መፍትሔ ያልተበጀለት የሸቀጦች ዋጋ ንረት ጉዳይ

0
1588

በዕለት ተዕለት ሕይወት ብዙዎችን እያሳሰበ የመጣው ነገር ግን ለረጅም ዓመታት መፍትሔ ያልተገኘለት የሸቀጦች ዋጋ ንረት ጉዳይ ነው። በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እና ቋሚ ገቢ የሚያገኙትን የኅብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ደረጃ አማርሯል። ሳምሶን ኃይሉ የሸቀጦች የዋጋ ንረት እና የኑሮ መወደድ የአንድ አገራን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዴት እንደሚያውክን እንዲሁም ድህነትን እንደሚያባብስ ነባራዊውን የአገራችን ሁኔታ ጨምሮ በዓመታት ውስጥ ያጋጠሙትን የምጣኔ ሀብት ከፍታና ዝቅታ በተጨባጭ ምሳሌዎች አስረድተዋል፤ መፍትሔ ነው ያሉትንም ምክረ ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የሸቀጦች የዋጋ ንረትና አጠቃላይ የኑሮ መወደድ የአንድ አገርን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከማወኩም በላይ የዜጎችን ደኅንነትን (welfare) በመቀነስ ድህነትን ያስፋፋል። ባለፉት ዐሥር ዓመታት በአማካኝ 10 በመቶ በላይ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግባለች የምትባለው ኢትዮጵያ በዚሁ የሸቀጦች የዋጋ መናርና ተያይዞ ከሚመጣው የኑሮ መወደድ ምክንያት ፈታኝ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች።

ከ2009 በፊት በአንድ አኀዝ ተገድቦ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ንረት ቀስ በቀስ በማሻቀብ በአሁን ወቅት ባለ ኹለት አኀዝ ሆኗል። የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው በነሐሴ 2011 አጠቃላይ የዋጋ ንረት 18 በመቶ ደርሷል። ይህም ባለፉት ስድስት ዓመታት ያልታየ ከፍተኛ አኀዝ ነው። የምግብ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት በአሁኑ ወቅት 23 በመቶ ደርሷል። ከዚህም በላይ በጣም አሳሳቢ የሆነው በየዓመቱ እየተጠራቀመ የመጣው የዋጋ ንረት ነው። ከ1995 እስከ 2010 ባሉት 15 ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካኝ 15 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይቷል። ይህም አሁን ምግብና ምግብ ነክ ካልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከሚታየው የዋጋ ንረት ጋር ተደማምሮ የኅብረተሰቡን ናላ እያዞረው ይገኛል።

ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የዋጋ ንረት የሚከሰተው በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል አለመጣጣም ሲኖር ነው። ይህም ማለት ወይ የሚመረተው ምርት ከፍላጎት በታች ነው ማለት ነው አልያም ፍላጎት ከሚመረተው ምርት በላይ አሻቅቧል ማለት ነው። ነገር ግን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የዋጋ ንረት መንስዔዎች እንደየዘርፉ፣ እንደየቦታው እና እንደየጊዜው ሊለያዩ ይችላሉ። እነዚህን ከግምት ውስጥ ከተን ጉዳዩን በጥልቀት ስንመረምር በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መንስዔዎች ቀጥተኛ (direct factors) እና ቀጥተኛ ያልሆኑ (indirect factors) ብለን ልንከፋፍላቸው እንችላለን።

ቀጥተኛ የሆኑ ምክንያቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም በወራቶች፣ በቀናት አንዳንዴም በሰዓታት ውስጥ የዋጋ ንረትን የሚያስከትሉ ሲሆኑ በአብዛኛው ከማምረቻ ወጪዎች መጨመር (cost-push factors) ጋር ይያያዛሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ አብዛኛውን የጥሬ እቃ ሆነ ያለቀለት ምርት ፍላጎቷን የምታሟላው ከውጭ በማስገባት ነው። የውጭ ምንዛሬ በአገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ስለማይገኝ አስመጪዎች ከጥቁር ገበያው ከፍ ባለ ዋጋ የውጭ ምንዛሬ ለመግዛት ይገደዳሉ። ይህም ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ የማስገቢያንና የማምረቻን ወጪን እንዲጨመር በማድረግ የመሸጫ ዋጋ እንዲንር ያደርጋል። በአገራችን ከውጭ የሚገቡ አልባሳት፣ መለዋወጫ እቃዎች፣ በመማሪያና የህክምና ቁሳቁሶች ላይ እና ከውጭ በሚገቡ ጥሬ እቃዎች አገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ፍራፍሬ ጭማቂ፣ ፓስታና ዳቦ ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ምንጭ ይህ ነው።i

ሌላው ደሞ በዓለም ገበያ ላይ ከሚታየው የዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ነው። ኢትዮጵያ ነዳጅ ፍላጎቷን የምታሟላው ከውጭ በማስገባት ነው። የነዳጅ ዋጋ ደግሞ የሚወሰነው በኢትዮጵያ ሳይሆን በዓለም ገበያ ላይ ባለው ፍላጎትና አቅርቦት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ምክንያት በተደጋጋሚ ትጎዳለች። የነዳጅ ዋጋ መጨመር ተፅዕኖ ነዳጅ ላይ ብቻ አይወሰንም። ነዳጅ ለትራንስፖርትና ለማምረት ዋነኛ ግብዓት ስለሆነ በእሱ ላይ የሚመጣው የዋጋ ጭማሬ በተደጋጋሚ እንዳየነው ገበያ ላይ ባሉት የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

ነገር ግን የማምረቻን ወጪን በኢትዮጵያ የሚያንረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ወይም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ብቻ አይደለም። አጠቃላይ የኑሮ መወደድ ሌላው የማምረቻን ወጪን የሚያንር ምክንያት ነው። ለምሳሌ በኑሮ መወደድ ምክንያት የገበሬዎች ለማዳበሪያና ለጸረ ተባይ የሚያወጡት ወጪ ስለሚጨምር ባሕሎች ላይ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል።

ነገር ግን ሌሎች የግብርና ውጤቶች አመረታታቸው እምብዛም ለኑሮ መወደድ ያልተጋለጡ ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጨምር ይስተዋላል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ በቅርበት ያሉ ሽንኩርት አብቃይ ገበሬዎች በአሁኑ ሰዓት አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከሦስት እስከ አምስት ብር ለነጋዴወችና ደላላዎች ይሸጣሉ። ይህንን በቅርቡ ለሥራ ከአዲስ አበባ በወጣሁበት ጊዜ የታዘብኩት ሀቅ ነው። አዲስ አበባ ላይ ግን አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከዐሥራ ስምንት እስከ ሃያ ብር እየተሸጠ ይገኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ ጅማ አካባቢ ያሉ ቡና አብቃይ ገበሬዎች አንድ ኪሎ ቡና ሃያ ብር ሲሸጡ አዲስ አበባ ግን ከስልሳ ብር በላይ እያወጣ ነው። ለዚህ ምክንያት የግብይት ስርዓቱ ቅልጥፍና የጎደለው ስለሆነ ነው። እንደሽንኩርትና ቡና ዓይነት ምርቶች ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ለመድረስ በዛ ያለና የተለጠጠ የግብይት ሰንሰለት ማለፍ ይገደዳሉ። በዚህ ላይ የድለላ፣ የትራንስፖርት እና የማከማቺያ ቦታ ኪራይ ሲደመርበት በምርቶች ላይ የዋጋ ንረት ያስከትላል።

ከላይ የተጠቀሱት ቀጥተኛ የሆኑ ከማምረቻ ወጪዎች መጨመር እና ቅልጥፍና ከጎደለው የግብይት ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ብቻ አይደሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረትን እያስከተሉ ያሉት። በቅርብ ጊዜያት በተደጋጋሚ እንዳየነው የዋጋ ንረት ይከሰታል ብሎ መጠበቅ (inflation expectation) እና አስቀድሞ መገመት (speculation) በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ንረት ሲያስከትሉ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ ከጥቂት ወራቶች በፊት ከውጭ የሚገቡ መኪኖች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ሊቀየር ነው የሚል ወሬ በሰፊው ከመሰራጨቱ በሰዓታት ውስጥ አስቀድመው ወደ አገር ውስጥ የገቡ እንደ ቪትስ ዓይነት መኪኖች ላይ ሳይቀር እስከ 30 ሺሕ ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። የብር ዋጋ ማሻሽያ (devaluate) ይደረግበታል ተብሎ በሰፊው ሲወራም አይደለም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ ቀድመው ከገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉ ጥሬ እቃዎች በኢትዮጵያ የተመረቱ ሸቀጦች ላይ ዋጋ ሲጨመር ማየት የተለመደ ነው። በዋነኝነት የዋጋ ንረት ይከሰታል ብሎ መጠበቅ እና አስቀድሞ መገመት የሚመነጨው መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ድብቅነት ስለሚስተዋልበትና ፖሊሲዎችን በግልፅ ከኅብረተሰቡ ጋር ሳይመክርባቸው ሥራ ላይ ስለሚያውላቸው ነው።

ቀጥተኛ የሆኑና በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረትን የሚያስከትሉ መንስዔዎች ከፍተኛ ኀይል ቢኖራቸውም ቀጥተኛ ያልሆኑና ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ምክንያቶች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ዋነኛው ቀጥተኛ ያልሆነና ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለው ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና በከፍተኛ ደረጃ እየተከማቸ የመጣው በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ነው። ይህን ለመረዳት ዕይታችንን የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ በስፋት መታየት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ማስፋት ይጠይቃል። በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በስፋት መታየት የጀመረው መንግሥት የላላ የገንዘብ (fiscal እና monetary) ፖሊሲ 1996 ጀምሮ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። በዚህ ምክንያት በባጀት መልክም ሆነ ቀጥተኛ በሆነ መልክ ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨው ገንዘብ ያለ ገደብ እያደገ መጥቷል፤ ተያይዞም የዋጋ ንረት ተከስቷል። ለምሳሌ በሚሊኒየሙ መባቻ አጠቃላይ የዋጋ ንረት 50 በመቶ አካባቢ መድረሱ የሚዘነጋ አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ መተግበር ጀምራለች። ትላልቅ የመሰረተ ልማት የሥራ እቅዶችን ትኩረት አድርጎ የተነሳው የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት የተመነደገ የሚመጣ የገንዘብ አቅርቦት ያስፈልግ ነበር። ስለዚህም መንግሥት ከተለያየ ምንጮች ገንዘብ በመሰብሰብ ወደ ኢኮኖሚው አሰገብቷል። ባለፉት ዐሥር ዓመታት አጠቃላይ የገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) በአማካኝ በ20 በመቶ በየዓመቱ ጨምሯል።

የመንግሥት የገንዘብ ምንጭ በዋነኝነት ሦስት ናቸው። የመጀመሪያው በግብር እና ቀረጥ መልኩ የሚሰበሰብ ነው። በሚሊኒየሙ መባቻ 40 ቢሊዮን የነበረው ዓመታዊ የመንግሥት ገቢ አሁን 200 ቢሊዮን በላይ ሆኗል። ኹለተኛው ከአገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች በብድር መልክ የሚሰበሰበው ነው። ይፋ በሆነው ዘገባ መሰረት የመንግሥት ብድር 50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። የመጨረሻው ገንዘብ በማተም የሚገኝ ነው። ይፋ የሆነ መረጃ ባይኖርም ትንሽ የማይባል ገንዘብ ታትሞ ባለፉት ዐሥር ዓመታት ወደ ሥራ ገብቷል።

በእነዚህ መልኩ ወደ ኢኮኖሚው በገባውና ከዓመት ዓመት እየጠራቀመ በመጣው ግዙፍ የገንዘብ ሀብት ምክንያት የኅብረተሰቡ ገቢ ብሎም የመግዛት አቅም ጨምሯል። ይህም ከፍተኛ የሆነ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ፍላጎት በአገር ውስጥ ፈጥሯል። ፍላጎት ባደገበት መጠን ግን ምርትና ምርታማነት አልጨመረም። ይህም ፍላጎት አመጣሽ የዋጋ ንረትን (demand-pull inflation) አስከትሏል።

መንግሥት ይህን ፍላጎት አመጣሽ የዋጋ ንረት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ነው ያመጣው ብሎ በተደጋጋሚ ሲከራከር ቢቆይም በስተመጨረሻ ግን በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣው የገንዘብ አቅርቦት መሆኑን ሳይፈልግም ቢሆን አምኗል። ይህን ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል። የመንግሥት ወጪና የባጀት ዕድገት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በዚህ ብቻ መንግሥት ሳይገደብ ወደ ዋናው መፍትሔው መሔድ አለበት። የገንዘብ አቅርቦት በመቀነስ ፍላጎት አመጣሽ የዋጋ ንረት መቆጣጠር የማዕከላዊ ባንኮች ተግባር ነው። ወደ አገራችን ስንመጣ ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ ይሆናል ማለት ነው። ነገር ግን የገንዘብ ፖሊሲን ተጠቅሞ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ባንኩ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ መላቀቅ አለበት። እዚህ ላይ መንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት።

ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከማምረቻ ወጪዎች መጨመር ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከውጭ የሚገቡትን ሸቀጦች በአገር ውስጥ ማምረት (import substitution) የሚያስችል አቅም መፍጠር፣ በሥራ ላይ ያሉትን የግል ባለሀብቶች ማበረታታትና ምርትና ምርታማነትን በቶሎ ማሳደግ ያስፈልጋል። ግብይት ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የዋጋ ንረት ደግሞ እንደ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓይነት ተቆማት በየዘርፉ በመመስረት የገበያውን ቅልጥፍና ማሻሻል ከመጠየቁም በላይ ሕገወጥ ነጋዴወችንና ደላሎችን መቆጣጠር ያሻል። ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች መፍትሔዎችን በቶሎ ሥራ ላይ ማዋል ካልቻልን ግን አገሪቱ ሌላ በቀላሉ የማትወጣው ችግር ውስጥ መግባቷ አይቀሬ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here