ፎርቹን ጋዜጣ በ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል አገልግሎቱን ሊያሰፋ ነው

0
510

• ሰባ በመቶ የአክስዮን ድርሻ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል

በኢትዮጵያ በኅትመት መገናኛ ብዙኀን ዘርፍ ኹለት ዐሥርት ዓመታትን ከተሻገሩ በጣት ከሚቆጠሩ ሚዲያዎች መካከል አንዱ የሆነው ፎርቹን ጋዜጣ ለ10 ዓመት የሚቆይ የተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማዘጋጀትና ማውረትረቻውን (capital) ወደ 40 ሚሊዮን ብር ሊያሳድግ እንደሆነ አስታወቀ። በዚህም የኩባያውን አቅም በማሳደግ በተለያዩ ቋንቋዎች እና የመገናኛ ዘዴዎች ወደ ሕዝብ ሊደርስ እንደሆነ አስታውቋል።

የጋዜጣው አሳታሚ የኢንዲፔንደንት ኒውስ ኤንድ ሚዲያ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ ሥራ አስኪያጅ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ተቋሙን የማሻሻል ጥናት ለኹለት ዓመታት ሲካሔድ መቆየቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ያለፉት ኻያ አምስት ዓመታት ስንከተላቸው የቆዩ የኅትመት የመገናኛ ብዙኀን ሥራ ተምሳሌቶች ከቴክኖሎጂ መሻሻል ጋር አብሮ መዝለቅ የማያስችል በመሆኑ ይዘት፣ ተደራሽነትና ብዝኀነትን ለማካተት የሚያስችል የኅትመት ሚዲያ ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቀርፀናል›› ሲሉ ታምራት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኅትመት መገናኛ ብዙኀን አቀራረብ ለአንባብያን ዐይንና ቀልብ የሚስቡ ሥራዎችን በመሥራት፣ የአንባብያንን ፍላጎት በመጨመር እንዲገዙዋቸውና እንዲመለከቷቸው የሚደረግበት አካሐየድ ዘላቂ አለመሆኑንም ይገልጻሉ።

ኅትመት‹‹ከኅትመት በኋላ እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብ ከመሆን ባለፈ የማስታወቂያ ድርጅቶች ለማስተወቂያ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠየቁበት አሰራር ሆኖ ስንብቷል›› እንደ ታምራት ገለፃ።

በዘመነ ቴክኖሎጂ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን የንግድ ቅርጻቸው እየተዛባ ከመምጣቱ ባሻገር የብሮድካስት ሚዲያውም ቢሆን በዲጂታል ሚዲያው ጫና ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ።

በመሆኑም የተግባቦት ሒደቶችንም ከአንድ አቅጣጫ ወደ አንባቢ የሚላኩበት ብቻ ሳይሆን መረጃዎችን አሳታፊ በሆነ መልኩ ከብዙ አቅጣጫ ወደ ብዙ አቅጣጫ እንዲሐየድ ማድረጉ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ የሆኑ መገናኛ ብዙኀንን ብቻ ሳይሆን በተያያዥነት የመጡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህሪ የተከተሉ የመረጃ ምንጮች እንዲበዙ አድርጎታል ሲሉም ያስረዳሉ።

‹‹በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የማንበብ ልምድ ዝቅተኛ በሆነባቸው አገራት ለኅትመት ፕሬሱ ዕድገት እንቅፋት ቢሆንም እያደገ የመጣውን የቴክኖሎጂ ለውጥ በተንቀሳቃሽ ስልክ ፈጣን መረጃዎች አማካኝነት በሚለቀቁ ሐሳቦች ተደራሽ ማድረግ አስችሏል›› በማለት የዲጂታል ሚዲያውን አቅም ከአገራዊ ሁኔታው ጋር ያስተሳሥራ ሉ።

የዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት መረጃዎች ይዘታቸውን ጠብቀው በአጭር ምስልና ድምጽ፤ በምስል እንዲሁም በድምጽ ብቻ በማድረግ አንባብዎቻቸውን በቀላል መልኩ በሚይዙት ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካኝነት በኅትመት ሥራዎቻቸው የሚያካትቷቸውን ይዘቶች ሳይለቁ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችን ያከናውናሉ።
ፎርቹን ጋዜጣም ይህንን በመከተል የኅትመት ስርጭትን ብቻ የሚያከናውን ብቻ ሳይሆን የይዘት ባለቤትም መሆኑን ከግምት ውስጥ በመክተት ያለውን ይዘት የተለያየ የቪዲዮ ሥራዎችን፣ አጫጭር የሬዲዮ ድምጾችን (ፖድካስት) እንዲሁም የጋዜጣ ስርጭቱን ሳያቋርጥ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአሳታሚነት ሚና ወደ ይዘት ባለቤትነት በመቀየር በቋንቋ፤ በይዘትና ተደራሽነት መሔድ የሚያችሉ አካሔዶችን በመፍጠር መሥራት የሚያስችለውን አካሄድ እንደሚከተልም ገልጸዋል።

‹‹ይህ ሒደት የችሎታና የዐቅም ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ ኹለት ዓመታት ውስጥ ሰማንያ የሚሆኑ ሰዎችን እናሠለጥናለን›› ያሉት ታምራት ‹‹ሙያተኞቹ ሪፖርተሮች፣ ምስል ፈጣሪዎች፣ የመተግበሪያ ባለሙያዎች፣ የገበያ ጥናት ባለሙያዎች እንዲሁም የአስተዳደር ባለሙያዎች ናቸው›› ብለዋል።

በእንግሊዘኛ ብቻ ተደራሽ የነበረውን ኅትመት በአዲሱ ስትራቴጂ መሰረት ኦሮሚኛ፤ ትግርኛ፤ አማርኛ ቋንቋዎችን አካታች ለማድረግ ፍላጎት እንዳለም ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የሚዲያ ተቋሙ ለመጀመር የሚያስፈልገው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርሰውን ሀብት እስካሁን ባለው ካፒታል ተቋሙ ማድረግ ስለማይችል፣ 70 በመቶ የሚሆነውን ሃብት የማፈላለግ ሥራውን ከህብረተሰቡ ለማግኘት እንደሚሠራ ተገልጿል።

የ10 ዓመት ስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት የድርጅቱን ሃብት ያለውን አቅም በማስጠናት ያጠናቀቀ ሲሆን ድርሻ የመያዝ ፍላጎት ላላቸው ሰዎችም ክፍት መሆኑን ታምራት አስታውቀዋል። በኅትመት ፕሬስ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት የሚጋብዝ አካሔድ እየተከተሉ እንደሚገኙ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ለዚህም ፍላጎቱ ያላቸው አካላት ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በቢዝነስ ዘገባዎች ላይ የሚያተኩረው ፎርቹን በንግድ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራ የእሁድ ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነገ የሚወጣውን ዕትም ጨምሮ ያለማቋረጥ ለ1018 ጊዜ ታትሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here