ይመለከተኛል! ይመለከትሻል! ይመለከተናል!

0
656

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

‹‹እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል
እህት ወንድም ቢሞት በአገር ይለቀሳል

አገር የጠፋ እለት ወዴት ይደረሳል›› አስቴር አወቀ ይህን እውነት የሆነ የስንኝ ቋጠሮ በዜማ አጅባ በሙዚቃዋ አቅርባልናለች። ሁሉም የሚያምረው በአገር ነው። አሁን ላይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ልጆቻቸውን ይዘው እየለመኑ የምናያቸው ከአገራቸው ተሰድደው የወጡ ሰዎች ለዚህም የተሻለ እድል አግኝተው ነው። ኢትዮጵያውና እርስ በእርስ ከመተዛዘን በላይ ለሌሎች ማዘን ስለሚቀናንም ይሆናል።

እኛስ የት ልንሰደድ ነው? ማን ነው አዝኖ ፍርፋሪ ሊሰጠን የሚፈቅደው? ማን ነው መልካችንን አይቶ ሳስቶልን ‹‹ሲያሳዝኑ›› ብሎ የሚያስጠልለን? የየትኛው አገር በር ነው ተከፍቶ የሚቀበለን? አፍሪካውያን’ኮ ስደት እንኳ የሚያምርብን አይደለንም። ተሰድደን ለምነን ለማደር እንኳ ተቀባይ አይኖረንም።

አሁን ላይ አገራችን ያለችበት ሁኔታ በግልጽ በሚታይ ደረጃ አሳሳቢና አስጊ ሆኗል። በአንድ በኩል ብሔርን መሠረት አድርገው የተነሱ ግጭቶች ተያይዞ ሃይማኖትንም ተገን ያደረጉ ናቸው። ይህ ግጭት፣ ውዝግብና አለመስማማት አገርን መድረስ ካለባት ደረጃ ከማዘግየቱ በቀር ግን የሚፈይደው ነገር የለም። አንድ ትውልድ ቢጠፋ ተተኪው ከነ ፍርስራሹም ቢሆን ይረከባል፤ ታሪክም ይህን መዝግቦ ያስቀምጣል። ግን ለምን? በሰላም ችግሮችን በጋራ እየታገሉ መኖር ሲቻል ለምን እርስ በአርስ መታገል?

በዚህ የሴቶች ጉዳት ከማንም በላይ ነው፤ አረጋውያንና ህጻናትን ሳንዘነጋ። በብዙ ግጭቶችና አለመስማማቶች መካከል የሚሰደዱትና የሚሰቃዩት ሴቶች ናቸው። ወንዶች ቀጥተኛ ጥቃት አድራሽ እንዲሁም የጥቃት ሰለባ ሲሆኑም ተጎጂ እናት፣ እህትና ቤተሰብ ነው። ይባስ ሲል፤ በአዲስ ማለዳ ጥቅምት 8 ቀን 2012 50ኛ እትም ላይ ቤተልሔም ነጋሽ ‹‹ሴቶችን ከጥቃት የመጠበቅ ቸልተኛነት›› በሚል ርዕስ በማኅበረ ፖለቲካ ገጽ እንዳስነበቡት፤ በሕዝቦች መካከል በሚኖር ጠብ አንደኛው ወገን ሌላው ላይ የሚፈጽመው ከፍተኛ ንቀትና ክህደት አንዱ ማሳያ አስገድዶ መድፈር ነው፤ ይህም በሴቶች ላይ ይፈጸማል።

በዚህ ደረጃ የተፈጸመ ድርጊት መኖሩን እስከ አሁን በመረጃ ያየን ባለመሆኑ ይቆየን። ነገር ግን በኢትዮጵያውን መካከል ሊገመት የማይችል የእርስ በእርስ ግጭት ተፈጥሮ ለተመለከተ፤ ይህኛውም እንደማይከሰት ምንም ዋስትና የሚሰጥ አይገኝም። ያም ብቻ አይደለም፤ እሳት ቤት ካጠፋ በኋላ እንጂ ቀድሞ ጩኸት ሰምቶ የሚደርስ የመንግሥት አካል አለመኖሩም ልብ ሊባል ይገባል።

በዛም አለ በዚህ አሁን መብት መጠየቂያ ሰዓት ላይ የምንገኝ አይመስለኝም። ስጡን የምንለው ሥልጣን፣ አስጠብቁልን የምንለው የመኖር መብት፣ አሳዩን የምንለው እኩልነትና ሌላውም ሁሉ ተጨፍልቋል። አሁን ሁሉም በሰውነትና በኢትዮጵያዊነት ቋት ውስጥ ገብተው ተውጠዋል። ዛሬ አገር ደኅና ትሆን ዘንድ መጠየቂያ ጊዜ ነው። አለበለዚያ ከነበረው የከፋ እንደማይመጣ እርግጠኛ መሆን አንችልም።

አገር ደኅና እንድትሆን የሴት ድርሻ ቀላል አይደለም። ዱላ ይዞ የሚወጣ ልጇን ማስቆምና መከልከል፣ ለሐሰተኛ ወሬ መልዕክተኛነት የሚከፈለውን ወንድሟን ተው ማለት ይጠበቅባታል። ‹‹ይለይልንና እንፍረስ!›› የሚለው ትርፍ አገር ላላቸው ይሠራ ይሆናል፤ አንድ ኢትዮጵያን አገራችን ላደረግን ግን ፌዝ ነው። እናም ሴቶች! መብት ስንጠይቅ ኖረናል፤ የአገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ ግን ከማንም የምንቀበለው በትር አይኖርም። ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ካለብንም እንሳተፍ፤ እስኪሰጡን ከመጠበቅ ሄደን እንቀበል። በአገራችን ላይ ወንዶችን ብቻ ወሳኝ ሲሆኑ ቁጭ ብለን አንመልከት፤ በአገራችን ጉዳይ ላይ ድምጻችንን ለማሰማት ጊዜው አሁን ነው።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here