በ1.3 ሚሊዮን ብር በእድሳት ላይ የቆየው የወመዘክር አዳራሽ መጠናቀቅ አልቻለም

0
899

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ወመዘክር በዋናው አዳራሽ ላይ በ1.3 ሚሊዮን ብር የሚያደርገው እድሳት በመስከረም 2012 ይጠናቀቃል ቢባልም ባጋጠመው የዲዛይን ችግር የወንበር አደራደሩ ወደ ጣራ በመቅረቡ ምክንያት ፈርሶ እንዲሠራ ተወሰነ።

እድሳቱ ከአሜሪካን ኤምባሲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሰኔ 2011 የተጀመረ ሲሆን የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያስተናግደው የአዳራሹ የወንበር አደራደር ምቹ ባለመሆኑ በደረጃ ለማድረግ ታስቦ ነበር የተጀመረው። ነገር ግን ሥራውን የያዘው ኮንትራክትር ያለ ግንባታ ዲዛይን አማካሪ የሚሠራ መሆኑን ተከትሎ የወንበሮቹ አቀማመጥ ለጣሪያው በጣም በመቅረቡና ይህም በአዳራሹ ውስጥ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ ሙቀት እንዲፈጠር ምክንያት በመሆኑ ከኤጀንሲው አስተዳደር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መድጋሚ ፈርሶ እንዲሠራ መደረጉን የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ ይኩኖአምላክ መዝገቡ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እድሳቱ የኤሌክትሪክ ሥራዎችን፣ የመብራት ማዘመን እና የወለል ምንጣፍ ቅያሬን የሚጨምር ሲሆን፣ ለእድሳቱ ድጋፍ ያደረገው ኤምባሲው በወመዘክር አዳራሾች ተደጋጋሚ መርሃ ግብሮችን እንደሚያከናውንም ይታወቃል።

ለእድሳቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቅቅ በአዳራሹ እድሳት መዘግየትም መደረግ የነበረባቸው ኪነ ጥበባዊና የመጻሕፍት ላይ ውይይቶች በኤጀንሲው በሚገኙ በሌሎች ትንንሽ አዳራሾች ውስጥ እየተደረጉ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ባለፉት ኹለት ወራት ምርቃታቸውን ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ ኹለት መጽሐፍትን በአዳራሹ ለማስመረቅ እንዳልተቻለ ተገልጿል።

አዳራሹ 120 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በዋናነት የድምጽ እና የመብራት ችግር ነበረበት የሚሉት ይኩኖአምላክ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲሁም በአዳራሹ ውስጥ ጥናታዊ ጽሑፎችን በምስል ማቅረብ፣ ፊልሞችን ማሳየት እንዲችል እና መጸዳጃ ቤትን ጨምሮ መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማሻሻል በማሰብ እድሳቱ በመካሔድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከኮንትራክተሮች ጋር ውይይቶችን በማድረግ የአዳራሹን እድሳት ሥራ በጥቅምት ወር ለማጠናቅቅ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፣ በእድሳቱ ላይ ለተፈጠረው ስሕትት ሙሉ ለሙሉ ወጪውን ኮንትራክተሩ እንዲሸፍን ተደርጓል።

የአዳራሹ የመያዝ አቀም ትንሽ መሆኑን ተከትሎ በወንበር 120 ሰዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ትልልቅ መረሃ ግብሮች በሚኖሩበት ጊዜ ፕላስቲክ ወንበሮችን በመጨመር እስከ 150 ሰው እንዲይዝ ይደረጋል ሲሉ ኀላፊው ገልፀዋል። በቀጣይ ኤጀንሲው በጊቢው ውስጥ በሚያስገነባው ህንፃ ላይ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት መስጠት የሚችል አዳራሽ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ “የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር” በሚል ስያሜ በ1936 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን አገልግሎት መስጠት የጀመረውም ንጉሡ ባበረከቱት ከ 200 በላይ የመጻሕፍት ስጦታ ነው። በ1958 በተደረገው የቤተ መጻሕፍት መዋቅር ለውጥ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት የሚል ስያሜን ይዞ በጥንታዊ ቅርሶች አስተዳደር ሥር እንዲሠራ ተደርጓል።

በ1968 ለባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ከሚታተሙ ማናቸውም ህትመቶች ሦስት ሦስት ቅጂዎችን እንዲረከብ በመንግሥት የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ቤተ-መጻሕፍቱ እንዲያስፈጽም ውክልና አግኝቷል።

በ1998 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ ቁጥር 471/98 የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ስያሜ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛብትና ቤተመጻሕፍት ድርጅት – ኤጀንሲ በሚል መጠሪያ እንዲለወጥ ተደርጎ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት የ24 ሰዓት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ደራስያንና ጸሐፍያን ለመጽሐፍ ሥራቸው እውቅናን የሚያገኙበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በድረ ገጽ ገበያ መጽሐፍቶቻውን ለመሸጥ የሚያስችላቸው የመጻሕፍትና የመጽሔት መለያ ቁጥር ይሰጣል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here