በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ

0
669

በሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ በተፋሰስ አገራት በተለይም ደግሞ በግብጽ በኩል የሚሰማውን ቅሬታ ተከትሎ ሰሞኑን ሦስቱ የላይኛው ተፋሰስ አገራት በአሜሪካ ዋሽንግተን ከትመው ነበር።

ግብጽ ሦስተኛ ወገን አወያይ በጉዳዩ ላይ እንዲገባ መጠየቋን ተከትሎ እና ኢትዮጵያም በተነሳው ሃሳብ በመስማማቷ በዋሽንግተን የተገናኙት የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ወጭ ጉዳይ ሚንስትሮች እና የውሃ ሚንስትሮች አሜሪካን በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ማዕከል በማድረግ ነበር። በሦስቱ አገራት የተደረገው ውይይት ታዲያ በአሜሪካው የገንዘብ ሚንስትር እና በዓለም ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ታዛቢነት መደረጉን የተለያዩ የዜና አውታሮች ሲያሰተጋቡት ሰንብተዋል። አወያይ አገር አሜሪካ ፕሬዘዳንትም በለመዱት ብዙኃኑን መድረሻ መንገዳቸው ትዊተር የተደራዳሪ አገራትን መገኘትና የተደረገው ውይይትም ፍሬያማ እንደሆነ ጠቁመው አልፈዋል።

በሦስቱ አገራት ውጭ ጉዳዮች እና ልዑካኖቻቸው መካከል የተደረገው ውይይት እና ከውይይቱ በኋላ ይፋ የሆነው መግለጫም በብዙዎች ዘንድ ትችት ሲሰነዘርበት እና ከውጫሌው ውል አንቀጽ 17 ጋር እያመሳሰሉ የአሁኑን አንቀጽ 10 ሲያነሱ ፤ሲጥሉ ሰንብተዋል። በተለይ አሜሪካ ከግብጽ ጋር ያላትን ጥብቅ ወዳጅነት በማንሳት ‹‹እንዴት ኢትዮጵያ አሜሪካን በሦስተኛ ወገንነት ታስገባለች›› ሲሉ ይሞግታሉ። ቀጥለውም አሜሪካ የግብጽን ጥቅም ከማስጠበቅ ወደ ኋላ እንደማትልና የወጣው መግለጫም በድርድሩ ግብጽ በላይነቷን ያሳችበት ነው ሲሉ ተደምጠው፤ ‹‹የዓባይን ነገር መርሳት ይሻላል ›› ሲሉም ተስፋ መቁረጥ ስሜታቸውን አስታገብተዋል።

ከዚህ በተቃራኒው የሚቆሙት ደግሞ በዛው በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ድርድሩ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አድርገው ሚመለከቱ ሰዎች ሰህተት እንደሆነና ኹሌም ለድርድር መቀመጥ የተሸናፊነት ምልክት አለመሆኑንም ያስረዳሉ። አያይዘውም በመልካም ጎን ሊታይ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነና ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ተደራዳሪዎች በእኩል አሸናፊነት ሊወጡት የሚችሉት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለድርድሩ ለመቅረብ አሻፈረኝ ማለት እንደማይኖርባት ያስቀምጣሉ።

በአሜሪካ ዋሽንግተን ተካሔደው ውይይት ቀነ ገደብ በመወሰን የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ወር አጋማሽ ድረስ እልባት ላይ ካልተደረሰ በፈረንጆች 2015 የተፈረመውን ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል። ይህም አገራት በራሳቸው ተደራድረው መግባባት ላይ ካልደረሱ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንደሚገባ የሚያትት አንቀጽ ነው። ይህንም ታሳቢ በማድረግ እስከ ተያዘው ቀነ ገድብ ድረስ አራት የቴክኒክ ውይይቶችን በማድረግ ለመስማማት ወስነዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here