የሚያስቀና ሥልጣኔ፤ ከደቡብ አፍሪካ ሰማይ ስር

0
1492

አፓርታይድ በብዙ በፈተናትና ከዛ ተሻግራ ማለፍ በቻለችው፣ መጤ ጠልነት በሚያሳማት፣ የጽናት ተምሳሌት በሆኑት በኔልሰን ማንዴላ አገር ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ቆይታ ያደረገው ኤርምያስ ሙሉጌታ፣ ጉዞውን አስቃኝቶናል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ከታዘበው ጨልፎም የአገሪቱን ገጽታና የሕዝቧን መልክ አስመልክቶናል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በቁስም ሆነ በእውቀት የደረሰችበት ሥልጣኔ ለእኛም ባደረገልን! ያሰኘው መሆኑን በተከታዩ ጽሑፍ አጫውቶናል፡፡

ሰርክ የማይቦዝነው የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደተለመደው የኮራ የደራ የገበያ ማእከል መስሏል። ወደ ደቡባዊው የአኅጉሪቱ ክፍል፣ ጭፈራ እና ሳቅ የማይነጥፍባቸው፣ ከስጋ ወዳጅ ሕዝብ መገኛ፣ የነጻነት ፋይዳ ከሆነው የማዲባ አገር አጠር ያለች ቆይታ ለማድረግ ነበር ማልጄ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኘሁት።

ወደ አውሮፕላን ጣቢያው ሳቀና  አዲስ አበባ በቅጡ መንቃት ሳይሆን ሦስተኛው ወይም አራተኛው ምዕራፍ እንቅልፍ ላይ ብትሆን ነው። ባተሌው አውሮፕላን ጣቢያ ግን ወፈ ሰማይ መንገደኛን በእቅፉ ሸክፎ ሲያስተናግድ ነበር የደረስኩት።

የፍተሻውን እና ከዜግነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ከአገር ለመውጣት የሚያስችለኝን የይለፍ ፈቃድ በግሩም መስተንግዶ አጠናቅቄ ወደ መጨረሻው የአውሮፕላን መሳፈሪያ እና መጠበቂያ ስፍራ ተሸጋገርኩ። ማልጄ የተገኘሁት ሰው ከፊት ከነበረው ረጃጅም ሰልፍ የተነሳ የመጨረሻውን ፍተሻ ሳጠናቅቅ የማለዳዋ ጮራ ምድርን ማሞቅ ጀምራ ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራውን የማስፋፊያ ሥራ ጠቀሜታ በልቤ እያሞካሸሁ እና በማያቸው መጠነኛ መዛነፎች ድርጅቱን እየወቀስኩ የመሳፈሪያ ጊዜዬ እስኪደርስ ሁልጊዜም እንደማደርገው ከቀረጥ ነጻ ሱቆችን ዘወርወር እያልኩ እየታዘብኩ ነው።

ረጅም ሰዓት መሰለፌ ይሁን ወይም ደግሞ ረጅም ሰዓት ያለማቋረጥ መዞሬ፤ ብቻ ለወትሮው ከደብተር በጥቂት ትከብድ የነበረችው ላፕቶፔ የአሎሎ ያህል ከብዳኝ ትከሻዬን ልትበጥሰው ደርሳ ኖሮ መቀመጥ እንዳለብኝ ወስኜ ወደ አውሮፕላን መንደርደሪያው ፊቴን አዙሬ በመስታወቱ አንጻር ተቀምጩ ዙሪያ ገባውን መመልከት ቀጠልኩ።

ከራሱ አልፎ የበርካታ አገራትን ግዙፍ የሰማይ ጋሪዎች በኩራት አሳርፎ በደርዝ ሰድሮ ስመለከተው የአውሮፕላን ጣቢያው ትልቀት በጥቂት ገብቶኝ በብዙ አጃኢብ አስብሎኛል። የወጪ ወራጁን እና ወደ ዓለም ጫፍ ተንደርዳሪውን የሰው ልጅ ከዝብርቅርቅ የቆዳ ቀለሞቻችን ጋር ደርቤ እየታዘብኩ ሳይታወቀኝ ሰዓቱ ነጉዶ ኑሮ ከተቀመጥኩበት በመነሳት ወደ መሳፈሪያዬ ደጃፍ ተንቀሳቀስኩ። በእርግጥ ተንቀሳቀስኩ የሚለው አገላለጽ እንደዛ እስከዝንተ ዓለም የእግር ጉዞ ላደረኩት ለመሰለኝ ለእኔ የሚስማማ አልነበረም።

ብቻ ምን አለፋችሁ! በሰው ማዕበል ውስጥ እያለፍኩ ረጅም ተጉዣለሁ። የሰው ብዛት፣ ትርምሱ፣ የዕቃው ጋጋታ እና የሻይ ቤቶች ውክቢያ አቅል ቢያስት እና የት እንዳሉ ለአፍታ ቢምታታብዎት የሚገርም አይሆንም። በመተላለፊያ መንገዶች ላይ ጥግ ይዘው ልጆቻቸውን ታቅፈው ቀዝቃዛው ወለል ላይ የተቀመጡትን እናት መንገደኞች ዐይቼ የእናትነትን ገደብ የለሽለት ብታዘብም፣ ለአፍታ ግን የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ያለሁም መስሎኝ ነበር።

የሰዓታት ጥበቃው አልቆ ወደ ጢያራው ለመሳፈር ሌላ እስከ ገነት የተዘረጋ የሚመስል ሰልፍ ጋር ተጋፈጥኩ። ብዙም አልከፋኝም፤ በአቪዬሽን ሥልጣኔ ቅንጡ ነው የተባለለት ኤር ባስ ኤ 350 ካሰብንበት ሊያደርሰን አፍንጫውን ወደ ምሥራቅ ቀስሮ የጥቅምትን ውርጭ ከማለዳ ፀሐይ ጋር ደባልቆ እስከ ጨፌ ዶንሳ ድረስ፣ እስከ ኤረር ጋራ ድረስ የሚያሸት ይመስላል። በአፍሪካ ሰማይ ላይ በኩራት ቦራቂ፣ ባለ ሦስት ቀለማቱ ብሔራዊ ኩራት፤ የማያውቀው የአፍሪካ የአየር ክልል ይኖር ይሆን ማለት መድከም ይመስለኛል። ብርቅዬ የዱር አራዊት ሳይቀር ክንፉን እና ጭራውን ያስዋበበትን ግሩም ቀለማት ዐይተው ሳይሽኮረመሙ ይቀራሉ ብላችሁ ነው።

ጉዞው ተጀምሯል። እንዲያው ለይስሙላ ከስድስት ሰዓታት ይሸራርፉት እንጂ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ኦሊቨር ታምቦ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ከእኩለ ቀን ላቅ ያለ ጊዜ እንደሚወስድ ልብ ይባል።

የሰዓታት የአየር ላይ ጉዞ ተጠናቆ ምድርን ስንሳለም፣ ይሄ ቅንጡ ጢያራ በእውቅ የኢትዮጵያዊያን አብራሪነት ችሎታ ጋር አብሮ እንደ ሩህሩህ ሞግዚት እሹሩሩ ብሎ ነው ያሳረፈን። እንዲያው የከዚህ ቀደሙ የአውሮፕላኖች የማረፍ እና የመነሳት መንገራገጭ ልቤን ይሰልበኝ የነበረው እኔ ምስኪኑ፣ ኤር ባስ ኤ 350 የሠሩትን እጆች፣ ኮልኩለው ካስወነጨፉት የብሔራዊ ኩራት አብራሪዎች ጋር ደርቤ አመስግኛለሁ።

መሬት የነካው አውሮፕላናችን እኛን ለማውርድ በሩን ከአውሮፕላን ማረፊያው ደጅ ጋር ለማገናኘት ዘለግ ላለ ጊዜ የየብስ ጉዞ አድርጓል። ታዲያ በዚህ ወቅት በመንደርደሪያው መስክ ላይ ከተለያዩ ኃያላን አገራት አውሮፕላኖች መሳ ለመሳ አንድ ጥቁር፣ ኩሩ፣ የአቭዬሽን ኢንዱስትሪው ድምቀት የሆነውን በአገሬ ዓርማ ጭራውን ያስዋበውን አውሮፕላን ከርቀት ስመለከት ልክ ሊቀበለኝ የመጣን ወይም ደግሞ ከረጅም ዘመን በኋላ በባዕድ ምድር ወዳጄን ያገኘሁ ያህል ነበር ልቤ የሞቀው። አታስዋሹኝ! ቅንድቤን ለሰላምታ ከፍ ዝቅ አድርጌ እንደመፍገግ ብያለሁ። ወደ ቀልቤ ተመልሼ ሳስበው ደግሞ ብቻዬን የተንከተከትኩበትም ገጠመኝ ነበር።

መቼም ጀግኖቻቸውን ማወዳደስ እና ማጀገን ይችሉበት የለም? በጉምቱ ፖለቲከኛው እና በጸረ አፓርታይድ ትግሉ አንቱ የተባለው እና የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን ከፈረንጆች 1967 እስከ 1993 ድረስ ባገለገለው ኦሊቨር ሬጊናልድ ካዛና ታምቦ ሥም የተሠየመው አውሮፕላን ጣቢያ ደረስኩ። በዛም አስፈላጊውን የኢምግሬሽን ጣጣ ጨርሼ ወደ ሆቴል ወደሚያደርሰኝ ወደተዘጋጀልኝ መኪና አዘገምኩ።

ውዝግቡ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፤ ጥቂት አገራት ብቻ ተግባራዊ አድርገው ከሚጠቀሙበት አንዱ የሆነው የቀኝ መሪ የትራፊክ ሕግ አንደኛው በደቡብ አፍሪካ ይገኛል። ጎረቤት አገር ኬንያም ተጠቃሽ ናት። ታዲያላችሁ ጓዜን ለአሽከርካሪው ሰጥቼ ከመኪናው ማዘያ ላይ እንዲሰቅልልኝ ባደረኩበት ቅጽበት ወደ መኪናው ለመሳፈር እንደለመድኩብት በስተቀኝ በኩል ሄጄ ለመክፈት ስሞክር ከተሽከርካሪው መሪ ጋር ተገጣጠምኩ፤ መሸወዴን አምቄ በተቃራኒው በኩል ሄጄ ተሳፍሬ ጉዞ ወደ ሆቴል ሆነ።

የአውሮፓ አገራትን ለጎበኘ የደቡብ አፍሪካዊቷ ጁሀንስበርግ ምንም ልዩነት አያገኝባትም። እንዲያው አፍሪካ አሉን እንጂ በደምሳሳው ጉዳዩስ ለየቅል ነው። የመንገዱ ጥራትና ምቾት፣ የትራፊክ ፍሰቱ መሳለጥ እና ፍጥነት፣ የዙሪያ ገባው ልምላሜ እና ውበት ግድ የላችሁም አፍሪካ የምትባለውን አኅጉርማ ተሰናብቻታለሁ እንጂ እንዲህማ ሁሉም ነገር መስመር የለበትም ልትሉም ይከጅላችኋል። ያው የአፍሪካ ስዕላችን የተበላሸ አይደል!?

ከጀት መለስ ባለ ፍጥነት የሚከንፈው አሽከርካሪ የአገሩ ባህል መሆኑን እና ዝግ ማለት ለመንገድ መዘጋጋት ምክንያት መሆኑን አርድቶኛል፤ የፍጥነቱ ነገር አሳስቦኝ በጠየኩት ጊዜ። በዛ አሳቃቂ ፍጥነት ለ25 ደቂቃ አካባቢ ስንሰግር ቆይተን ማርፊያዬ ደርሻለሁ።

ሥልጣኔው ያስቀናል…

ከተወገደ 30 ዓመታትን ያስቆጠረው አፓርታይድ እንዳልተፈጠረ ተረስቶ ጥቁር እና ነጭ የቆዳ ቀለም ሰዎች ትከሻ ለትከሻ እየተለካኩ ሲኖሩ ሲታዩ የእድገታቸው ምስጢር፣ የሥልጣኔያቸው ዳራ ወለል ብሎ ይታያችኋል። የ30 ዓመቱ ታሪክ እንዲህ ተዳፍኖ ባልኖርንበት፣ ባልሰማነው እና ባላየነው የአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል ታሪክ ዜጎቿ ዛሬም ከሚባሉባት አገር ለሄደ የእኔ ቢጤው ግርታን ብቻ ሳይሆን ቁጭት ቢነድበት አይገርምም።

ይህ ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ በመጤ ጠልነት ሥማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳው ደቡብ አፍሪካዊያን እልፍ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ነግደው የሚያተርፉባት፣ ወልደው የሚስሙባት የክፉ ቀን መሸሸጊያ ሆና ያስጠጋቻቸው የባለውለታቸው ልጆች ናቸው። “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ ደቡብ አፍሪካዊያን ሠራተኞች አይደሉም። ይህም ደግሞ በስደት ለሚኖረው ሕዝብ የእንጀራቸው ምንጭ ነው። ኢትዮጵያዊያን፣ የማላዊ እና የዝምባብዌ ዜጎች ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው፤ ጆሀንስበርግ ውስጥ።

ጆሀንስበርግን ዙሪያ ገባውን በሚያስጎበኘኝ የአክስቴ ልጅ አማካኝነት ብዙ ታዘብኩ፣ ብዙ ተከዝኩ፣ ብዙ ቀናሁ፣ ብዙ ጊዜም የብሽቀት ይሁን የቅናት ብቻ ፈንቅሎ ሊወጣ የነበረውን እንባዬን መልሼዋለሁ። ምክንያቱን አትጠይቁኝ አላውቀውም!

“ነገ ውጣ፣ ከእኛ ወገን አይደለህም” እባላለሁ ሳይል ገላውን ሰድዶ የሚተኛው እና የሚሠራው የሐበሻ ቁጥር እልፍ ነው። የእጃቸውን ሥራ ፈጣሪ ባርኮላቸውም በጆሀንስበርግ ‹GP› ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ‹ይህ የሐበሻ ፎቅ ነው…ሕንጻ ነው› ሲባል እንዴት ልብ ያሞቃል መሰላችሁ። ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ደቡብ አፍሪካ የከተሙት ኢትዮጵያዊያን ጋር በነበረኝ ጥቂት ቆይታ፣ “ከኢትዮጵያ ይልቅ እዚህ ደኅንነት ይሰማኛል” የምትል ለእነሱ ቀላል ለእኔ ግን ትልቅ ሕመም የሆነች ንግግር የተለመደች ናት። በእርግጥ አልተከራከርኩም፤ ልክ ናችሁ ብዬም አልደገፍኩም። ዝም ብዬ በቅጽበታዊ ፈገግታ እያጀብኩ ሕመምን መታመም።

ወይ ሥልጣኔ! ወይ ልቆ መሄድ! ወይ መደማመጥ! ወይ የእውነት ይቅርታ! እንዴት ያስቀናል መሰላችሁ። ከተሞቻቸው ውብ ናቸው። በቅኝ ግዛት ቢገነቡም የተሠራን ጠብቆ ማስቀጠልስ፣ ካለው ላይ እንዲገነባ መፍቀድስ፣ ታሪክን ክፍ አድርጎ ማጉላትስ? ኧረ ስንቱ ይጠቀሳል። ብቻ በሥልጣኔያቸው ቀንቼባቸዋለሁ።

ትምህርት

ደቡብ አፍሪካ የጉምቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መገኛም ናት። እንደነገርኳችሁ ሥልጣኔያቸው ያስቀናል። የጉዞዬ ዓላማ የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ኮንፈረንስን ለመካፈል እና የኢትዮጵያን ልምድም ለማካፈል ነው። ታዲያ የዝግጅቱ ዋና አጋፋሪ እነሱ ሲጠሩት “ቬትስ” ይሉታል፤ ሲጻፍ ግን ‹Wits› ወይም University of the Witwatersrand, Johannesburg ነው።

ታዲያላችሁ የግቢው ስፋት፣ የትምህርት ክፍሎች መዋቅር እና የመምህራን ብቃት በቆይታዬ በዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጻ በተደረገልኝ ወቅት የታዘብኩት ነው። የግቢውን ስፋት ለመናገር ቃላት ያንሳል። ይሁን እንጂ በግቢው ውስጥ የትራፊክ መብራት ሳይ የስፋቱን ጉዳይ ደመደምኩ። ድፍን አንድ ምዕት ዓመትን ባስቆጠረበት ሰሞን ነበርና የሄድኩት የክብረ በዓሉ ሽር ጉድ አልበረደም ነበር። ማስታረቅ ያቃተኝ ግን 100 ዓመታትን እንደወይን እየጎመራ የቆየበት እና የቀድሞ ሕንጻዎች የኪነ ሕንጻ አለመደብዘዝን ነው። እውነቴን ነው እኔ እኮ በቅጡ 50 ዓመታትን ያልተሻገሩ ሕንጻዎች በአጭር ከሚቀጩባት አዲስ አበባ ነው የሄድኩት።

ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ሥልጣኔያቸው ያስቀናል። የሥልጣኔ መሠረቱም፣ ማስቀጠያውም፣ ማቀጣጠያውም ትምህርት ነው። ለዚህም ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚዋ ናት።

ቆይታየን እያጠናቀኩ ነው። ማዲባ የማይገባበት ስፍራ የለም። መንገድ ተሰይሞለታል፣ በስኳር ማሸጊያ ጀርባ ላይ ሳይቀር በሕይወት ዘመኑ የተናገራቸው መሬት ጠብ የማይሉ ንግግሮቹ ተቀንጭበው ተከትበውለታል። ተጠቃሚው እንዳሻው ይኮመኩማል፣ ማዲባን ይዘክራል። ጎላ ባለ ድምጽ የሚነጋገሩት፣ ጨዋታ አዋቂዎች፣ ዳንኪረኞች፣ papa ወይም ደግሞ Sir የሚሉ ቅጥያዎችን ከአዲስ ሰው ትውውቅ በፊት የሚያስቀድሙትን ደግ ሕዝቦችን ልሰናበታቸው ነው።

ዐይናችሁ ክፉ አይይ፣ እንደሳቃችሁ ኑሩ፣ ተድላችሁ ይክረም፣ የሰማይ አምላክ ክፉን ያርቅላችሁ፣ ካፊያችሁ ምድርን ያረስርስ፣ የዘራችሁት ይብቀል። ደግመን እስክንገናኝ ልቤን ወስዳችሁታልና አደራ እላችኋለሁ። አብባችሁ ቆዩኝ!

የመልስ ጉዞ ወደ እናት ምድር፤ ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ ቤቴ!


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here