የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ወጪ ንግድ በ150 ሚሊዮን ብር አሽቆለቆለ

0
605

• በሩብ ዓመቱ የ10 ሚሊዮን ዶላር ምርት ብቻ ወደ ውጪ ተልኳል

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2012 ሩብ በጀት ዓመቱ ውስጥ መሰረታዊ የግንባታ ብረታ ብረት ምርቶችን ፣ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ 10 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን አስታወቀ።

በነዚህ ሶስት ወራት በወጪ ንግዱ የተሳተፉ የዘርፉ ኩባንያዎች ከ10 በላይ ሲሆኑ ለምርቶች የገበያ መዳረሻ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ 20 ሀገራት እንደነበሩ ተገልጿል።

ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ150 ሚሊዮን ብር ወይም የአምስት ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ለዚህም ጥሬ እቃዎችን ለማስገባት የውጪ ምንዛሬ እጥረት ፣የኀይል መቆራረጥና ማነስ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ምንም እንኳን ዘርፉ በከፍተኛ መጠን ከውጭ የሚገባውን ያለቀለት ብረታ ብረት እና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ምርቶቹን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በ2012 ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን የኢንስቲትዩቱ ሕዝብ ግኑኙነት ኀላፊ ፊጤ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ገቢው ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ለመሆኑ በኢንስቲትዩቱ ግብአት ለማስገባት ያጋጠመው የውጪ ምንዛሬ እጥረት በመንስኤነት የተነሳ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከብሔራዊ ባንክ የዓመቱን የብረታ ብረት ጥሬ እቃዎች ዋጋ መሰረት በማድረግ እና እያንዳንዱ ፋብሪካ በዓመት ውስጥ የሚያስፈልገውን ጥሬ ዕቃ መጠን በማያያዝ ጥያቄ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

የውጪ ምንዛሬ እጥረቱም ፋብሪካዎች ከማምረት አቅማቸው በታች እንዲሠሩ ማድረጉ ከዘርፉ መገኘት የሚገባወን ጥቅም ከማሳጣቱም በላይ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል እንዳይፈጠር መንስዔ መሆኑ ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም የኀይል መቆራረጥ እና ማነስ ቀላል የማይባል አስተፅእኖ እንዳለው ተገልጿል።
ከውጪ የሚገቡትን ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ ለማምረት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እና ቴክኖሎጂ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከውጪ ሀገራት በማምጣት በሀገር ውስጥ እሴት በመጨመር ለውጪ ገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ለወደፊት ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሃብት በማውጣት ለመጠቀም እንቀስቃሴዎች መኖራቸውንም ነው ፊጤ በቀለ የተናገሩት።

‹‹የሀገር ውስጥ ገበያን በተመለከተ ከውጪ የሚገቡ ያለቀላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የውጪ ምንዛሬን ማዳን አላማችን አድርገን ብንሠራም ግዢ ፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ከብረት ውጪ ያሉ እንደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ተሸከርካሪ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና ሌሎች ኢንዱስትሪ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ ለመግዛት ፈቃደኛ አይደሉም።›› ሲሉ ፊጤ ይናገራሉ። ‹‹በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ገበያ እንዲያጡ ከማድረጉም በላይ ያለ አግባብ የውጪ ምንዛሬ እያባከኑ ነው›› ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ መንግሥታዊ እና የግል ኢንዱስትሪዎች በየትኛው ዘርፍ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ በማማከር ሥልጠናዎችን የመስጠት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የኒቨርስቲዎችን ከ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማገናኘት አጋር እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በኢንስቲትዩቱ ከ 115 በላይ ኢንዱስትሪዎች ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን በ2011 የበጀት ዓመትም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባት ችሏል።
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2002 ሲቋቋም፣ ዓላማው የአገሪቱን የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ቴክኖሎጂዎች ልማትና ሽግግርን በማፋጠን ኢንዱስትሪዎቹ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ፈጣን ልማት እንዲያስመዘግቡ ለማብቃት የሚል ሲሆን ከ2006 ጀምሮ የብረታ ብረት ምርቶችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here