መጤው የወባ ትንኝ ወረርሺኝ

0
1707

የወባ በሽታ በሞቃታማ አካባቢዎች በስፋት በሚራቡ ትንኞች የሚከሰት ከዓለማችን ገዳይ በሽታዎች በቀዳሚነት የሚሰለፍ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካቶችን በየዓመቱ ለሞት የሚዳርገው ይህ በሽታ እንደየወቅቱና አካባቢው እየተፈራረቀ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

ከሠሞኑ በአፍሪካ የተከሰተ አዲስ የወባ ወረርሺኝ የነበረውን ስጋት በመጨመር መጠነ ሰፊ ርብርብ እንዲደረግ እያስገደደ ነው። በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ያሳወቀው የዓለም ጤና ድርጅት ከአገራቱ በቀዳሚነት የተጠቃችው ደቡብ ሱዳን ናት ሲል አሳውቋል።

በፈረንጆቹ 2021 ብቻ በወባ በሽታ በዓለም ዙሪያ ከተጠቁ 228 ሚሊዮን ሰዎች 95 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካዊያን ናቸው። ከእነሱም ውስጥ 600 ሺሕ ያህሉ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተወካይ ተናግረዋል። አንደተቋሙ የአንድ ዓመት ሪፖርት ከሆነ፣ በበሽታው ይጠቃሉ ተብለው ከተገመቱት ቁጥር አኳያ በየቀኑ ኻያ አፍሪካዊያን በወባ በሽታ ሳቢያ ይሞታሉ።

በወባ በሽታ ከሚጠቁ የአፍሪካ አገራት መካከል ደቡብ ሱዳናዊያን ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ያመላከተው ጥናቱ፣ በአማካይ 10 ሺሕ የአገሪቱ ዜጎች በየቀኑ በወባ ትንኝ ተነክሰው በሽታው እንደሚይዛቸው ነው። ይህ የተነገረው አገሪቱ በየዓመቱ በምታካሂደውና ዘንድሮ “ስቶፕ ማሌሪያ” በሚል መሪ ቃል ሠሞኑን በተካሄደው ጉባዔ ነው።

ደቡብ ሱዳናዊያን በወባ መጠቃታቸው አዲስ አይደለም ያለው ተቋሙ፣ ወረርሺኙን ለማስቆም በተናጥል ከመሞከር ይልቅ የጋራ መፍትሄ ላይ መረባረብ እንደሚገባ ጠቁሟል። አብዛኞቹ የበሽታው ተጠቂዎች በድህነት የሚኖሩና መከላከያውን ማግኘት የማይቻላቸው ከመሆናቸው በላይ፣ ሕክምናውን ማግኘት የሚቸግራቸው የገጠር ነዋሪዎች እንደሆኑ ተነግሯል።

አፍሪካ እንደአኅጉር የወባ በሽታ ተጠቂዎች የሚበዙባት እንደመሆኗ ከምታጣው የሰው ሕይወት በተጨማሪ በበሽታው ሳቢያ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ ይነገራል። በሽታውን ለመከላከል በየዓመቱ ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ባሻገር፣ በሽታው ያለባቸውን ለማከም እጅግ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ይህ ብቻ ሳይሆን የታመሙ ቤተሰባቸውን ለማሳከምም ሆነ ለመንከባከብ ቤተሰቦች ከሚያወጡት ገንዘብ በተጨማሪ፣ በሕመሙ ሳቢያ የሚቀርባቸው ገቢም የትየለሌ እንደሆነ ይገመታል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ትንበያ ከሆነ፣ የወባ በሽታ አጠቃላይ አፍሪካን በየዓመቱ ቢያንስ ኹለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያስወጣታል። በዚህም ሳቢያ ለአኅጉሪቱ ድህነት አባባሽ የሆነ ዋና ምክንያት ተደርጎም እንደሚወሰድ ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ አፍሪካን ከሚያሰጋት የወባ በሽታ ወረርሺኝ ለመታደግ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ በየጊዜው ቢነገርም፣ ወጥ የሆነ ድጋፍ የሚያደርግ ባለመኖሩ በሽታውን እንደሌሎች ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አለመቻሉ ይነገራል። በአንድ አካባቢ ብቻ በመታገል ውጤታማ እንደማይኮን ስለሚታመንም፣ ዓለም ዐቀፍ የሆነና ቀጣይነት ያለው የትብብር ዘመቻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። መፍትሔ የሚባል አንድና ኹለት አማራጭ ብቻ ሳይሆን ቅርጫት ሙሉ የመፍትሔ አማራጮች ቀርበው ርብርብ ማድረግና መደጋገፍ አስፈላጊ መሆኑም ሲነገር ይደመጣል።

የየአገራቱን የጤና ተቋማት ማዘመንና ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አገራት ተቋሞቻቸውን ብቁ እንዲያደርጉ መታገል ቀዳሚው እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል። ለበሽታው መከላከያ የሚሆኑ አጎበርን የመሳሰሉ መከላከያዎችንና መድኃኒቶች በየአካባቢው ለማዳረስ አስቀድሞ ዝግጅት ማድረጉም ወሳኝ ሂደት ነው። መከላከያ አማራጮችንም ሆነ መታከሚያውን ለማግኘት የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድም አስፈላጊ ግብዓት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ይጠቁማል።

በተለይ በዝናባማ ወቅቶች ሳቢያ ጎርፍና የውሃ መጥለቅለቅ በሚከሰትበት ጊዜ የትንኞቹ እርባታ በስፋት እንዳይከሰት፣ እንዲሁም መንገዶች ተዘጋግተው የመከላከያ መንገዱንም ሆነ ሕክምናውን እንዳያስተጓጉሉ ቅድመ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን መከተል እንደሚበጅ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

 ‘‘Zero Malaria Starts with Me’’ በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ከ4 ዓመት በፊት በሞሪታኒያ በተካሄደ ጉባዔ የተጀመረው የወባ በሽታ ስርጭትን የመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውጤት እንዲያመጣ ተግባራዊ መደረግ የሚጠበቅባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተጠቁሟል። ከ8 ዓመት በኋላ ለመድረስ የታቀደው ግብ እንዲሳካ በየጊዜው እንዲሠሩ የሚጠበቁትን ቃል የተገቡ እንቅስቃሴዎች አገራት መተግበር እንደሚጠበቅባቸውም ተቀምጧል።

እንቅስቃሴው የወባ በሽታ ወረርሺኝን ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካዊያን ጉዳይ የሆኑትን የሳንባ ነቀርሳንና የኤድስ በሽታንም ለመግታት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማቀላጠፍ ቃል የተገባበት ነው።

በተገባው ቃል መሠረት የአፍሪካ አገራት ለሚያሰጓቸው ወረርሺኞች መከላከያ ብለው የሚይዟቸውን በጀቶች በከፍተኛ መጠን እንዲያሳድጉ ይጠይቃል። አገራት ብቻም ሳይሆኑ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትም ሆኑ ግብረሰናይ ተቋማትና አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የበለጠ ትኩረትም እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው።

በድጋፍ ብቻ የሚከናወን የመከላከል እርምጃ እንዳይሆንና በተወሰኑ ተቋማት ብቻ ተገድቦ እንዳይቀርም፣ ባለሀብቶች በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ ግብዐቶችን በማምረቱ ዘርፍ በሰፊው እንዲሰማሩና ያለውን እጥረት እንዲቀርፉ ተጠይቋል። ስለሕክምናውም ሆነ በሽታውን ለማጥፋት የሚደረጉ ምርምሮችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሚናገረው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የሚደረጉ ማናቸውም ድጋፎችም ሆኑ ተግባራት በጊዜ በሚያስፈልጉበት ወቅት ካልተደረጉ ፋይዳቸው አናሳ እንደሚሆን አመላክቷል።

ኢትዮጵያና ወባ በሽታ

ከአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን 52 በመቶ የሚሆኑት ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ማሌሪያ ኮንሶርቲየም የተባለ ተቋም በድረ ገጹ እንዳመላከተው፣ በኢትዮጵያ በወባ በሽታ ከሚጠቁት ኢትዮጵያዊያን መካከል በደቡብ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ነው። ከአጠቃላይ ተጠቂዎች 18 በመቶው በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሆኑ ይጠቁማል።

በዓለም ዙሪያ የሚታወቁ አራት ዓይነት የወባ በሽታ አምጪ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣ እንደልዩነታቸው የገዳይነት መጠናቸውም ይለያያል። አፍሪካ ከምታውቃቸው ዝርያዎች የተለየና ገዳይ የሆነ አዲስ ዝርያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መገኘቱ ሲነገር ቆይቷል።

ይህ በከፍተኛ መጠን ተስፋፊ ነው የተባለ ዝርያ ከህንድ የመጣና በቀላሉ የሚዛመት መሆኑንም ባለሙያዎች ሲናገሩ ቆተዋል። ጅቡቲን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ዝርያው ሲገኝ ቆይቶ ዘንድሮ ያልተጠበቀ ወረርሺኝ ማስከተሉም ሲነገር ነበር። በተለይ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በቅርቡ የተከሰተውና በርካቶችን ያጠቃው የወባ ወረርሺኝ ከህንድ የመጣው የወባ ትንኝ ዝርያ ሳቢያ የተከሰተ መሆኑን የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ጭምር ሲዘግቡት የነበረ ነው።

“Anopheles stephensi” በተሰኘ የወባ ትንኝ ዝርያ አማካኝነት በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው ይህ ዝርያ ከተለመደው የተለየ መሆኑ ተነግሯል። ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው ድረገጽ ይፋ እንዳደረገው፣ ይህ ተስፋፊና ወራሪ ዝርያ እንደተለመዱት የወባ ትንኞች እርጥበትን ተከትሎ የሚስፋፋ ሳይሆን በደረቅ ወቅትም መኖር የሚችል አደገኛ ዝርያ እንደሆነ ነው።

ይህም በሽታውን ለመከላከል የሚደረግ ዘመቻን እጅግ አዳጋች ያደረገው ሲሆን፣ የተጠራቀመ ውሃን በማጥፋት አልያም ኬሚካል በመርጨት ይደረግ የነበረውን የመከላከል ተግባር ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ ዝርያ ነው ተብሏል።

የዝርያው ባሕሪ በአፍሪካ ከተለመደውና “Anopheles gambiae” ከሚባለው ዝርያ የተለየ በመሆኑ ርቢውን መቆጣጠርም ሆነ መግታት አለመቻሉን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። እንደሌሎቹ ዝርያዎች ለመራባት ውሃ ስለሚያስፈልገው እንቁላሉን በውሃ ውስጥ ለመጣል ደም ስለሚያስፈልገው ከሰው ሲመጥ በሽታውን ያስፋፋል። በዚህም መንገድ በተወሰነ ወቅት ብቻ ተራብቶ የሚሞት ሳይሆን፣ በደረቅ ወቅትም በሕይወት መቆየት ስለሚቻለው የርቢ ስርጭቱንም ሆነ ወረርሺኙን ማስቆም አልተቻለም።

የእስያው አዲሱ ዝርያ አፍሪካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በጅቡቲ ከ10 ዓመት በፊት ቢሆንም፣ ያን ያህል አስጊነቱ ሳይታይ እየተስፋፋ አሁን በበርካታ የአፍሪካ አገራት ተንሰራፍቷል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ የመን እና ናይጄሪያን በመሳሰሉ አገራትም በስፋት መሰራጨቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

 በድሬዳዋ ከተማ በየዓመቱ ይከሰት ከነበረው 200 ገደማ የተጠቂዎች ቁጥር ከፍ ብሎ፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በ10 እጥፍ ገደማ ጨምሮ ወደ 2 ሺሕ 400 መድረሱን የአርማወር ሃሰን ምርምር ማእከል ባለሙያ ከሰሞኑ አሳውቀው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን አዲሱ ዝርያ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለ ዝርዝር ምርምር ባለመደረጉ ጉዳቱ ለወደፊትም ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል።

ተቋሙ ከወራት በፊት በድሬዳዋ የተከሰተውን ወረርሺኝ ተከትሎ በአካባቢው ባካሄደው ጥናት በድሬዳዋ አካባቢ ካሉ የወባ ትንኝ ዝርያዎች 97 በመቶ የሚሆኑት ከእስያ የመጣው የአዲሱ ዝርያ ትንኞች ናቸው ማለቱ ታውቋል። አዲሶቹ ዝርያዎች እንደተለመዱት የተጠራቀመ የዱር ውሃን እንቁላሉን ለመጣያ ከመምረጥ ይልቅ፣ በመኖሪያዎች ውስጥና አካባቢ ያሉ ያልተከደኑ ውሃዎችን ለመጣያ ስለሚጠቀሙ ጎጂነታቸው በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር በአርማወር ሃሰን የምርምር ማእከል ባለሞያ ፍጹም ታደሰ፣ የጥናት ውጤቱን በሲያትል በተካሔደ የዓለም ዐቀፍ ስብሰባ ላይ ይፋ ባደረገበት ወቅት ጠቅሰዋል።

በካርቱም ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት አይማን አህመን በበኩላቸው ስለ አዲሱ ወረርሺኝ ሲናገሩ፣ እንደቀደሙት ዝርያዎች ኹለትና ሦስት ወር ብቻ የሚከሰት ሳይሆን ዓመት ሙሉ ስጋት ላይ የሚጥል ነው ብለውታል። ለወደፊቱም ከፍተኛ አደጋ የሚያመጣ ጥፋትን ያስከትላል ሲሉ ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ ስጋታቸውን አጋርተዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here