በራያ ቆቦ ወረዳ ቆላማውና ደጋማው ክፍል፤ በዋግኽምራ ዞን የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እና ሌሎች አካባቢዎች በሦስተኛው ዙር ጦርነት ጭምር የተጎዱ ቦታዎች መሆናቸው ይታወቃል። የተወሰኑ የአፋር ክልል ነዋሪዎችም የሦስተኛው ዙር ጦርነት ተቋዳሽ ሆነው ቆይተዋል።
የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ በዚሁ ጦርነት ሳቢያ በምግብ እጥረት ምክንያት ጨቅላ ሕፃናት ሲሞቱ ለማየት አእምሯቸው አልፈቅድ ብሏቸው ራሳቸውን እስከማጥፋት ደረጃ የደረሱበት አጋጣሚ ነበር። እንዲህ ሆኖ ኹለት ዓመት አልፏል። የሆነው ሆኖ በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ አካባቢ ነዋሪዎች ከስምምነቱ በኋላም ቢሆን ከድጥ ወደ ማጥ የሆነ ሕይወት ውስጥ መሆናቸውን ከመናገር አልቦዘኑም።
በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ከነበሩ አካባቢዎች መካከል የኮረምና ዛታ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ከስምምነቱ በኋላም በጦርነቱ ሳቢያ የተከሰቱ ችግሮች አሁንም ዋጋ እያስከፈሏቸው ስለመሆኑ እሮሮ በማሰማት ላይ ናቸው። በኮረምና ዛታ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የቀደመውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ቢያስደስታቸውም በተለይም በምግብ እና በመድኃኒት እጥረት እየተቸገሩ ነው።
ሙሉሰው ጌታነህ የዛታ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እናቶችን ጨምሮ ሕፃናት ተርበዋል ሲሉ የተመለከቱትን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጦርነቱ ምክንያት በመድኃኒት ዕጥረት በተከታታይ መድኃኒት እንዲወስዱ በሕክምና የታዘዘላቸው የኤች.አይ.ቪ ኤድስ፤ የደም ግፊት እና መሰል በሽታ ሕሙማን ሕይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል። አክለውም አካባቢው ከጦርነት ቀጠና ነጻ ወጣ እንጂ፣ የምግብ እርዳታ ማግኘት ባለመቻሉ ነዋሪዎቹ ርሃብ እያንዣበባቸው መሆኑን አንስተዋል።
የዛታ ከተማ ጤና ጣቢያ በሰላሙ ወቅት ሲሰጠው የነበረው የሕክምና አገልግሎት ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር ገደማ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ጥቅምት 28/2015 የቀደመ አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል።
በጤና ጣቢያው በተለይም የኤች.አይ.ቪ ኤድስ፤ የደም ግፊት፤ የስኳር እንዲሁም የሚጥል በሽታ ሕሙማን የሚሆን መድኃኒት እንዳልተሟላ እና 429 ሕፃናት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያሻቸው መሆኑን ከዋግኸምራ ብሔረሰብ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የኮረም ከተማ በጦርነቱ ቀጠና ከነበሩት ቦታዎች መካከል አንዷ ስትሆን፤ ነዋሪዎቹ ሰሞኑን የመብራት አገልግሎት ማግኘት ቢችሉም በምግብ እጥረት እየተፈተኑ ነው። የኮረም ጤና ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም፣ የተለያዩ መድኃኒቶች ባለመሟላታቸው ሳይታከሙ እየተመለሱ መሆናቸውን ወደ ጤና ጣቢያው ያቀኑ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ የሕክምና አገልግሎት ካለማግኘታቸው በተጨማሪ የምግብ እጥረት በመከሰቱ ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ በተለይም እመጫት የሆኑ እናቶች በርሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን በማማረር ይናገራሉ።
በአማራ ክልል ዋግኸምራ ሰቆጣ ዙሪያ የሚገኙ 92 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ቤት ንብረታቸው በከፍተኛ ኹኔታ መውደሙ እንዳሳሰባቸውም የዞኑ ባለድርሻ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምግብን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች የሚያስፈልጓቸው ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ስለመኖራቸው የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ለአዲስ ማለዳ መግለጹ ይታወሳል።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከ500 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሞቱ የሚነገር ሲሆን፤ ምንም እንኳ ጦርነቱ ተቋጭቶ ሰላም ይሰፍን ዘንድ በጎ ጅማሬ ቢኖርም፣ በጦርነቱ ቀጠና ያሉ በርካታ ሰዎች አጣዳፊ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የገፈቱ ቀማሾች ከወዲሁ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
በራያ አላማጣ፤ ዋጃ፤ ራያ ቆቦ ወረዳ ደጋማውና ቆላመው ክፍል አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ የተመለከተቻቸው ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳተጋረጠባቸው ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት መሠረት፣ ከዋጃ እስከ አላማጣ የሚገኙ ቦታዎች በጅምላ መቃብር የተጀቦኑ ናቸው። አንድ ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ የዋጃ ከተማ ነዋሪ፣ ‹‹በራያ አላማጣ ዙሪያ ወያኔ የቀበራቸው ሰዎች እስካሁን ከተገኙት የጅምላ መቃብሮች ቢበልጥ እንጂ አያንስም›› ይላሉ።
አክለውም፤ ‹‹እዚህ የተቀበሩት የኔ ወንድሞችና እህቶች ናቸው›› ብለው ሲናገሩ ሳግ ተናንቋቸዋል። በርካቶች ለህልፈተ ሕይወት ከመዳረጋቸው ባሻገር የነዋሪዎቹ ንብረት ተዘርፎ በማለቁ ድጋፍ ካልተደረገ ርሃብ መከሰቱ አይቀሬ ነው ብለዋል።
የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ስለመቆየታቸው ገልጸው፤ በተለይም በጤናው ዘርፍ አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆኑን አንስተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የሕክምና መገልገያዎች በመውደማቸው በወሊድ ምክንያት ወደ ጤና ተቋም የሚያቀኑ እናቶች መሬት ላይ ተኝተው ሲወልዱ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። በራያ ቆቦ ወረዳ ዙሪያ የሚገኙ ጤና ጣቢያ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ በተቋማት ላይ ከባድ ውድመት እንደደረሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የቆቦ ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ብርሀኔ ተንሳው፣ የጤና ጣቢያው ንብረት በሙሉ በጦርነቱ በመውደሙ ለማኅበረሰቡ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ምንም እንኳ የመብራት አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ከቆዩበት ጨለማ መላቀቃቸው ቢያስደስታቸውም፣ አገልግሎቱ በኹሉም ቀበሌዎች አለመዳረሱ ቅሬታ አሳድሮባቸዋል።
የቆቦ ከተማ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት በየዓመቱ 3 ሺሕ 500 ተማሪዎችን እየተቀበለ የሚያስተምር ቢሆንም፤ የአይ.ሲ.ቲ ተማሪዎች ጨምሮ የሚገለገሉበት ኮምፕዩተር ዕጥረት ስለመግጠሙም ተጠቅሷል።
ከቆቦ ከተማ በስተምዕራብ በኩል የሚገኙት ተኩለሽ እና ሸዎች ማርያም ያሉ ታዳጊ ከተማዎች የመብራትና የስልክ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም። በእነዚሁ ከተሞች የሚገኙ የዕድሜ ባለፀጋ እናቶች እህል ተሸክመው ወደ ወፍጮ ቤት አራት ሰዓት የሚወስድ የእግር መንገድ ሲጓዙ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
በጦርነቱ ምክንያት ሰብላቸው ከወደመ በርካታ ሰዎች መካከል መንግሥት እርዳታ እንዲያደርግላቸው የጠየቁም አሉ። አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ እናት በኹሉም ማሳቸው ላይ የዘሩት አተር እና በቆሎ እንደነበር ገልጸው ታጣቂ ቡድኑ ስላወደመው አሁን ምንም የሚቀመስ የለኝም ሲሉ ተደምጠዋል።
በጦርነት ቀጠና ውስጥ ከነበሩ ነዋሪዎች ንግግር አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው፣ በጦርነቱ ምክንያት በደረሰባቸው በደል ቂም መያዛቸውን ነው። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የ70 ዓመት አረጋዊ፣ ምንም እንኳ የሰላም ንግግር ቢደረግም በግንባር ቀደም ግን ውስጡ በቁርሾ የጠቆረውን ማኅበረሰብ ማስታረቁ ወሳኝ ነው ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
የሥነ ልቦና ባለሙያ ትዕግስት በሱፈቃድ በበኩላቸው፣ በጦርነት ውስጥ ያለፈን ሕዝብ በምክር አገልግሎት በፍጥነት መጠገን ይገባል ብለዋል፤ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
የሰው ልጅ ስጋ በባህሪው በቀል ለማድረስ የተጋለጠ ነው ያሉት ትዕግስት፤ ጦርነት በተፈራረቀባቸው የትግራይ፤ አማራ፤ አፋር እንዲሁም ከሦስት ዓመት በላይ በታጣቂዎች እየታመሱ ላሉት በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አፋጣኝ የሥነ ልቦና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አክለውም፤ በሰላም ስምምነቱ መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ከማስፈታት ጎን በጎን የማኅበረሰቡን ጉዳት መጠገን ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል።
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቀቄ) በበኩሉ፣ የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎች አሁን ባሉበት አማራ ክልል ስር ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ዘንድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት በአፋጣኝ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥቅምት 30/2015 በሰጠው ወቅታዊ መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።
አብን ባወጣው መግለጫ ‹‹የአማራ ሕዝብ ክፋይ የሆኑት እና ከ30 ዓመት በላይ በአማራዊ ማንነታቸው ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመባቸው የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎች አሁን ባሉበት አማራ ክልል ስር ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት በአፋጣኝ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ›› ሲል ነው የጠየቀው።
እናት ፓርቲ በበኩሉ፣ የሰላም ስምምነቱ እሰየው የሚያስብል ጅማሬ ቢሆንም ሕዝብ ስለ ሂደቱ በግልጽ አለማወቁ እንዳሳሰበው ባሳለፍነው ጥቅምት 29/2015 ወቅታዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በድርድሩ ያልተወከሉና በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ “ኢትዮጵያ አሸንፋለች” ብሎ ደጋግሞ በመናገር ለማሳመን ከመጣር ይልቅ የሚያመጣላቸውን በረከት፣ የሚያመጣባቸውን መዘዝ በተለይ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን ማኅበረሰብ በግልጽና በዝርዝር ቀረቦ ማናገር ያስፈልጋል።›› ሲል አሳስቧል።
እንዲሁም፤ ‹‹የድርድሩ ስምምነት ወደትግበራ ከመግባቱ በፊት በፓርላማው ለውይይት እንዲቀርብና እንዲያጸድቀው›› የሚሉት በመግለጫው ተካተዋል። በጦርነት ቀጠና የነበሩ የራያ እና የወልይት አካባቢ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ሕወሓት በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚያነሳባቸው የወልቃይት እና ራያ አካባቢዎችን በተመለከተ ከስምምነቱ በኋላ ግልጽ ማብራሪያ አለመሰጠቱ ከላይ ከዘረዘሯቸው ችግሮቻቸው በተጨማሪ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015