ዳሰሳ ዘ“መደመር” ትናንትን ለመቀየር፥ ዛሬን አስተካክሎ መሥራት!!!

0
837

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር በዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው “መደመር” መጽሐፍ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ታትሞ ለአንባቢያን መቅረቡ ይታወቃል። መጽሐፉን ያነበቡት መላኩ አዳል የመጽሐፉን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በማንሳት ትችታቸውን አቅርበዋል።

እንደ መግቢያ
ለመደመር ዋናዎቹ ገባሮች የጋራ እሴቶቻችንና ተፈጥሯዊ መስተጋብር ናቸው። መደመር ለአንድ አገር ስኬት፣ አለመደመር ደግሞ ውድቀት ወሳኝ ነው። መደመር ያሉንን ጥሩ እሴቶች ይዘን፣ ጎጂዎችን አስወግደን፣ አዲስ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን እየጨመሩ አዎንታዊ ታሪክን መሥራት ነው ይሉናል። ለእኔ መደመር፣ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ሲያቀነቅነው የኖረው አንድነት ነው።

የሰው ልጅ ፍላጎቶችን ሁሉ የሚመራው ህልውናን የማረጋገጥ ጥቅል ፍላጎት ነው። ይህ ፍላጎት በቀጥታ ራስን ከአደጋ የመከላከልና በሕይወት የመቆየት ፍላጎትና በኹለተኛ ደግሞ በተዘዋዋሪ ህልውን ለማረጋገጥ ደግሞ ስጋዊ፣ የክብር (ሥም) እና የነፃነት ፍላጎቶች አሉ። ለእነዚህን ፍላጎቶች መሟላት ለመሥራት ደግሞ ስለሰው ማወቅ ያስፈልጋል። ሰው ፍላጎቶቹ በስርዓት ከተሟሉለት፣ አዎንታዊነቱ የሚያመዝንና ተደማሪ ሲሆን ያለዚያ ግን ህልውናውን ለማረጋገጥ ሲል አሉታዊውን ይመርጣል። የዚህን ሒደት ለማስተካከል ደግሞ የጋራ ራዕይ፣ መተማመንና ተነሳሽነት ያስፈልጋል። የፉክክርንና የትብብርን ሚዛንን መጠበቅ ይጠይቃል። ለዚህም መፍትሔው ለሁሉም የሚሆን አገራዊ እውቀት፣ ርዕዮትና ስርዓት እንዲኖር መሥራት ነው ይላሉ።

ርዕዮት ዓለም
ይህን ለመምራት ደግሞ ለአገር የሚጠቅም ርዕዮት ዓለም ይጠይቃል። ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም፣ ሶሻል ዴሞክራሲና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተዳሰዋል። ሶሻሊዝም እኩልነትን ሲያቀነቅን፣ ካፒታሊዝም ነፃነትን ያቀነቅናል። ግን የሶሻሊዝም እኩልነት ሐሳብ የሰው ነፃነትና የውድድር ፍላጎትን በመግታት ምርታማነትን ይቀንሳል። የካፒታሊስቱ የነፃነት ሐሳብ ደግሞ በአልተደላደለ የውድድር ሜዳ ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ደካሞችን የበለጠ ተጎጂ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። እናም የተሻለ ሀብት ያፈሩ አገሮች ኹለቱንም ርዕዮቶች በማጣመር የሶሻል ዴሞክራሲን ፈጠሩ። ይህ ስርዓት ምርታማነት እንዳይገታ ጥረት እያደረገ፣ በሌላ በኩል ደካሞችን ለመርዳት የማኅበራዊ ደኅንነትን በጠንካራ የታክስ ስርዓት ሀብትን በመሰብሰብ ለሌሎች ያዳርሳል። ችግሩ ሀብትን ባላሳደገች አገር የመተግበሩ አስቸጋሪት ነው፣ ምን ሊከፋፈል? ከዚህ በመነሳት የምሥራቁ አገሮች ልማታዊ መንግሥትን በመመስረት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበዋል። በተጓዳኝም የተቆማትን ግንባታ አጠንክረው፣ ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገሩ አሉ። እኛም ከእነሱ የወሰድነውን ሐሳብ ለመተግበር የሞከርነው ገበሬውንና ዝቅተኛ ‘ምሁሩን’ በማቀፍ ነው። ዓላማው ግን አገርን የማሳደግ ሳይሆን ተቋማትን በማዳከም ወይም ባለማቋቋም ሥልጣንን የማራዘሚያ መንገድ ሆኖ ያገለገለና በመጨረሻም በመንግሥት ደረጃ የስርቆት መንኸርያ እንድንሆን ነው ያደረገን ይላሉም።

ይህ የሚያሳየን፣ ለእኛ የሚሆነው፣ በእኛ ለእኛ መታሰብ እንዳለበትና በጥንቃቄ መተግበር እንዳለበት ነው። እና የተሻለው ርዕዮት የቱ ነው፣ በምን ሁኔታ ሲተገበር? ትብብር ከውድድር የተሻለ መሆኑ ማንም ያውቃል። ችግሮቻችን፣ በኅብረትና በትብብር መፍታቱ የተሻለ የእኔነትንና በአጭር ጊዜ መፈታትንም ያመጣል። ችግሩ ተፈጥሯዊ ሊሆንም፣ ላይሆንም መቻላቸው ነው። ምክንያቱም ትብብር አስፈላጊ የሆነውን ያህል ውድድርም አስፈላጊ ነው። ስለዚህም የትብብሩንም፣ የውድድሩንም ሜዳ በሕግ አርቆ የመሥራትና የማስተካከል ሥራ የመንግሥት ነው። የመንግሥት፣ ፖለቲከኞች፣ ልኂቃ፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የግል ባለሀብቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና መገናኛ ብዙኀን ተሳትፎ ደግሞ ችግሮችን ለመፍታትና የተሻሉ ሐሳቦች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግና መተግበር መሆን አለበት። የመጨረሻው መዳረሻችን ለሁላችንንም የምትሆን፣ ዲሞክራሲና የአገር ህልውና የማይጋጩበትን፣ በባሕል ላይ የሚቆም የዲሞክራሲ ስርዓትን መገንባት ነውና።

የመደመር እንቅፋቶች
ለመደመር እንቅፋቶች በጠቅላላው ያለማወቅ ውጤቶች የሆኑት በእውቀትና አመክንዮ አለመመራት፣ የችግሮቻችንን መንስኤ መለየት አለመቻል፣ የአንድን ጉዳይ የመንስኤንና ውጤትን ግንኙነት መሰረት ባደረግ መንገድ በሙሉ ለማየት አለመቻል፣ የልኂቃን በእውቀት አለመብሰል፣ ኑባሪያዊ ሁኔታዎችን አለመረዳት፣ ስህተትን በጊዜ አለማረም፣ ድኅነት፣ ድንቁርና፣ ችጋር፣ ድርቅ፣ የደኅንነት ስጋት፣ ግለሰባዊና መዋቅራዊ ጭቆናዎች፣ ለሥራ ያለን ክብር ማነስ፣ የሲቪል ማኅበራት አለመጠናከር፣ የጋራ እሴት መዳከም፣ ብሔራዊ መግባባት አለመኖር፣ የመተማመንና የመቻቻል ባሕል አለመኖር፣ የውይይት ባሕል ማነስ እና የዴሞክራሲ ባሕል አለመኖር ናቸው።
በተጨማሪም የተጣመመ የታሪክ ትርክት፣ አገራዊ ብሔርተኝነትና አርበኝነት መድከም፣ የወንድማማች ግንኙነት መላላት፣ የሕዝበኝነትና ልኂቅነት ጉዳይ ፖለቲካችን ውስጥ መጠንከር፣ የቡድን ማንነት ጥያቄዎች የችግሮች አባባሾች መሆናቸው፣ ቡድናዊ አክራሪነት፣ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምና የቀይ ባሕር አካባቢ ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማነስ፣ ብሔራዊ ጥቅምን አለመለየት፣ ስደት፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ያልተጠናከረ የሰላምና የፀጥታ ማስከበር ግንኙነት፣ የወደብና የባሕር በር አለመኖር፣ ዲያስፖራው ለአገሩ እንዲሠራ አለማድረግ፣ ተጠያቂነት አለመኖር፣ የአገረ መንግሥት ቅቡልነት ማነስ፣ የፓርቲና መንግሥት መደበላለቅ፣ የሞራል አለመኖርና ንቅዘት፣ የአመራሮች አቅም ማነስ፣ መሪዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር አለመቻል፣ አካታች የሆነ የአመራር ስብጥር አለመኖር፣ የሰላም መጥፋት፣ የመንግሥትና የስርዓት ጉድለት፣ የገበያ ጉድለት፣ የፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር፣ በሕገ መንግሥቱ ይዘትና ሒደት ስምምነት አለመኖር፣ የተቋማት አለመደራጀትና የተደራጁትም ውግንናቸው ከሕዝብ ጋር አለመሆን የመሳሰሉት ናቸው ብለዋልም።

ሌላውና ዋናው መሰናክል የልማት ሥራዎች በበቂ ሰላልተሰሩ የአገር ብሔር ምስረታው መጓተቱ ነው። ይህም የመሪዎችን ቅቡልነት በመቀነስ፣ ሰላም እንዲጠፋ አድርጓል። በኢኮኖሚውም ዘርፍ ዕድገት ቢመዘገብም መሰረቱን እርዳታና ብድን ያደረገ በመሆኑ እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ችግር የነበረበት ነው። በተጨማሪም የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተፈላጊ ምርቶች አገር ውስጥ ማምረት አለመቻል፣ ሥራ አጥነት፣ ደካማ የፕሮጀክቶች ክንውን፣ የልማት ፋይናንስ እጥረት፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በዩኒቨርስቲዎች መካከል ትስስር አለመኖር፣ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ አለማደግ፣ ሀብትን የመጠቀም የአቅም ውስንነት፣ ለዓለም ገብያ የምናቀርባቸው ምርቶች ጥራትና ዋጋ መውረድ፣ የምርቶች ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና፣ የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ የኮንትሮባና ሕገ ወጥ ንግድ፣ የበጀት ጉለት፣ ቁጠባና የኢንቨስትመት ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የግብር ገቢ መቀነስ፣ የሰላም መጥፋት ወዘተ ተጨማሪ የጥራቱ ጉድለት ማሳያዎች ናቸው። ብዝኀነታችን ትልቅ መከላከያ፣ ሰፊ ገቢያ፣ ትልቅ የገቢ ግብር፣ ብዙ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንኙነት መሰረት ቢሆንም ይህ እንዲሆን ግን በሰው ልማት ላይ የተሠራው ሥራ በቂ ባለማሆኑ ምክንያት ሸክም እንጂ አምራች አልሆነም ይላሉ።

ትችት መጽሐፉ ባነሳቸው ጉዳዮች ዙሪያ
1. መጽሐፉ የአገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ተዳሰውበታል። ነገር ግን በጣም ብዙ የሚጣረስ ሐሳቦችን የያዘ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የማኅበራዊ ሳይንሱ ሐሳብና ጸሐፊው ለማለት የሚያስቡት ስብከት የማይገኛኝ ስለሆነ ይመስለኛል። የችግሮች መፍትሔ የተጠቆመው በጥቅል እንጂ ይህን ተጠቅምን እንለውጠው የሚል ሆኖ አላገኘሁትም። በመቅድሙ ላይ የባሕልን ክፍሎች እሴቶችን፣ ወግና ልምድን፣ ቋንቋን፣ ምልክቶችንና ሳይንስና ቴክኖሎጂን ከራሱ ካባሕል ጋር ሲቃላቀል ይታያል። ሁሉንም የርዕዮተ ዓለም በጥቅል ከማቅረብ በዘለለ፣ በምን ርዕዮተ ዓለም የኢትዮጵያን ችግር እንፈታለን የሚልም ነገር አልተጠቆመም። የእሱ አቋሞች ሳይታሰቡ በተዘዋዋሪ የሚታዩ እንጂ ደፍሮ እንዲህ መሆን አለበት ሲል አይታይም። የጤናና የኢንዱስትሪ ማሻሻያ አማራጭ ሐሳብ አልተነሳም።
2. መደመር ሁሉ ሲነርጂ (synergy) ነው ብሎ የማመን ነገር ይታይበታል። ይህ ግን ተፈጥሮን ካለመረዳት የመነጨ ነው። ተፈጥሮ በብዙ ተቃራኒ ዑደቶች (antagonists) የተሞላችም መሆኗል አለመረዳትም ነው። ከዚህ ጋር በተገናኘ እውቀትንና ርዕዮትን አገራዊ ለማድረግ መታሰቡ ይብል የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ፤ መደመር ሲነርጂ እና የተቃርኖ ዑደቶች የሚሆኑበት ኢትዮጵያዊ እውነትና እውቀት ሲዳሰስ አይታይም። በሁሉም ላይ በሚያሰኝ መልኩ የምዕራቡንና የምሥራቁ ዓለም ሐሳቦችን ቅጂ እንጂ ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ጋር የተንሰላሰለ አማራጭ ሐሳብ ሲያቀርቡ አይታይም። ስለዚህም መደመር በምንም መልክ አገራዊ የሚያሰኘው ነገር አላየሁም። እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆንም የፖሊሲና የስትራቴጂ አቅጣጫ አልተጠቆመም።

3. ነፃ ፈቃድ ምን እንደሆነ ባልተተነተነበት ሁኔታ ነፃ ፈቃድ አለ ብሎ፣ በዚህ መሰረት ያደረጉ ትንተናዎች፤ ሰዎች መውጣት ከማይችሉት የአካባቢ ተፅዕኖ ነፃ ይወጣሉ ብሎ መፃፍ ስህተት ነው። የሚሻለው ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር ስለሌለ፣ ሰውን ከአካባቢ ተፅዕኖ ለማውጣት ስለማይቻልም፣ አካባቢንና ማኅበራዊ ስራን በመስራት የአካባቢ ተፅዕኖውን እንዴት እንቀይረው ነው። ሰው ከሌሎች እንሰሳት የተለየው ችግር መፍታት የሚችል ለአዋቂዎች በአማካኝ 1 ሺሕ 300 ግራም የሚመዝን አዕምሮ ባለቤት መሆን በመቻሉ ነው። የአስተሳሰባችን ሁኔታ በነርቭ ህዋሳት ብዛት፣ በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት፣ በዘረ መል (ጀነቲክስ) እና በውጫዊው የዓለም ሁኔታ የሚወሰን ነው። የነርቭ ህዋሳት በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት በሰው ውስጥ ከፍተኛ መሆን በተለይም ፕሪፈሮንታል ኮርቴክስ ላይ ያለው ከፍተኛ አደረጃጀትና ግንኙነት ትልቁ አሳቢ ፍጡር እንዲሆን አድርጎታል። አዕምሯችን በመነጋገር (ኮሚኒኬት) ማድረግ በሚችሉ የነርቭ ህዋሳት መካከል ብቻ በሚደረግ የኔትወርክ (የሞጁሎች) ስብስብ ነው።

እነዚህ ሞጂውሎች በተለይም በግራው የአዕምሮ ክፍል የሚገኙት ምንም እንኳን የተገናኙ ቢሆንም የራሳቸውን ሥራ ያለ ማዕከላዊ ዕዝ በራሳቸው መሥራት የሚችሉ ናቸው። ይህም ከተለያዩ ሞጁውሎች የተገኘውን የተሻለ ውሳኔ መምረጥና ትክክል የመወሰን ዕድሉ እንዲሰፋ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ ዓይነት ኀይል (ንቃተ-ህሊና) የምንመራ እንድንሆንም አስችሎናል። በአምስቱ የስሜት ህዋሳታችን ከውጭ የምናገኝው ኢንፎርሜሽን ለእያንዳንዱ የሞጁውል መፈጠር ወሳኝ ነው። እንደተባለው ለአዕምሮ ዕድገት አንዱ ግባት፣ ከአካባቢያችን የምናገኘው ትምህርትና ሥልጠና ነው። ብዙዎች የአዕምሮ ውሳኔዎች ኢንፎርሜሽኑ ከንቁው የአዕምሮ ክፍል ሳይደርስ ባልነቃው የአዕምሮ ክፍል ነው። ምክንያቱም ንቁ የአዕምሮ ክፍል ውሳኔዎች ብዙ ጊዜና ሜሞሪ ስለሚፈልጉ ውድ ናቸው። ይህም በጠቅላላው የሚያመለክተን ሰው በተወሰነ ደረጃ ንቃተ-ህሊናውን የሚጠቀም ቢሆንም፣ በአብዛኛው ጊዜ ግን የውስኔዎቹ መነሻ የአልነቃው የአዕምሮ ክፍል መሆኑን ነው። በተጨማሪም፣ ዘረ መል እና አካባቢ (ማኅበራዊ መስተጋብር) ህሊናን ብሎም አዕምሮን በተፅዕኖ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አዕምሮም በህሊና፣ በዘረ መልና በአካባቢ ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነው። እንዲሁም ሁላችንም ዩኒቨርሲቲን በሚመራው የተፈጥሮ ፊዚካል ሕግ ውጭ አይደለንም። ይህም ሁሉንም የፊዚሎጂና ኢኮሎጂ መስተጋብሮችን እንደሚወስን ነው። ስለዚህም የነፃ ፈቃድ መኖር እጅግ አጠራጣሪ ነው።

4. የኢትዮጵያ ችግሮች ከእውቀት ማነስና የዴሞክራሲያዊነት ባሕል አለመጎልበት በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል አወቃቀሩ ስምምነት አለመኖሩ እና በዘውግና በዜግነት ፖለቲካው አራማጆች መካከል ያለው ልዩነት መጉላቱ ናቸው። እነዚህን ተቃርኖዎች ለመፍታት የሚበጀው መንገድ አልተጠቆመም። እንዲያውም በዜግነት ፖለቲካና በዘር ፖለቲካ መካከል ሲዋልል ይታያል። በአንድ በኩል የብሔር ጥያቄዎች መነሻ ምክንያት እንዳላቸው አምኖ፣ ግን ከተነሱበት ዓላማ አልፈው ሔደዋል ብሎ እንደሚያምን እያየህ፣ በሌላ በኩል ግን ከዚሁ የብሔር ፖለቲካ ቅርቃር አስተሳሰብ እንዳልወጣ ትዝብት ላይ ይጥላል። ለምሳሌ፣ የግለሰብ መብት መከበር የቡድን መብተን አያስከብርም ሲል አሳማኝ ማስረጃ አያቀርብም።

5. ብሔር ማለት በቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብና ባሕል፣ መልከዓ ምድር፣ ሀብትና የገቢ መጠን፣ የፍላጎቶች ልዩነት ውስጥ አንድ ጥቅልና ብሔራዊ ደረጃ ያለው፣ እርስ በርስ የተሳሰረ፣ የፍላጎትና የምርጫዎች አንድነት ወይም ተመሳሳይነት ያለው ሕዝብ መጠሪያ ማኅበራዊ ጽንሠ ሐሳብ ሲሆን ይህም ልዩነት ለአገር ደኅንነት አደጋ የማይሆኑበትን ትስስር ይፈጥራል። የብሔር ግንባታ ያለ ግዳጅ፣ ዘመናዊት ትምህርትን፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን (የኮሚውኒኬሽን አውታሮች፣ መንገድ)፣ የገጠሩን የእርሻ ዘዴዎች ማሻሻል፣ ነፃ ገቢያንና የኢኮኖሚ ትስስርን፣ መልካም አስተዳደርን ግባት ያደርጋል። እነዚህ ግባቶች አብዛኛው ሕዝብ የግልና የጋራ ደኅንነቱን፣ ኑሮውን ከውጭ ኩነቶች ጥገኝነት የሚላቀቅበት የተግባር ደረጃ ይፈጥራል። የብሔር ግንባታ ሕዝብ የጋራ ማንነት የሚፈጥርበትና የሚያዳብርበት የረጅም ጊዜ ተግባር ነው። የአገራችን ዋናው ችግር እንደ ሕዝብ የብሔረ መንግሥትነት ተግባር አለመፈፀሙና ከብሔር ደረጃ አለመድረሳችን ነው።

ይህንንም ክፍተት የዘውጌ/ዘር ፖለቲከኞች ለራሳቸው ከፋፋይ ፖለቲካ መጠቀማቸው ነው፣ የሌለው ብሔር መሰረት ያደረገ የብሔር ጭቆና ነበር የሚል የሐሰት ትርክት። ብሔር ግንባታ የተሳካ የሚሆነው የዳበረ የካፒታል ልማትና መስፋፋት ከጥሩ የፋይናነስ አስተዳደርና አድሏዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ ወካይ ከሆነ አስተዳደር ጋር ሲጣመር ነው። ስለዚህም ለዚህ የብሔር ግንባታ ጠንክረን በኅብረት መሥራት ይጠበቅብናል። ሰውየው ግን ብሔር በብዙ አዋቂዎች እንዴት እንደታየ ሲወራ ይቆይና ብያኔውን ሳይሰጥ ያልፍና አንዴ ብሔር ከሌሎች የጎላው ፖለቲከኞች ስላጮሁት ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የብሔር ጭቆና ስለነበር ነው ይለናል። የብሔር ጭቆና ነበር ሲል ጨቋኝ ብሔር ነበር እያለ መሆኑን እረስቶ ወይስ አሁንም በፈረደበት አማራ ሥም ጓዶቹን ለማስደሰት? በአንድ በኩል የሲቪክ ባሕል ማደግ ለዴሞክራሲ ዕድገት ወሳኝ ነው ይልና የማንነት ፖለቲካ ሲደግፍ ይገኛል።

በጠቅላላው መጽሐፉ መነበብ ያለበት፣ ነገር ግን ለርዕዮት ዓለምነት የሚበቃ ወጥ አገራዊ ፍልስፍና የሌለው ከዛም ከዛም የተለቀመ የሐሳብ ስብስብ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here