በምስረታ ላይ ያለው የአማራ ባንክ የአንድ ቢሊዮን ብር አክሲዮን ሸጠ

0
472

በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ አክሲዮን መሸጥ የጀመረው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በኹለት ወር ተኩል ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አክሲዮን ውል የፈፀመ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 725 ሚሊዮን ብሩ የተከፈለ እንደሆነ አስታወቀ። ባንኩ ከተፈቀደለት የኹለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ ግማሹን ያሟላ ሲሆን በመጪው አንድ ወር ውስጥም ወደ ምሥረታ እንደሚገባ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም አክሲዮን የገዙና አሁንም ተጨማሪ መግዛት ለሚፈልጉ ተጨማሪ አክሲዮኖች ለሽያጭ መቅረቡን አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል። አዲስ በተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ መሰረትም፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችም ተቀባይነት ባለው የውጭ አገር ገንዘብ ብቻ የባንክ አክሲዮኖች መግዛት እንደሚችሉ አስተባባሪዎቹ ጨምረው አስታውቀዋል። የአማራ ባንክ አክሲዮን ሽያጭች በእስከዛሬ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ሽያጭ ትልቁ የተከፈለ የአክሲዮን ሽያጭ መሆኑ ታውቋል። በምስረታ ላይ ያሉ የወለድ ነፃ ባንኮችም ከፍተኛ አክሲዮን ሽያጭ በማከናወን ላይ መሆናቸውን እና በወራት ውስጥ የምሥረታ ጉባኤያቸውን እንደሚያካሒዱ መግለፃቸው ይታወቃል።

የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የጠቅላላ ባለ አክሲዮኖች ጉባኤና ምሥረታ ለማድረግ ኅዳር 20/2012 እቅድ መያዙ ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here