ከ300 መቶ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች ለአራት ወራት ሥራ ሳይዙ ተቀምጠዋል

0
798

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማቋቋም በጀመረው ሥራ ወደ ማሠልጠኛ እና ማገገሚያ ከገቡ የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል 300 የሚሆኑት ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ በዝቅተኛ ገንዘብ ሥራ አንይዝም፣ የተገባልን ቃልም አልተፈፀመም በሚል ያለ ሥራ በመቀመጣቸው ቅሬታቸውን አሰሙ።

ሠልጣኞቹ በብረታ ብረት ሥራ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቀለም ቅብ፣ በእንጨት ሥራ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ ለምንሠራው ሥራ እየቀረበልን ያለው ደሞዝ አነስተኛ ነው በማለት ሥራ ሳይቀጠሩ መንግሥት ሙሉ ምግብ፣ የአልባሳት እና መሰል ወጪዎችን እየሸፈነላቸው ላለፉት ዘጠኝ ወራት በአራት መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

አዲስ ማለዳ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኛው ማዕከል በመገኘት ያነጋገረቻቸው ተነሺዎች መካከል፣ ብስራት ፈቃዱ እንደምትለው፣ የጨርቃ ጨርቅ እና ልብስ ስፌት ሥልጠና ወስዳ አጠናቃለች። እንደርሷ አገላለጽ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ያገኙት ሥልጠና በቂ ባለመሆኑ ቀጣሪዎች ችሎታ የላችሁም በሚል በአነስተኛ ደሞዝ እንደሚቀጥሯቸው ትናገራለች።

‹‹ከ 15 ቀናት በፊትም ሥልጠናውን የወሰድን 19 ሰልጣኞች ኀይሌ ጋርመንት በልብስ ስፌት ሥራ ብንጀምርም የሚከፈለን ደሞዝ ከ 1500 ብር በታች በመሆኑ፣ ከካምፕ ወጥተን የራሳችንን ሕይወት መመሥረት አልቻልንም፤ በመሆኑም በመጠለያ ውስጥ ያለ ሥራ ለመቀመጥ ተገደናል›› ስትል ገልጻለች።

ብስራት ከቤተሰቦቿ ጋር በተፈጠረ አለመስማማት በ 14 አራት ዓመቷ ወደ ጎዳና ልትወጣ ተገዳለች። በጎዳና ላይ 5 ዓመታትን እንዳሳለፈችም ገልፃለች። ይህንን እድል በማግኘቷ ደስተኛ ብትሆንም፣ የክፍያው ሁኔታ ግን አዲስ ሕይወት የመጀመር ሕልሟን እንዳጨናገፈባት ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።

ሌላዋ ሠልጣኝ አበባ ጌታቸው በበኩሏ ‹‹ሥልጠናው ብቁ የሚያደርገን አልነበረም፣ ከ አንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ በመሆኑ በቂ እውቀት ሳናገኝ በመቅረታችን ቀጣሪዎች እናንተ አትችሉም በሚል በወር 6 መቶ እና 700 ብር ክፍያ ነው የሚያቀርብልን›› ሰትል ታስረዳለች። ‹‹ይህም ከመጠለያው ወጥተን የራሳችንን ሕይወት እንዳንመሰረት አድረጎናል›› ሰትልም የብስራትን ሃሳብ ትጋራለች። ‹‹ወደ ሥልጠናው ስንገባ ከ4 ሺሕ እስከ 5 ሸሕ ብር ደሞዝ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሥራ አፈላልጎ ማስቀጠር ሳይችል ቀርቷል›› ስትል የሆነውን ለአዲስ ማለዳ ታስረዳለች።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ሥራ ስንሰማራ ልጆቻችንን የምናስቀምጥበት ስፍራ ባለመኖሩ ተንቀሳቅሰን መሥራት አልቻልንም የሚሉ እና ወደ ቤተሰቦቻቸን እንመለስ ብንል እንኳን የሚሰጠን ማቋቋሚያ ገንዘብ ከ4 ሺሕ ብር የሚበልጥ አይደለም የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በቃሊቲ መጠለያ ውስጥ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አስተባበሪዎች በበኩላቸው ሠልጣኞቹ በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ ካልተቻለ ሌሎች በጎዳና ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመቀበል እክል እና ሠልጣኞችም በመሰላቸት ወደ ሱስ እና ወደ ጎዳና ሕይወት መልሰው እንዲገቡ ምክንያት ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ማህበራዊ ዘርፍ ቢሮ ኀላፊ ተወካይ የሆኑት ቢኒያም ግርማ፣ ሠልጣኞቹ የሚከፈለን ደሞዝ አነስተኛ እና ለኑሮ የማይበቃን ነው በሚል ምክንያት ሥራውን እንደሚለቁ ይገልፃሉ። ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር ክፍያው በቂ ነው ተብሎ አይታመንም ያሉ ሲሆን ክፍያው የሀገሪቷን ኢኮኖሚ የመክፈል አቅም መሰረት ባደረገ እና የሠልጣኞችን ችሎታ ባገናዘበ መልኩ የሚፈፀም መሆኑን ገልጿዋል።

ወደ ሥልጠናው ከመግባታቸው በፊት ከተለያየ መንግሥታዊ እና የግል ድርጅቶች ጋር በመወያየት ሠልጣኞቹ ሥልጠናውን እንዲያገኙ ብናደርግም በወቅቱ ሠልጣኞቹን ለመቀበል እና የሥራ እድል ለማመቻቸት ቃል የገቡ ተቋማት በገቡት ቃል መሰረት ሠልጣኞችን ባለመቀበላቸው ሠልጣኞቹ ሥራ ማግኘት አልቻሉም ብለዋል።

ልጆቻቸውን የሚያስቀምጡበትን ስፍራ በተመለከተም፣ ቢሮው ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እንዲያዘጋጁ ለማድረግ እንሠራለን ያሉ ሲሆን፣ ከዛ ውጪ ግን ቢሮ ለልጆቻቸው ሞግዚት መቅጠር አቅም የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱ ሠልጣኞችንም በተመለከተ ለእያንዳንዳቸው ለመቋቋሚያ የሚሆን አራት ሺሕ ብር እና ለጉዞ 1 ሺሕ ብር እንደሚሰጥ የገለፁት ቢኒያም፣ በቂ ነው ተብሎ ባይታሰብም ቢሮው ባለው ውስን አቅም ምክንያት ከዚህ በለጠ ድጋፍ ማድረግ አይችልም ብለዋል። በሚሔዱባቸው ክልሎችም የሚመለከተው አካል በማደራጅት እና ሥራ እንደፈጥሩ በማድረግ የድረሻውን ሊወጣ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በአራት በጠለያ ስፍራዎች ከ 300 በላይ ሠልጣኞች ሥራ ሳይዙ በመንግሥት ድጋፍ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 200 የሚሆኑትን በማደራጀት ከአንባሳ አውቶብስ ድርጅት አሮጌ አውቶቢሶችን በመውሰድ እና ሱቅ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ለማድረግ እየተሠራ ነው የተባለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ከግል እና ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር በመወያት ሥራ እና የተሻለ ክፍያ የሚያገኙበት መንገድ እየተፈለገ መሆኑም ተግልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here