በዋግ ኽምራዞን 250 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይሻሉ ተባለ

0
712

ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሰሜን ኢትዮጵያ ካጋጠመው ጦርነት የተነሣ ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በጦርነት ሥር የቆዩት የዋግ ኽምራ ዞን ነዋሪዎች ከፍተኛ ረሀብ አጋጥሟቸዋል ተባለ፡፡

በዚህ ረሀብ ምክንትያት ቢያንስ 250 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ዝናሽ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ከፌደራል መንግሥት እስካሁን 8 ሺሕ 800 ኩንታል እህል ወደ አካባቢው የተላከ ቢሆንም፤ ይህ ግን የሚበቃው ለ58 ሺሕ ሰው ብቻ ነው፡፡ይህንን ጥያቄ በተመለከተ አዲስ ማለዳ የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስተና ኮሚሽንን ያነጋገረች ሲሆን፤ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ደበበ ዘውዴ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፤ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የተላከው ድጋፍ በቂ አይደለም ማለታቸውን በሚመለከት “እሱ የራሳቸው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ደበበ አክለውም “እኛ መላክ ያለብንን ነው መላክ ያለብን እንጂ ማንም በፈለገው ልክ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የዋግሕምራ ዞን አማራ ክልል ከትግራይ ጋር የሚዋሰንበት አካባቢ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዞኑ አስቀድመው የጦርነቱ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ወትሮ ለሌላም የሚተርፉት የኮረም፣ ወፍላ እና ዛታ ወረዳ አርሶ አደሮች ላለፉት አንድ ዓመት ከስምንት ወራት የእርሻ ሥራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው ለረሀብ ተገልጠዋል፡፡ በመሆኑም ለዞኑ ሕዝብ ፈጣን ምላሽ ካልተገኘ የብዙዎች ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከዞኑ ሰምታለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here