የሰብዓዊ ቀውስ የተጋረጠባት ኢትዮጵያ!

0
790

ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ አራትና አምስት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እያስተናገደች የምትገኝ አገር ሆናለች፡፡ ሰብዓዊ ቀውሱ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቀጥታ የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ፣ ቀሪው ዜጋ ደግሞ በተዘዋዋሪ የገፈቱ ቀማሽ መሆኑ አልቀረም፡፡

እንደ አገር ኢትዮጵያን የገጠማት ውስብስብ ችግር ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሄድ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተፈለገለት አሳሳቢ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የሰብዓዊ ቀውስ አደጋዎች ያስከተሉትን ችግር ጋዜጠኛ ዋለልኝ ክፍሌ እንደሚከተለው በዝርዝር ከትበውታል፡፡

 የፈረንጆቹ 2022 ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ ፈትኗታል፡፡ ተደራራቢ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ያስተናግድንበት ያለፈው ዓመት ተሻጋሪ ችግሮች ከ2023 ተጨማሪ ቀውሶች ጋር ተደምሮ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንን የለጋደሾችን እጅ ጠባቂ አድርጓቸዋል፡፡

ኢትዮጰያ አጋጥሟት በነበረውና ዛሬም በቀጠሉት በርካታ ተደራራቢ ሰብአዊ ቀውሶች ምክንያት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ችግሮች መበራከታቸውን ተክትሎ፣ ከፍተኛ እና አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቶች ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀቡ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ(OCHA) በመጋቢት ወር መጨረሻ ያወጣው ሪፖርት ለዚህ በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በ2023 ኢትዮጵያ በመላው አገሪቱ ለተከሰተውን፣ የሰብዓዊ ቀውስ ምለሽ ለመስጠት 4.6 ቢሊዬን ዶላር ወይም ኹለት መቶ አርባ ሰባት ቢሊዬን አምስት መቶ ሚሊዬን ሰባት መቶ ሺሕ (247,500,700,000.0) ብር ያስፈልጋታል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት በሰፊዊ ሲያሰጠነቅቁት የከረሙትና አሁን በርካቶችን ለእለት ደራሽ እርዳታ የዳረገው ፖለቲካዊ ቀውስ፣ በአየር ንበረት ለውጥ ሳቢያ ከተከሰተው መጠነ ሰፊ ድርቅ ጋር ተዳምሮ የኢትየጰያን ችግር በእንቅርት ላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት በዚሁ ሪፖርት ላይ እንዳመላከተው ኢትዮጵያ ኋላ ቀር በሆነው የግብርና ስርዓቷ የተነሳ፣ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለሚመጡ ችግሮች በእጅጉ የተጋለጠች ሆናለች፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ የተከሰተው የዝናብ እጥረትም አሁን ላይ ሚሊዮኖችን ሰዎችን ለረሃብ ሲያጋልጥ በርካታ ሚሊዮን የቤትና የዱር እንስሳትን ገድሏል፡፡

ሁኔታው በእያንዳንዱ የበልግ ዝናብ ወቅት ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በተለይም በምስራቅና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የምግብ እጦትና ረሃብ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የውሃ አቅርቦት እና የጤና ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንዲሄድ እያደረገው ይገኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ ዛሬም ባላባራ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እየዳከረች ነው፡፡ እዚህም እዛም በየዕለቱ ንፁሃን በማንነታቸው የተነሳ ይገደላሉ ከቀያቸውም ይፈናቀላሉ፡፡ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. በ2022 መገባደጃ በሰሜን ኢትዮጵያ (አፋር፣ አማራ እና ትግራይ) ለኹለት ዓመታት ያክል ሲደረግ የነበረውና ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ምንጭ ሆኖ የዘለው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መቋጫ ያገኘ ቢመስልና፣ በአከባቢው አንፃራዊ ሰላም ቢያመጣም፣ በግጭቱ ምክንያት የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ለሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት የሚቀጥል ስለመሆኑ ለመናገር የፓለቲካ ተንታኝ መሆንን አይጠይቅም፡፡

በሰሜኑ የኢትየጵያ ክፍል ብቻም ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ ይህም ሰብአዊ አቅርቦትን በማደናቀፍ እንዲሁም በክልሉ ዓለፍ ሲል ደግሞ ወደ አማራ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት እያደረገው ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ አሁን ላይ 4.6 ሚሊዬን በላይ ህዝብ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሀኗል፡፡ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች እየተፈጠሩ የሚገኙት ፖለቲካዊ ግጭቶች አለመቆማቸው ሲታይ ደግሞ ይህ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ አሃዝ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ለምሳሌ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዓመቱን ሙሉ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የነበረው ጦርነት እየቀነሰ በመምጣቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በ2023 መጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ማቀዱን ይፋ አድርጓል። በተቃራኒው ግን በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልል አጎራባች አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ግጭቶች መንገዶች እንዲዘጉ በማድረጋቸው ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መገለለ ስለመዳረጉ ክልሉ ይናገራል፡፡

ይህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የዋጋ ግሽበት አስከትሏል፡፡ በዚህም በክልሉ የረጂ ያለህ የሚለው ህዝብ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች መፈናቀልና ሰብዓዊ ፍላጎቶችን ማስከተላቸውንም ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ታዲያ ይህንን ከፍተኛ አደጋ በአገሪቱ ላይ የደቀነውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመመከት ይቻል ዘንድ “ኢትዮጵያ፣ የ2023 የሰብአዊ ምላሽ እቅድ” ሰብዓዊ ምላሽ እቅድና ሁኔታ የሚያሳይ ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ እቅድ መሰረት በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ለዕለት እርዳታ ጠባቂነት ከተዳረጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከ20 ሚሊዬን ለሚበልጡት ሰብዓዊ ድጋፍ የማዳረስ ዕቅድ እንዳለው ተመላቷል፡፡

በዚህ የተመድ ዕቅድ መሰረት እ.ኤ.አ. በ2023 ቅድሚያ የሚሰጠው የሰብአዊ ምላሽ በሦስት መንገዶች ይከናወናል፡፡ ይህም አፋጣኝ የህይወት አድን እርዳታዎችን ማዳረስ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉን አቀፍ የአስፈላጊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግና እና ከመሰል ችግሮች ለማገገም እና ለመቋቋም የሚረዱ ዘላቂ ድጋፎችን ማድረግ እንደሆነ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የችግሩ ግዝፈት ግን በዚህ ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡ ከመነሻውም ቢሆን ለዚህ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገውን 4.6 ቢሊዬን ዶላር የማፈላለግና ከለጋሾች መሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሚሆን የሚናገረው ተመድ ሌላም ፈተና ከፊቱ ስለመደቀኑ ያስጠነቅቃል፡፡ሃገሪቱ በ2023 በርካታ፣ እና ተደራራቢ ቀውሶች ከፍተኛ የሰብአዊ ፍላጎቶችን መፍጠራቸውን ይቀጥላሉ በማለት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ ከዓለም ማኅበረሰብ ለመደበቅ እየጣረ ያለ ይመስላል፡፡ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ እየተከሰተ ሚሊዮኖች የሚላስ የሚቀመስ ባጡበት በዚህ ጊዜ የስንዴ ከምርት ወደ ውጭ መላክ ስለመጀመሩ ለዓለም ለማሳየት መጋጋጡን ለዚህ እንደማሳያ የሚያነሱ ብዙ ናቸው፡፡ ከተፈጠረው ከፍተኛ ቁውስ አንጻር መንግሥት እውነታውን በመቀበል አፋጣኝ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ ባጋጠማት በዚህ ችግር ምክንያት የሚደርሰውን ሰብዓዊ ኪሳራ ቢያንስ መቀነስ ይቻላት ዘንድ የለጋሾችን ከፍ ያለ የህይወት አድን እና የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ይኖርባታል ይላል የኦቻ ሪፖርት። ሪፖርት እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2022፣ የኢትዮጵያ ከአፍጋኒስታን እና የመን በመቀጠል ሶስተኛዋከፍተኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የጠየቀች ቢሆንም ከዚህ ውስጥ ማግኘት የቻለቸው ግን 51 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ቀውስ የተነሳ በከፍተኛ የሰብአዊ ፍላጎቶች በመጨመራቸው ነው ይላል ድርጅቱ፡፡ ይህም በዓመቱ ውስጥ ያሉትን ጥልቅ፣ የተራዘሙ እና ውስብስብ የሰብዓዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ ለመፍታት በቂ አልነበረም።

ሁኔታው በ2023 ይሻሻላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የሰብአዊ ፍላጎቶች ከፍተኛ እንደሆኑ እና የሰብአዊ ቀውሱ አሁንም ከባድ እና ውስብስብ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል። አስቸኳይ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገላቸው ችግሩ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህም ቀድሞውንም ተጋላጭ የሆነውን ህዝብ ለከፋ ችግር እንዳያጋልጥ ያሰጋል፡፡ እናም መንግስት ችግሩን መሸፋፈን በመተው የችግሩን ጥልቀት በመቀበል የህዝብን ህይወት የሚታደግ የተግባር እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here