መምህርት፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ናት። በሕጻንነቷ የግእዝ ትምህርትን መማር የጀመረች ሲሆን፣ በዛ ለጋ እድሜዋ ማስተማሩንም አሀዱ ብላ ጀምራለች። በእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋ መምህርነት ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በዲፕሎማ፣ በሥነመለኮት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ የግእዝ ቋንቋ ጥናት ኹለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች። ‹ማኅቶተ ጥበብ ዘልሳነ ግእዝ› የሚል መጽሐፍ በ2006 ለንባብ አብቅታለች።
ከአንደኛ እስከ ዐስረኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች የሚሆኑ የግእዝ መማሪያ መጽሐፍትን ከአስራ አምስት ዓመታት ድካም በኋላ ጥቅምት 20/2015 አስመርቃለች። ለአጸደ ሕጻናት ተማሪዎችና ለ11ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች መማሪያ የሚሆኑ መጽሐፍትንም በ2016 እንደምታስመርቅም ትናገራለች። የአፄ ላሊበላ ባለቤት የቅድስት መስቀል ክብራን ገድልም ወደ አማርኛ ተርጉማ በቅርቡ ለንባብ እንደምታበቃም ገልጻለች።ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት ያገለገለችውና በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን በጋዜጠኝነት በማገልገል ላይ የምትገኘው ኑኀሚን ዋቅጅራ ከአዲስ ማለዳው እሱባለው ጋሻው ጋር በነበራት ቆይታ ስለሥራዎቿ እንዲሁም ስለግእዝ ቋንቋ ያላትን ምልከታ አጋርታለች።
ምንም እንኳን የግእዝ ቋንቋ ተናጋሪ ባልሆንም በግእዝ ቋንቋ አንቱታ እንደሌለ እሰማለሁ። በምንነጋገርበት አማርኛ ደግሞ አንቱታን መጠቀም የተለመደ ነው። ብዙዎችም ሲቸገሩበት ይታያል። እኔስ አንቱ ወይስ አንቺ እያልኩ ልቀጥል?
(ሳቅ!) እንዲህ ካየኸኝም በኋላማ አንቺ እያልክ ቀጥል።
በሰዎች ዘንድ ግእዝ ቋንቋን ከባድ ቋንቋ አድርጎ የማየት አዝማሚያ አለ። እውነት ግእዝ ከባድ ቋንቋ ነው?
የግእዝ ቋንቋ በጣም ግልጽና ቀላል፤ ነገር ግን ትኩረት የሚፈልግ ቋንቋ ነው። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግእዝ በጣም ቀላል ቋንቋ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ እየተነጋገርነው ያለነው ቋንቋ ስለሆነ ወይም ግእዝ የማያውቅ አማርኛ ተናጋሪ ስለሌለ ነው። ምንም እንኳን የስያሜው ትክክለኛነት ጋር ጥያቄ ቢኖረኝም፣ በ33 የአማርኛ ፊደላት ላይ ከምናያቸው ፊደላት መካከል 26 ፊደላት የግእዝ ፊደላት ናቸው። በአንድ ስበሰባ ላይ የአብዛኛው ሰው ድምጽ አሸናፊ እንደሚሆነው ኹሉ ከ33 ፊደላት ውስጥ 26 የግእዝ ፊደላትን የያዘው የፊደል ገበታም የግእዝ የፊደል ገበታ መባል እንዳለበት አምናለሁ።
እንዳልኩት የግእዝ ቋንቋ በጣም ቀላል ነው፤ እየተነጋርን ያለነው ነው። ለምሳሌ ሁሉንም ትተን፣ የምንነጋረው ሁሉ እነዚህን 26ቱን ፊደላት አጣምረን ነው። ስለዚህ ግእዝ የማያውቅ ሰው የለም ብዬ የማምነው በዚህ ነው።
የአማርኛ ፊደላትም ከግእዝ የመጡ ናቸው። ከግእዝ ፊደላት ውጭ የሆኑት ሰባት ፊደላት ናቸው። እሳቱ ሰ ላይ ተቀጥሎ ሸ፣ ተ ላይ ተቀጥሎ ቸ፣ ነ ላይ ተቀጥሎ ኘ፣ ደ ላይ ተቀጥሎ ጀ፣ ጠ ላይ ተቀጥሎ ጨ፣ ዘ ላይ ተቀጥሎ ዠ ሆነ። እነዚህን ነው አማርኛ የምንላቸው። ስለዚህ የግእዝን 26 ፊደላትን እየተጠቀምን ነው። እነዚህ 26 ፊደላት ከተጠቀምን ግእዝን እናውቃለን። እንደ ጥራዝ ነጠቅ የምንጠቀማቸው ነገሮች አሉ፣ አማርኛ አድርገን። ለምሳሌ ዜና የሚለው ቃል ግእዝ ነው። ቤተክህነት፣ ቤተመንግሥት፣ ማኅበረሰብ እነዚህ ሁሉ የምንጠቀምባቸው ግእዝ ናቸው። ግእዝ ቀላል ነው ያልኩት ለዛ ነው።
እውነታው እንደዚህ ከሆነ በሰዎች ዘንድ ከባድ ቋንቋ ሊያስብለው የቻለው ምክንያት ምን ይሆን?
ግእዝን ከባድ ያስባሉት ኹለት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ግእዝ ቋንቋን 90 በመቶ መባል በሚችል ልክ የሚጠቀሙበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መሆናቸው ሲሆን፣ የቤተክርስትያኗ ሥርዓተ አምልኮ የሚከወነው በግእዝ ቋንቋ መሆኑ ቋንቋውን የሥርዓተ አምልኮ ቋንቋ ብቻ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖሩ ነው። ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ በእለት ከእለት እንቅስቃሴ ለመግባቢያነት የሚጠቀመው እምብዛም መሆኑ ነው።
ለዚህም ኹለት መፍትሔ አለው። የመጀመሪያው የግእዝ ቋንቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸምበት ቋንቋ መሆኑን ተገንዝበን፣ ቤተክርስትያኗ የቋንቋው የአደራ እናት መሆኗ እንጂ ቋንቋው የኹሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የአረብኛን ቋንቋ መመልከት ይቻላል። ቋንቋው የእስልምና ሀይማኖት ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸምበት ቋንቋ ቢሆንም፣ ሀይማኖቱን የማይከተሉ ሰዎችም በቋንቋው እንደሚጠቀሙበት መመልከት ይቻላል።
ግእዝን ሀይማኖታዊ ቋንቋ ብቻ አድርጎ መመልከትም ቋንቋውን እንደጎዳው መመልከት ይቻላል። የሌላ ሀይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው ቋንቋውን ሀይማታዊ በማድረግ እንዳይማር አድርጎታል።
ብዙውን ጊዜ ቋንቋ የብሔርና ማንነት መመዘኛ ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚህ አንጻር እንደ ማኅበረሰብ ወይም እንደ አገር ስለ ቋንቋ ያለንን መረዳት እንዴት ትታዘቢዋለሽ?
አንድ ልንገነዘበው የሚገባ ጉዳይ አለ። ቋንቋ ከመግባቢያነት ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም። ቋንቋን ከመግባቢያ ውጭ እንደ ብሔር ስንመለከተው የባህል መግለጫ ነው። ያለንን ትውፊትና ባህላዊ ነገር በቋንቋ ማስተላለፍ እንችላለን። ትልቁ ነገር ግን ብንጽፈውም፣ ብንናገረውም ቋንቋ ከመግባቢያነት ውጭ ምንም ዓይነት ሌላ ነገር የለውም። እኔና አንተ የምንነጋገረው በአማርኛ ስለምንግባባ ነው። በእንግሊዝኛም ብንግባባ መነጋገር እንችላለን። ሆኖም ግን አማርኛ ስለተናገርን አማራ እንግሊዝኛ ስለተናገርን እንግሊዝ ነን ማለት አይደለም። ማንኛውም ሰው ቋንቋን የማወቅ ስጦታ ስላለው የምንናገረው ቋንቋ መግባቢያ ከመሆን ውጭ ሊከፋፍለንም ሊለያየንም አይችልም። እኔ እንደዛ ነው የማምነው።
አንድ ቋንቋ የመጥፋት ወይም የህልውና አደጋ ውስጥ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው?
ከግእዝም አልፎ የቋንቋ ተማሪ ስለሆንኩ አንድን ቋንቋ በኹለት ዓይነት መልክ አደጋ ውስጥ ነው ማለት እንደምንችል እገነዘባለሁ። የመጀመሪያው ቋንቋውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚያደርገው ሰው ሲጠፋና ኹለተኛው ደግሞ የተናጋሪው ቁጥር ሲቀንስ ነው። ይሄ በዓለም ዐቀፍ ደረጃም በቋንቋ ጥናት ውስጥ የሚነገር ነው። ይሁንና ቋንቋውን የአፍ መፍቻ የሚያደርገውና የሚነጋገርበት ሰው መጥፋቱ ቋንቋውን ይገድለዋል ወይ? የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ነው።
አንድ ተናጋሪ ብቻ ያለው ቋንቋ ተጨማሪ ተናጋሪዎች የማፍራት እድል አለው። የተናጋሪው ቁጥር ቀንሷል እንጂ ሞቷል ማለት አንችልም። እንደግል አመለካከቴም በተናጋሪዎች መቀነስ ቋንቋ አይሞትም። አንድን ቋንቋ ሞተ ለማለት የሚያስችለን ስለዛ ቋንቋ ምንም ዓይነት ጥንተ ታሪክ መናገር የሚችል ሰው ማግኘት ሳይቻል ሲቀር ብቻ ነው።
በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ዘንድ የግእዝ ቋንቋን ከአምልኮታዊ ጥቅም ውጭ እንደ መግባቢያነት ከመጠቀም አንጻር ያለውን ሁኔታ እንዴት ትገልጭዋለሽ?
በሥራ ምክንያት ለሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅርብ ነኝ። አንዳንዴ እኔም የምታዘበው ነገር አለ። ነገር ግን አይነጋገሩም የሚለውን ነገር መወሰን አንችልም። የሆነ ምስጢር ነገር ሲኖራቸው በእርግጠኝነት በግእዝ ይነጋገራሉ። ይሁንና በኹሉም ቦታ በግእዝ አይነጋገሩም። ለዚህም ምክንያት ያላቸው ይመስለኛል። አንተ የምትነጋገረውን ቋንቋ መነጋገር በማይችሉ ሰዎች መሀል ስትሆን ምንም እንኳን ሌላ ተናጋሪ ብታገኝ ለሌላውም ሰው እንዲሰማ በሚል ኹሉም በሚያውቀው ቋንቋ እንደምትናገረው ኹሉ፣ ሊቃውንትም እንደዛ የሚያደርጉ ይመስለኛል። እንደማንኛውም ቋንቋ ሰፋ ተደርጎ ባይነገርም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሲነገር ግን እሰማለሁ። ለዚህም የዐይንም የጆሮም ምስክር ነኝ።
የግእዝ ቋንቋን ለማስተዋወቅና ለመጠቀም ምን መደረግ አለበት? ካንቺ ተሞክሮ ጋር አያይዘሽ ብትነግሪኝ!
ቋንቋው ወደፊት በምን መልክ መነገር አለበት ለሚለው፣ አንዳንዴ መስማትና ማየት በጣም ልዩነት አለው። ማሰብና መሆንም ልዩነት አለው። የግእዝ ቋንቋን እኔ ልጅ ሆኜ ሰማሁ አልልም፤ እግዚአብሔር ፈቅዶና እድለኛ ሆኜ ነው። አንዳንዴ ሳትፈልጋቸው የሚፈልጉህ፣ ሳትመርጣቸው የሚመርጡህ ብዙ ነገሮች አሉ። እኔ ግእዝ ቋንቋ ሳልፈልገው የፈለገኝ፣ ሳልመርጠው የመረጠኝ ቋንቋ ነው ብዬ ነው የማስበው። ይህን ያህል ርቀት የአቅሜን ልሂድ የምለው ለዛ ነው።
ይህን ስል፣ የውዳሴ ከንቱ ንግግር አይደለም። ትክክለኛውን ነው። አንዳንዴ ነባራዊውን ሁኔታ አስቀምጠን መሄድ ግዴታችን ስለሆነ ነው።
የግእዝ ቋንቋን ስናስብ የሰሜኑ አካባቢ ተወላጆች ቋንቋ እንደሆነ ነው የምናስበው። የቤተክርስትያንና ቤተክህነት ቋንቋ እንደሆነ፣ የወንዶች ትምህርት እንደሆነ ሲነገር ነው የምንሰማው፤ አሁንም እየሰማን ያለነው። ግን የጾታ ልዩነት እንደሌለው ቀድሞውንም በነእማሆይ ገላነሽ ታሪክ ዐይተናል። የጾታውን እነሱ አፍልሰዉታል። የሀይማኖት ደግሞ እንዳንል የውጪ አገራት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ አይደሉም። እኛም ጋር ያሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የሚማሩት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ብቻ አይደሉም። ሌላው በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ሰሜኑ የሚባለው፣ እኔ እንደምሳሌ መወሰድ እችላለሁ። ንጹህ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፣ ከአዲስ አበባም መርካቶ ተወልጄ ያደግሁ ነኝ። ሰሜኑን ያወቅሁት አሁን በሚድያ ሥራ አጋጣሚ ነው። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አፈረሰ። ስለዚህ ግእዝ የሁሉም ነው የሚለው ነገር መጀመሪያ ያስማማናል። ግእዝ የኢትዮጵያም የዓለምም ነው።
ግእዙን በደብረ ገሊላ አማኑኤል ካቴድራል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሕጻነት ጀምሮ የተማርኩት እዛ ነው። እዛ እየተማርኩኝ እያለ መጋቤ ምስጢራት ጌድዮን መኮንን የተባሉ የግእዝ ሊቅ የቤተክርስቲያኑ የቅኔ መምህር ናቸው የግእዝ ትምህርትን ያስተምሩን የነበረው። እኔ እዛ ትምህርት ቤት ግእዙን ፈልጌ አልገባሁም። ትምህርቱን ፈልጌ፣ ለቤቴም ቅርብ ስለሆነ ከሕጻንነት አንጻር ቤተሰቦቼ አርቀው ማስገባት ስላልፈለጉ ነው እዛ ትምህርት ቤት ያስገቡኝ። እዛ ስገባ ግን ትምህርቱን ሙሉ ለሙሉ አገኘሁት።
ሕይወት ከፍለውልናል። ጠዋትም ማታም እስከ 9፡30 ያስተምሩናል። ከዛ በኋላ ደግሞ የግእዝ ፍላጎት ያላችሁ ብለው በግል ያስተምሩናል። እና ያንን እየተማርኩኝ ነው እዚህ የደረስኩት። ስለዚህ ቀላል የምልህም የሕጻንነት እድሜ እያሾፍን ተምረንም እኔ ውጤታማ ሆኜበታለሁ፤ ደግሞም ውጤታማ ልጆችን ዐይቼበታለሁ። ከዛም እርሳቸው ሲያርፉ የቤተክርስትያኑ ቅኔ መምህር ሊቀ ኅሩያን መሀሪ መኮንን ሲቀጠሩ፣ ከ1ኛ ደረጃ እስከ 6ኛ ክፍል ለነበረው ትምህርት ቤት ደግሞ የግእዝ መምህራን አስፈለጉ። በዛን ሰዓት እኔ ማትሪክ መፈተኔ ነበር፣ ውጤት እንኳ አልያዝኩም ገና። ግእዝን እዚህ እርሳቸው ጋር እየተማርኩኝ፣ የክፍል እኩዮቼንና ትልልቆቹን ሁሉ ግእዝ አስተምር ነበር።
ድፍረትም ነው። ድፍረት ስል ስለሌለህ አይደለም። ሲፈልግህ ሲሰጥህ ነው። ሰንበት ትምህርት ቤት በዛን ሰዓት የነበሩ ታላላቆቼ አምነው እንዳስተምር የፈቀዱልኝ ተሰጥታለች ብለው ስላመኑበት ነው። በዛን ሰዓት ሰንበት ትምህርት ቤት ሳስተምር የምስክር ወረቀት የሰጡኝ አባት አቡነ እንጦንስ ዛሬም ዐስሩን መጽሐፍት ሳስመርቅ በዛ ቦታ ላይ ተገኝተው መጽሐፌን በመመረቃቸው በጣም እድለኛ ነኝ። ያኔ የደብሩ አስተዳዳሪ ነበሩ። ዛሬ እርሳቸው ጵጵስና ደረጃ ላይ ደርሰው እኔም እዚህ ደርሼ፤ መጥተው መጽሐፉን ሲመርቁት በጣም ነው የተደሰትኩት። ብጹዕ አባታችን አቡነ ፊሊጶስም ቅድስት ሥላሴ አስተማሪዬ ነበሩ። ያስተማሩን አባቶች እኔ እዚህ ጋር ስደርስ እነሱም በቦታው ላይ ተገኝተው የዚህ ደስታ ተካፋይ በመሆናቸው ከምንም በላይ ውስጤ የተደሰተው በዛ ነው።
ለማስተማር እግዚአብሔር ፈቅዶ ገባሁኝ። ከአንድ እስከ ስድስት ሳስተምር ቆየሁ። አንዳንዴ ሥም ያስፈልጋል። መምህር ከተባልክ ሙያው ውስጥ መግባት አለብህ። ዝም ብሎ የልምድ መምህርነት አያስሄድም።
ልክ የማትሪክ ውጤቴን ስቀበል ቀጥታ፣ እዚህ ጋር ይህን ትምህርት ካቆምኩኝና የቀን መማር ከጀመርኩኝ ነገ ይህን እድል ላላገኘው እችላለሁ አልኩኝ። አንዳንዴ የተፈቀደልህን ነገር በሰዓቱ ነው መጠቀም ያለብህ። በማታ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የኢንግሊዘኛና የአማርኛ ቋንቋ የዲፕሎማ ተማሪ ሆኜ ገባሁ።
እዛ እየተማርኩኝ ሌሰን ፕላኑን፣ ዓመታዊና ሳምንታዊ እቅዱን በግእዝ ነበር የማወጣው። እና እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ሦስት መጽሐፍት አዘጋጀሁ። ለአንደኛ እና ኹለተኛ በአንድ መጽሐፍ፣ ሦስተኛና አራተኛ አንድ ላይ፣ አምስተኛ እና ስድስተኛ አንድ ላይ አድርጌ መጽሐፍ አዘጋጅቼ ነው ሳስተምር የነበረው። ትምህርት ቤቱ ቤተክርስትያን ጊቢ ውስጥ ቢሆንም ሁሉንም ነው የሚያተስምረው።
በወቅቱ ከአዲስ አባባ ትምህርት ቢሮ የመጡ ባለሙያዎች እነዚህን መጽሐፍት ዐይተው በዚህ መልክ ተዘጋጅቶኮ ለትምህርት ቢሮ ቢቀርብ ትምህርት ቢሮ ከታች ጀምሮ ግእዝን አስተምሮ ለመሄድ ደስተኛ ነው። በቤተክህነት ደረጃ በግእዝ ባለሞያዎቹ ዘንድ ይህ ነገር አለመዘጋጀቱ እንጂ በዚህ መልክ ቢዘጋጅ አሉኝ፤ ቃል በቃል።
ወዲያው ያ ነገር ውስጤ አቃጨለ። ለካ ሴት ልጅ ሥም ታስጠራለች የሚለውን አሰብኩ። እኔም ይህን ብቀጥል የመምህሮቼን ሥም ላስጠራ ነው። ከዛ በኋላ ቀጠልኩበት። ጳጉሜ 3/1999 ዲፕሎማ እንደተመረቅኩኝ 2000 ላይ እግዚአብሔር ፈቅዶ ወደ አቡነ ጎርጎሪዎስ የማኅበረ ቅዱሳን አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ለመቀላቀል እድሉን አገኘሁ።
በኢንግሊዘኛና አማርኛ በዲፕሎማዬ ተወዳድሬ ነው የገባሁት። የሥራ ልምዴን ዐይተው የግእዝ መምህር ፈልገን አላገኘንም፤ አንቺ ልታስተምሪልን ፈቃደኛ ነሽ ወይ ብለው ጠየቁኝ። እግዚአብሔር ፈቅዶ አቡነ ጎርጎሪዎስ የመጀመሪያ የግእዝ መምህር ሆኜ ቀጠልኩ። እዚህ ጋር በሦስት መጽሐፍ የጀመርኩትን በተንኩት። 2001/2002 ላይ በትኜው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ አራት መጽሐፍ፣ 2003 አምስተኛ እና ስድስተኛ፣ 2004 ላይ 7ኛ እና 8ኛ፣ 2005 ላይ 9ኛ እና 10ኛ አድርጌ እስከ 10 ታትሞ ልጆቹ መጠቀም ጀመሩ። ከዛ በማኀበሩ በሰዓቱ ከነበሩ ኃላፊዎች ጋር።
ምንድን ነው የምትፈልጊው ሲሉ፣ ይህ ነገር ከግለሰብ ይልቅ ተቋም ነውና ማኅበሩ፣ በተቋም ደረጃ እውቅና አሰጥቶት፣ በሊቃውንትም በትምህርት ቢሮም አስገምግሞ፣ ሁሉም ሰው የሚማርበት እንዲሆን ነው አልኩኝ። በዚህ ተነጋግረን ለሙከራ 2005 ላይ ልጆቹ እንዲማሩበት ተደረገ።
ሴት ልጅ ሥም ታስጠራለች የሚለው ሁሌ ያቃጭልብኛልና፣ ከዚህ በፊት ግን መጀመሪያ አንድ መጽሐፍ በመምህሬ ሥም መጻፍ አለብኝ ብዬ፣ ‹ማኅቶተ ጥበብ ዘልሳነ ግእዝ› የሚለውን 293 ገጽ የሚሆነው መጽሐፍ 2006 ላይ አሳተምኩኝና መታሰቢያነቱን ለመጋቢ ምስጢር ጌድዮን መኮንን አድርጌ ሥማቸውን አስጠራሁ። መጽሐፉ ሲመረቅ ዐስሩ መጻሕፍት በመጽሐፉ ጀርባ ላይ በዚህ በዚህ ዓመት ያለቁ ተብለው ታትመው ነበር።
ልክ መጽሐፉ ሲመረቅ፣ ከእኔ የተሻለ ትውልድ እንደሚወጣ ያወቅሁት ግእዝ ያስተመርኳቸው የኔ ተማሪዎች (የሰንበት ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች) የመጽሐፍ ምረቃው ላይ በግእዝ ድራማ ሠርተው አቀረቡ። ብዙ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዉት ነበር። ልጆቹ ድራማ ሠርተው መጽሐፌን አስመረቁ። ስለዚህ ግእዝ ቋንቋ ትውልዱ በጣም ወዶት፣ ተግባብቶበት እንደሚማረው አወቅሁ።
ከዛ በኋላ መጽሐፉን ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ጎርጎሪዮስ አሁን እየተማሩበት ነው። ያንን እየተሄደበት የበለጠ ማሻሻል ያስፈልገኛል አልኩኝ፤ ትላንት የነበረ አእምሮ እና ዛሬ ያለው ወይም ነገ የሚኖረው የተለየ ነው። ትምህርት ቤቶችንም ከዛ በኋላ አስተምሬበታለሁ።
ያንን እያስተማርኩ በየጊዜው በተማሪዎቹ ደረጃ ነገሮችን በምን ዓይነት መልኩ፣ ከቀላል ወደ ከባድ ይደግ፣ ትውልዱ ቀላል መሆኑን እንዲያውቅ እንዴት እናድርግ የሚለውን እየነካካሁ መጨረሻ ላይ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ዲግሪዬን ስይዝ በተያያዘ መልኩ ግእዙ ላይ ያለኝን ነገር የበለጠ እንዳዳብር ሆንኩኝ። በዛም ለልጆቹ ይህ ትምህርት ከሕጻናቱ በምን ይለያል፣ ዩኒቨርሲቲ ላይ ሲገቡ በዚህ ደረጃ ነው የሚማሩትና ታች በምን መልኩ መምጣት አለባቸው የሚለው በተመለከተ ሌላ ግንዛቤ ሰጠኝ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፊሎሎጂ ላይ ኹለተኛ ዱግሪዬን በግእዝ የጥንት ብራና መጻሕፍት ጥናት ላይ ስሠራ፣ የበለጠ ደግሞ ከብራናው ጋር ያሉትን ነገሮች ስታየው፣ ለልጆቹ በምን መልኩ በሚመጥን እየወረደ እንደሚሄድ ዐየሁ። እግዚአብሔር ሲፈቅድ ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ያሉት መጻሕፍት ደግሞ፣ ያው ትላንት የተጀመረ ቢሆንም ግእዝ አለ የለም በሚባልበትና አልፎ ተርፎ የግእዝ ፊደል ከውጪ ከግሪክ የመጣ ነው እየተባለ በሚነገርበት ሰዓት ለማስመረቅ በቃሁ።
ሲጀመር የግሪክ ታሪክና የኢትዮጵያ ታሪክን ማወቅ በራሱ የግእዝ ቋንቋ መነሻው የት እንደሆነ ይታወቃል። አንዳንድ ጊዜ ታሪክን ባለማወቅ የምንሰጣቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እናም ያንን ነገር ስረዳው፣ የእኛ ድክመት ነው። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች ድክመትም አለ። ይህን በግልጽ ነው መነጋገር ያለብን። በብዙ መልኩ ብዙ የግእዝ ሊቃውንት እንዳሉን አውቃለሁ። እኔ ይህን ያደረግኩት አንድ ጠጠር እንደመጣል ነው። በጣም ብዙ እድፍና ጉድፍ ሊኖረው ይችላል። ሽንፍላ እና ጽሑፍ እያደር ነው የሚጠራው፣ በአንዴ አይጠራም።
ግን ኹለት ነገሮች አስባለሁ። አንደኛ እኛ መሥራት የሚገባንን ነገር እርሷ አዘጋጀችው፣ ከእርሷ የተሻለ ማዘጋጀት አለብን በሚል መንፈሳዊ ቅናት ተነሳስተው የሚያዘጋጁ አባቶችና ወንድሞች እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ። ኹለተኛ ይህን ነገር አርሞ ከዚሀ የበለጠ መጠናከር አለበት ብለው የሚሰጡት ሐሳብ ይኖራል ብዬ አስባለሁ።
ምክንያቱም፣ እኔ እየሔድኩ ያለሁት እስከ 10ኛ ክፍል ነው። አጸደ ሕጻናት፣ (አንደኛ፣ ኹለተኛና ሦስት ዓመት) እንዲሁም 11ኛ እና 12 ክፍልን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየሠራሁ ነው። 2016 ላይ ከአጸደ ሕጻናት እስከ 12ኛ ክፍል በትምህርት ቢሮ ደረጃ፣ ቢሮው ከሊቃውንት ጋር ተነጋግሮ መታተም ያለበትን የትምህርት ባለሞያዎች ዐይተውና አርመዉት፣ ትምህርት ቢሮ ራሱ ተረክቦ ለትውልድ መስጠት አለበት። እኔ አንድ ጠጠር ነው ያስቀመጥኩት። ያለንን ነገር አስረክቤአለሁ። ከዚህ በላይ እኔ መሄድ አልችልም። ምክንያቱም ይህ የአገር፣ የትምህርት እና የማኅበረሰብ ጉዳይ ነው።
ግእዝን የመማር ጠቀሜታ ምንድን ነው?
ትውልዱ መማር አለበት። የግእዝ ቋንቋን መማሩ ጥቅሙ ምንድን ነው ነው ዋናው። እስከ አሁን ሳይማር የቆየው ሰው ምን ተጎዳ፣ ነገስ የሚማረው ሰው ምን ይጠቀማል የሚለው ላይ ነው ዋናው መሠረታዊ ነገራችን መሆን ያለበት። ባለመማራችን ማንነታችንን አጥተናል። የግእዝ ቋንቋን ባለማወቃችን ኢትዮያዊነታችንን አጥተናል። ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱነ አይቀይርም የሚባለውን አጥተነዋል።
ብዙ ነገሮችን አልፈን እርስ በእርስ እስከ መጠፋፋት የደረስነውኮ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ስላጣነው ነው። ኢትዮጰያዊ ማንነታችን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሆነው በኖሩ ወገኖቻችን ዘንድ ተጽፎ ያለ ታሪኩ ትውፊቱ፣ እውቀቱ፣ ጥበቡ፣ ምስጢሩን ስናውቀው ነው። የኢትዮጵያ ክብሯ ታምቆ በግእዝ ውስጥ ነው ያለው። ሊቃውንቱ በግእዝ መጽሐፍ ጽፈው አስቀምጠዉታል። ያንን ነገር ባለማወቃችን ተጎድተናል። አሁን ይህ ቀጣይ ትውልድም እንዳይጎዳ ኢትዮጵያን ማንነቱን አገራችንን እንዲያውቅ፣ ወደትላንት ማንነታችን እንድንመለስ ታሪካችንን ማወቅ አለብን። እነዛ ደግሞ የግእዝ መጽሐፍት ውስጥ ነው ያሉት።
ሴቶችን በተለያየ መስክ ጎልተው ስንመለከት እንደ አዲስ መጠየቃችን አይቀርም። በቋንቋ ዘርፍ በተለይም በግእዝ ቋንቋ በማስተማርም ሆነ በመማር የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?
በእርግጥ ባልሰጠነው ነገር ላይ አስተያየት መስጠት ይከብዳል። ነገር ግን እኔ ባለኝ ተሞክሮ ከመጋቤ ምስጢር ጌድዮን መኮነን ግእዝ ሲያስተምሩን በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረን ሴቶች ነበርን። በዚህም ምክንያት “ወንድ ብትሆኑ ሥሜን ታስጠሩ ነበር” በማለትም ይናገሩ ነበር። ይህም ሴቶች በግእዝ ትምህርት ብዙም ካለመቀጠላቸው የተነሳ ነበር። ስድስት ዓመታትን ባስተማርኩበት በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤትም ሴቶች በግእዝ ትምህርት ውጤታማ እንደሆኑ ዐይቻለሁ።
ወንዶች በአብነት ትምህርትና በሌሎች የቤተክርስትያን ትምህርቶች ቋንቋውን መማር እንችላለን የሚል አማራጭን ስለሚይዙና ሴቶች ደግሞ ግእዝን ለማወቅ የሚያገኙትን ትምህርት በአግባቡ መማር እንዳለባቸው ስለሚያስቡ፣ ያላቸውን እድል በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ተመልክቻለሁ።
ከዚሁ ጋር አያይዤም ለመናገር የምፈልገው እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ሰዎች አገራትን አቋርጠው ግእዝን ለመማር የሚመጡ ሰዎችም አሉ። የኔ መጽሐፍትም ምንም እንኳን በክፍል ደረጃ ቢቀመጡም ማንኛውም ግእዝን መማር የሚፈልግ ሰው ቋንቋውን ሀ ብሎ መማር እንዲችል የሚያደርጉ ናቸው። በዚህም ማንኛውም ሰው ግእዝን ቢማር መልካም ነው እላለሁ። ሚሊኒየሙን ባከበርንበት 2000 ዓመተ ምህረት በትላልቅ ቢልቦርዶች የግእዝን ቁጥር ስንጽፍ ስህተቶችን ሠርተናል። ይህም ሊቃውንት ባሉባት አገር የማይጠበቅ ነው። የራሳችንን ቋንቋ በአግባቡ መጠቀም አለብን።
እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ግእዝን በትምህርት ቤቶች ማስተማር አለብን። በዚህም የትናንት ማንነታችንን መመለስ አለብን። በትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችም ይህንን በመወስን ታሪክ እንዲሠሩ እጠይቃለሁ።
ቋንቋውን ለማተማር መምህራን ያስፈልጋሉ። ይህንን ቋንቋም በአግባቡ ማስተማር የሚችሉ በቂ መምህራን አሉ ብለሽ ታስቢያለሽ?
አንድን ትምህርት ለመጀመር ብቁ የሆነ መምህር እንደሚያስፈልገው አያጠራጥርም። ለመጀመሪያ ያህል በቂ መምህራን እንዳሉ አስባለሁ። የአብነት ትምህርት ከመማር አልፎ የሚያስተምሩ፣ በተለያዩ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት የተማሩ ሰዎችን የማስተማር ሥነ ዘዴን በማሠልጠን ብቁ መምህራን ማድረግ ይቻላል። ይህም ለተወሰኑ ዓመታት ይጠቅመናል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን በእነዚህ መምህራን የተማሩ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ትምህርታቸውን ጨርሰው መምህር የሚሆኑ ተማሪዎችን ማግኘትም እንችላለን።
የመጽሐፎችሽ የወደፊት እጣ ፋንታ ምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እነዚህን መጻሕፍት በመጠቀም በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተገምግሞ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያነት እንዲውሉ እመኛለሁ። ለዚህም ቤተክርስቲያን የመጻሕፍቱ ባለቤት ሆና ለትምህርት ሚኒስቴር እንድታስረክብ ምኞቴ ነው። በዚህም ዙሪያ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ቤተክርስቲያን የግእዝ ቋንቋ የአደራ እናቱ እንደሆነችው ኹሉ እነዚህን መጻሕፍትም ለሕዝብ በአደራ እንድታስተላልፍ እፈልጋለሁ።
አስሩም መጽሐፍት በኢትዮ ፋጎስ የመጽሐፍት መደብር እያንዳንዳቸው በ130 ብር የሽያጭ ዋጋ ይገኛሉ። ከዚህ በተረፈም በየደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መጽሐፍቱን ለማሰራጨት እየተሠራ ነው። ለመግዛት የፈለገም ሰው በእነዚህ አማራጮች ማግኘት ይችላል።
እነዚህ መጻሕፍት ሊቃውንትን እንደ ማንቂያም መታየት አለባቸው። ለ15 ዓመታት በጊዜ ሂደት የተጻፉ መጽሐፍት ናቸው። በየጊዜው የተሻሻሉ መጽሐፍት ናቸው። ይሁንና ሌሎች ሊቃውንትም የበኩላቸውን ተወጥተው መጻሕፍትን ማዘጋጀት አለባቸው።
እኔ እንደግል መሄድ እችላለሁ። የግእዝ ቋንቋ ጉዳይ ግን አገራዊ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በትብብር የግእዝ ቋንቋን ጉዳይ መከታተል አለብን። ኑኀሚን ይሄን አድርጋለች እንዲባል ሳይሆን አገራችንን ወደ ማንነቷ ትመለስ ዘንድ የግእዝ ቋንቋን ማስተማር አስፈላጊ ነው።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015