ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል በሕገወጥ ውህደት ተቀጣ

0
858
  • የታዋቂው ቢሊዮነር ዲንቁ ደያሳ እናት ያለፈቃድ ድርሻ ገዝተዋል ሲል ችሎቱ በይኗል

የሸማቶች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል የቀድሞ ባለቤቶች የአክሲዮን ድርሻቸውን ለሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ድንቁ ደያሳ እና ወላጅ እናታቸው ዳንሳ ጉርሙ ለባለሥልጣኑ ሳያሳውቁ መሸጣቸው ሕገወጥ ውሕደት ነው በሚል ጥፋተኛ አደረጋቸው።

የባለሥልጣኑ አቃቤአን ሕጎች የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደሩ ችሎት፣ ተከሳሾቹን በነፃ ማሰናበቱ አግባብ አይደለም በሚል ያቀረበውን አቤቱታ የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ፤ ማንኛውም ነጋዴ ከ 30 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት በሚፈፅምበት ወቅት ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ይገባዋል፣ የስር ፍርድ ቤቱ ሺያጩ በድርጅቶች መካከል የተደረገ ሲሆን ብቻ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ያስፈልጋል በሚል የሰጠው ውሳኔም አግባብ አይደለም ሲል ሽሮታል።

የሆስፒታሉ የቀድሞ ባለቤቶች መካከል የሆኑት አባት አና ልጅ ኢብራሂም ናኦድ እና አሕመድ ኢብራሂም በኅዳር 28/2011 ድርሻቸውን ለመሸጥ በጠቅላላ ጉባኤው ወስነዋል።

የታዋቂው ቢሊዮነር ዲንቁ ደያሳ ወላጅ እናት ዳንሳ በሆስፒታሉ ላይ ካላቸው 95 ሚሊዮን ብር በላይ የአክሲዮን ድርሻ በገዙበት ወቅት ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ነበረባቸው ሲል ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ወስኗል።

የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚደነግገው፣ ማንኛውም ዓመታዊ ሽያጩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የንግድ ድርጅት ውህደት ከመፈፀሙ በፊት በሸማቾች መብት እንዲሁም በፍትኀዊ ገበያ ውድድር ላይ ያለውን ጫና ባለሥልጣኑ እንዲያውቅና እና ፈቃድ እንዲያገኝ መጠየቅ ይገባዋል።

ተከሳሾች በበኩላቸው ‹‹ያደረግነው ግብይት ውህደት ሊባል አይችልም፤ ለዚህም ምክንያቱም ግብይቱ የተፈፀመው በግለሰቦች መካከል እንጂ በድርጅቶች መሀል አይደለም›› ሲሉ ተከራክረዋል። የተደረገው የአክስዮን ግብይት በኹለት ነጋዴዎች መካከል ስላልሆነ ለባለሥልጣኑ የማሳወቅ ግዴታም የለብንም ሲሉ ሞግተው። ባለሥልጣኑ በጠየቀው መሰረት ከዓመታዊ የግብይታቸውን 10 በመቶ ቅጣት መክፈል አይገባንም ሲሉ ተከራክረዋል።

አቃቤአን ሕጉም በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ለሕጉ የሰጠው ትርጉም ተገቢ አይደለም፣ በንግድ ድርጀት ስር የተካሔደ ሽያጭ እንደ ውሕደት ይቆጠራል ብለው ተከራክረዋል።

ክሱን የተመለከተው የባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግበኝ ሰሚ ችሎት ክርክሩን ካዳመጠ በኋላ የአቃቤ ሕግን ይግባኝ በመቀበል የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ከሆስፒታሉ የ2011 ዓመታዊ ገቢ ላይ አምስት በመቶ የገንዘብ መቀጮ እና የውህደት ድርጊቱም እንዲቆም ወስኗል። በተጨማሪም በግለሰቦቹ መካከል የተደረገው አክሲዮን ግብይት እንደ ውህደት የሚቆጠር ነው ሲል በይኗል።

በ2006 ስለ ንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ በወጣው አዋጅ መሰረት ማንኛውም ነጋዴ በውህደት ስምምነት ወይም ቅንብር ለመሳተፍ ሲያቅድ የታቀደውን ውህደት በዝርዝር በመግለጽ ለባለሥልጣኑ የውህደት ማስታወቂያ ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል። ባለሥልጣኑም የውህደት ማስታወቂያ ሲቀርብለት የታቀደው ውህደት በንግድ ውድድር ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ስለመኖሩ እንደሚያጣራ ይገልፃል።

እንደ አስፈላጊነቱም የውህደቱ ተሳታፊ ወገኖች ተጨማሪ መረጃ ወይም ሰነድ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያቀርቡ መጠየቅ እና ውህደቱ ተፅዕኖ ሊያስክትልበት የሚችል ማንኛውም ነጋዴ ተቃውሞ ካለው ይህንኑ ተቃውሞ ማስታወቂያው በታተመ በ15 ቀናት ውስጥ በጽሑፍ አንዲያቀርብ ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ ላይ በሚታተም ማስታወቂያ ሊጋብዝ እንደሚችል ይደነግጋል። ባለሥልጣኑ ውህደቱ በንግድ ውድድር ላይ የጎላ አሉታዊ ተፅዕኖ አንደማይኖረው ካመነበት ውህደቱን እንደሚፈቅድ ያትታል።

ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል በ2006 በ32 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ በህክምና አገልግሎት እና ትምህርት ዘርፍ አገልገሎት እየሰጠ ሲሆን አጠቃላይ ሀብቱም 132 ሚሊዮን ብር ደርሷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here